Friday, July 27, 2012

ክርስቲያን ኢትዮጵያዊያን የሙስሊም ኢትዮጵያዊያንን ትግል እንዲቀላቀሉ የቀረበ ጥሪ

ክርስቲያን ኢትዮጵያዊያን የሙስሊም ኢትዮጵያዊያንን ትግል እንዲቀላቀሉ የቀረበ ጥሪ

ትግሉም ድሉም የጋራ ነው!!!

Ginbot 7 weekly editorialየኢትዮጵያ ሙስሊሞች ለሰባት ተከታታይ ወራት ሲያደርጉት የነበረው ሃይማኖታዊ መብቶችን የማስከበር ትግል፣ ወያኔ በወሰደው አረመኔያዊ እርምጃ ምክንያት ወደ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግሯል።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ሲገልፀው እንደነበረው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጥያቄ የሙስሊሞች ብቻ አይደም። የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጥያቄ የመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ ነው።
የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ለሙስሊም ወገኖቻችን የእምነት መብቶች ጥያቄ የሰጠው የጥይት ምላሽ የጥያቄዎቻቸውን ደረጃ አሳድጎታል። ቀድሞ የሙስሊሞች ጥያቄ “የእምነት መብቶቻችን ይከበሩ” “መንግሥት በሃይማኖታችን ጣልቃ አይግባ”፤ “መሪዎቻችንን እኛው ራሳችን እንድንመርጥ ይፈቀድልን”፤ “እኛም እንደ ዜጋ የመሰማት መብት አለን” እና የመሳሰሉት ነበሩ። አሁን ግን ጥያቄው በሕይወት የመቆየትና እንደ ሰው የመቆጠር ጉዳይ ነው። ዛሬ የሙስሊም ወገኖቻችን ጥያቄ በኢትዮጵያ ውስጥ በሕይወት የመኖር መብት ጥያቄ ሆኗል።
በተፈጠረው አዲስ ሁኔታ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጥያቄ የሰው ልጆች ሁሉ ጥያቄ ሆኗል።
በአገራችን በሚገኙ የተለያዩ ሃይማኖቶች ምዕመናን መካከል ከዚህ በፊት ከነበረው እጅግ የላቀ መቀራረብ እየታየ መሆኑ እውነት ነው። ቀድሞ የነበረው መከባበር ዛሬ ወደ መደጋገፍ አድጓል።
ለምሳሌ:-
  1. በአዲስ አበባ ከተማ የመለስ ዜናዊ ገዳይ ቡድን በአወሊያ መስጊድ ውስጥ በነበሩት ሙስሊሞች ላይ ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት ባደረሰበት ወቅት ክርስቲያኖች አቅማቸው የቻለውን ያህል የመከላከል እርምጃ ወስደዋል። አብረው ተደብድበዋል፤ ቆስለዋልም።
  2. በአንዋር መስጊድ ተመሳሳይ ዝግጅት በነበረበት ወቅት የሙስሊም ወገኖቹ ድምጽ ጎልቶ እንዲሰማ አጠገቡ ያለው የራጉኤል ቤተክርስቲያ የድምጽ ማጉያውን አጥፍቷል።
  3. በደሴ ከተማ ሙስሊሞች ላደረጉት ሰደቃ ክርስቲያኖች ድንኳን በነፃ ሰጥተዋል፤ እንጀራና ለስላሳ መጠጦችን በማዋጣት ተባብረዋል።
በውጭ አገርም ተመሳሳይ መደጋገፍ እየታየ ነው።
ለምሳሌ፡-
  1. በስደት ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጥያቄ የመብት ጥያቄ መሆኑን በመረዳት ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ከጎናቸው እንዲቆሙ ጥሪ አድርጓል።
  2. ወያኔ በዋልድባ ገዳም ላይ የሚያደርሰውን ጥቃት በመቃወም በሰሜን አሜሪካ እና አውሮፓ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ከክርስቲያን ወገኖቻቸው ጎን ቆመው “ዋልድባ ታሪካዊ ቅርሳችን ነው፤ መደፈር የለበትም” እያሉ ድምፃቸውን አሰምተዋል።
  3. በደቡብ አፍሪቃ የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) ደጋፊዎች በጠሩት ስብሰባ ውስጥ አንድ የፕሮቴስታንት ሃይማኖት መምህር ሙስሊም ኢትዮጵያን ለሚያደርጉት ተጋድሎ አጋርነት ለመግለጽ “ሁላችን በአንድ ቃል ፈጣሪን እናመስግን” በማለት “አላሁ አክበር!” ሲሉ የአዳራሹ ተሰብሳቢ በሙሉ አብሯቸው “አላሁ አክበር” ብሏል።
ይህ በጣም አበረታች ነው። ሆኖም አሁን ለደረስንበት የትግል ደረጃ በቂ አይደለም።
ሙስሊም ወገኖቻችን በጽናት እየታገሉ ነው። በዚህም ምክንያት የጥይት አረር እየዘነበባቸው ነው። ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሙስሊም ወገኖቻችን ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ በርካቶች ቆስለዋል። ሕፃናትና ሴቶች ሳይቀሩ ተድብድበዋል፤ በጅምላ ታፍሰው ታስረዋል።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ የክርስቲያን ኢትዮጵያዊያን ተሳትፎ አሁን ከአለበት ደረጃ በላይ መሆን ይገባዋል። የኢትዮጵያ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ እያቀረበ ያለው ጥያቄ የሙስሊሙ ብቻ አይደለም። የሙስሊም ኢትዮጵያዊያን ጥያቄ በገዛ አገሩ ተከብሮ እንዲኖር የሚፈልግ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ጥያቄ ነው። የሙስሊም ኢትዮጵያዊያን ጥያቄ የሰው ልጆች ሁሉ ጥያቄ ነው።
ክርስቲያን ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ መስጠት ሳይሆን ትግሉን ሊቀላቀሉ ይገባል። የሙስሊም ኢትዮጵያን ትግል የሁላችንም ትግል ነው። የትግሉ ውጤትም የጋራችን ነው። በሰው ልጅነት፣ በኢትዮጵያዊነት አንድ ነን። ሁላችንም ፍትህን፣ ነፃነትን፣ እኩልነት፣ ዲሞክራሲን እንሻለን።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህ፣ ነፃነት፣ እኩልነትና ዲሞክራሲ እንዲኖር የሚፈልግ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ዛሬውኑ የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን ትግል እንዲቀላቀል በይፋ ጥሪ ያደርጋል።
ትግሉ የሁላችን፤ ድሉም የጋራችን ነው።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!!


1 comment:


  1. Fast cash loan offer for you today at just 2% interest rate, both long and short term cash of all amounts and currencies, no collateral required. We give out from a minimum range of 2000 to a maximum of 20 million.We are certified and your privacy is 100% safe with us Apply now for your instant approval and transfer approval process takes just 3 hours. contact us now I'll advise you can contact us

    abdullahibrahimlender@gmail.com
    whatspp Number +918929490461
    Mr Abdullah Ibrahim

    ReplyDelete