Saturday, August 3, 2013

እውን ጋዜጠኛው እስክንድር_ነጋ ‹የዘር ማጥፋት› ሰብኳል? EskinderNega ይናገራል!

እውን ጋዜጠኛው #እስክንድር_ነጋ ‹የዘር ማጥፋት› ሰብኳል? (#EskinderNega ይናገራል!)





Daniel Berhane ጦማሩ ላይ’ ‹ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የዘር ማጥፋትን ሰብኳል› የሚል ዘመቻ ከጀመረ ወዲህ የጦማሩ ጥቂት ተከታዮች ተመሳሳይ ቀኖና እያስተጋቡ ነው፡፡ 
ብዙዎቻችን የእስክንድር ነጋ እስር የመንግሥት ሴራ ነው ብለን ስናምን ዳንኤልና ወዳጆቹ ግን እስክንድርን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ከማብጠልጠል አይመለሱም፡፡ የዘር ጥላቻ እንዳለበት በተለይም ደግሞ የትግራይን ሕዝብ ለማጥፋት ይሠራ እንደነበር ያለመታከት ይጽፋሉ፡፡
ለመሆኑ ለዚህ ጥላቻ የሚያበቃ በቂ መረጃ አላቸው? በነሲብ ነው የሚመሩት? ልዩ ተልዕኮ አላቸው? ወይስ የተሳሳተ መረጃ ሰለባዎች ናቸው? ሁሉንም በራሴ ለመመለስ ከሞከርኩ በኋላ ትላንት (ሐምሌ 24፣ 2005) ቃሊቲ ሄጄ ጉዳዩን በዝርዝር ገልጬለት መልሱን ጠይቄ ነበር፤ የእሱንም ምላሽ ከዚሁጋ አያይዤዋለሁ፡፡

በመጀመሪያ ስለዘመቻው፡-የውንጀላው ሁሉ መነሻ ‹ወግድ ይሁዳ› በሚል የዛሬ ዐሥር ዓመት ‹‹የእስክንድር ነጋ ንብረት ነው›› በተባለ ‹አስኳል› የተሰኘ ጋዜጣ በተከታታይ የታተመ አምድ ላይ የታተመ ጽሑፍ ነው፡፡ በተለይ በአምዱ ላይ የሰፈረ እና ጀርመኖች አይሆዶችን የጨፈጨፉበትን ታሪክ ወግኖ ይሞግታል የተባለለትን አንድ ጽሑፍ በምሳሌነት ያጣቅሳሉ፡፡
 ይሁን እንጂ በውንጀላው ላይ ሆነ ተብለውም ይሁን ባጋጣሚ ግልጽ ያልሆኑ ነገሮች መዘለላቸው እውነታውን የሚያዛቡ ነጥቦች ሆነው አግኝቻቸዋለሁ፡-
(ሀ) እስክንድር ነጋ የጋዜጣው ባለቤትም ሆነ ዋና አዘጋጅም አልነበረም፤ የጋዜጣው ባለቤት የነበረችው ትግራዋይዋ ባለቤቱ እና የልጁ (ናፍቆት እስክንድር) እናት ሰርካለም ነበረች፣
(ለ) አምዱ ላይ ይጽፉ የነበሩት የተለያዩ ሰዎች ሲሆኑ በተለይ የተጠቀሰውን ጽሑፍ የጻፉት ታዲዮስ ታንቱ ሲሆኑ እሳቸው ለጻፉት ጽሑፍ የተሰጡት አፀፋዎች በዚያው ጋዜጣ ላይ ታትመው ይወጡ ነበር (ዳንኤል የእስክንድር ጋዜጣ እንዲህ ጻፈ ሲል፣ ትግራይ ኦንላይን ግን እስክንድር ነጋ ጻፈ ብሎ አስተጋብቶታል)፣
(ሐ) ‹ወግድ ይሁዳ› የሚለው አምድ ማብራሪያ ላይ “‹‹ይሁዳ›› ሕዝብን፣ ሀገርንና ጎሣን የማይወክል ቃል ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ ውስጥም ይሁዳ የሚለው ቃል ሀገርን፣ ጎሣንና ሕዝብን አይወክልም፡፡ ይሁዳ ትርጉሙ ከሐዲ ማለት ነው፡፡ ከሐዲ ደግሞ ግለሰብ ነው” የሚል ማብራሪያ ነበረው፤ በዳንኤል ጽሑፎች ላይም ቢሆን ምንም ዓይነት ብሔር አልተጠቀሰም፣
እስክንድርስ ምን ይላል?
‹አስኳል ጋዜጣ ከመጀመሩ በፊት እኔ አራት አምስቴ ታስሬ እየተፈታሁ ሐሳቤን መግለጽ የማልችልበት ደረጃ ደርሼ ነበር፡፡ ስለዚህ የአስኳል አዘጋጅም፣ ባለቤትም አልነበርኩም፡፡ የጋዜጣው ባለቤት ሰርካለም ነበረች – በሰርካለም አሳታሚ ድርጅት በኩል፡፡ ሆኖም በጋዜጣው ላይ ለሚወጡ ነገሮች ተጠያቂ አልሆንም አልልም፤ ምክንያቱም ከሞላ ጎደል ከጀርባ ነበርኩ፡፡ ይሁን እንጂ የታዲዮስን ጽሑፎች ግን ሙሉ ለሙሉ አንብቤያቸዋለሁ ማለት አልችልም፡፡ 
እንዲያም ሆኖ ከሳሾቼ ማወቅ የሚኖርባቸው ጉዳዮች ግን አሉ፡-‹አንደኛ፤ ታዲዮስ አምደኛ የነበረ እንደመሆኑ ጋዜጣው ላይ አምደኞች በሙሉ ያለምንም ቅድመ ምርመራ ጽሑፎቻቸው በሚስተናገዱላቸው መንገድ ተስተናግዶለታል – ቅድመ ምርመራ አለማድረግ የመርሓችን ጉዳይ ነበር፡፡ የታዴዮስ ጽሑፎች ሲወጡ ከስንት አንዴ ካልሆነ በቀር ብዙ ጊዜ የተሰጠባቸው መልስ በተመሳሳይ አምድ፣ እዚያው ገጽ ላይ ይስተናገድ ነበር፡፡ 
በተለይ ካሳሁን የተባለ ሰው ከአዲግራት በተከታታይና ሌሎችም ለታዴዎስ መልስ ይሰጡት እንደነበረ አስታውሳለሁ፡፡ እንዲያውም፣ በሚሰጡት መልሶች ላይ ታዴዎስን በግል ከመስደብ አልፈው የመጣበትን ማኅበረሰብ ሳይቀር የተቹበት ጽሑፍ እንዳለ አስታውሳለሁ፡፡ ይሁን እንጂ እንደነገርኩህ ቅድመ ምርመራ ባለመኖሩ ይህንንም ሆነ ያንን መቆጣጠር አልቻልንም፡፡
‹‹ሁለተኛ፤ አምዱ ላይ ታዴዎስ ጽሑፎቹን የደመደመው በ1996 ማለቂያ ላይ እንደሆነ አስታውሳለሁ፡፡ በ1997 አምዱ ተቋርጦ ነበር፡፡ ታዲዮስ ጽሑፎቹን ሲደመድም የኢትዮጵያ ባሕል የጀርመኑን ዓይነት ነገር እንደማይፈቅድ፣ እና ይህ ዓይነቱ ነገር እንደማይከሰት እና መከሰት እንደሌለበት ተናግሮ ነበር፡፡ ሆኖም ይህንን ሳይጠቅሱ መሐል ላይ ጽሑፍ ቆርጦ በማውጣት የጽሑፉን ይዘት በትክክል መናገር አይቻልም፡፡
‹ሦስተኛ፤ የጋዜጣው ባለቤት ሰርካለም የትግራይ ተወላጅ ሆና በጋዜጣዋ ላይ የትግራይ ተወላጆችን ክፉ ትመኛለች ብሎ ማለት የእሷን ማንነት መካድ ነው፡፡ ከዚያም በላይ የሚገርመው… ያኔ ሰርካለም በማንነቷ ከተለያዩ ወገኖች ብዙ ወቀሳ ሲሰነዘርባት አሁን የሚወቅሱን እነ ዳንኤል የት ነበሩ? ለምንስ ጥብቅና ሊቆሙላት አልቻሉም?
‹አራተኛ፤ እንዲህ ዓይነቱን ዘመቻ በአፓርታይድ ዘመን የደቡብ አፍሪካ መሪዎችም በANC እና ማንዴላ ላይ ያካሂዱ ነበር፡፡ እኛ ሥልጣናችንን ከለቀቅንላቸው ነጮችን በሙሉ ከደቡብ አፍሪካ ምድር ያጠፉናል እያሉ የነጮቹን ድጋፍ ለማግኘት ይሞክሩ ነበር፡፡ አሁንም የሕወሓት ሰዎች እንደዚያ ዓይነት አካሄድ እየተከተሉ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡
‹‹በመጨረሻ ልነግርህ የምፈልገው አንድ ነገር አለ፡፡ ይህ ሰው ይህን ዘር ሊያጠፋ ይፈልጋል የሚሉ ነገሮች የሚመጡት የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ላለመመለስ በሚደረግ ጥረት ነው፡፡ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ባለበት አገር እንዲህ ዓይነቶቹ ስጋቶች ጨምሮ ሌሎችም እንደሙስና ያሉ ችግሮች ይቀረፋሉ፡፡››

No comments:

Post a Comment