Saturday, July 7, 2012

ለእነ አቶ አንድዓለም አራጌ ጥሪ መልሳችን ይህ ነው!

ለእነ አቶ አንድዓለም አራጌ ጥሪ መልሳችን ይህ ነው!

የመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝ በአቶ አንዱዓለም አራጌ መዝገብ ላይ በሃያ አራት ንፁሃን ዜጎች ላይ በርካታ ወንጀሎችን ዘርዝሮ፤ በህገ ወጡ “የፀረ-ሽብር ህግ” ክስ መሥርቶ ሰኔ 20 ቀን 2004ዓ.ም. የጥፋተኝነት ብይን ሰጥቷል።
መለስ ዜናዊ ከፍርድ ቤቱ ቀድሞ ውሳኔውን ተናግሮ ስለነበር የይስሙላ ብይኑ ለብዙዎች አስደናቂ አልሆነም። የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ፍርድ ቤቶችን በተቀናቃኞች ማጥቂያ መሣሪያነት የሚጠቀም መሆኑ፤ ዳኞቹም የአገዛዙን ውሳኔ ከማሳወቅ ያለፈ ሥልጣን የሌላቸው መሆኑ ከኢትዮጵያዊያን አልፎ በውጭ አገራት ታዛቢዎች ሳይቀር የታወቀ ነው። በዚህም ምክንያት ብይኑ በራሱ አዲስ ነገር የለውም። የእለቱን “የችሎት” ውሎ የኢትዮጵያዊያን መነጋገሪያ እንዲሆን ያደረገው ከብይኑ ይልቅ አቶ አንዱዓለም አራጌ የቅጣት ማቅለያ ሃሳብ እንዲያቀርብ የተጠየቀበትን አጋጣሚውን በመጠቀም ያደረገው ንግግር ነው።
አቶ አንዱዓለም “በቅጣት ማቅለያ ሃሳብ” ሰበብ በአገኘው ትንሽ አጋጣሚ ያስተላለፈው መልዕክት ከፍርድ ቤቱ የወራት ድራማ እጅግ በላይ ዋጋ ያለው መልዕክት ነው።

አቶ አንዱዓለም እንዲህ ነበር ያለው
ያሳለፍነው ግማሽ ምዕተ ዓመት የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሰብዓዊ ክብሩና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹ የታገለበት ዘመን ነው። ይሁን እንጂ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹ ባለቤት ለመሆን እስካሁን አልታደለም። እኔም በተፈጠርኩበት በዚህ ዘመን ለራሴ፣ ለልጆቼና ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ዴሞክራሲና ነፃነት እንደሚገባን በማመን አቅሜ በፈቀደው መጠን ታግያለሁ። ይኼን በማድረጌ በማንም ላይ በክፋት አልተነሳሁም። ይኼን በማድረጌ ህግ ጥሼ አላውቅም። ይኼን በማድረጌ በደሃዋ ሃገሬ ጥቅም ላይ አልተነሳሁም። ይሄን በማድረጌ ፈጣሪዬን፣ የኢትዮጵያን ሕዝብንም ሆነ ህሊናዬን የሚያሳዝን አንዳች ነገር ፈፅሜያለሁ ብዬ አላምንም። ፍፁም ሰላም ይሰማኛል። እኔን እዚህ ያቆመኝ የነፃነት ናፍቆት ነው። በኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶችም ፍትህን ለምኜ ስነፈግ ይህ የመጀመሪያዬ አይደለም። ከሳሾቼ እንድጠጣው የሚፈልጉትን የግፍ ፅዋ በፀጋ ከመጠጣት ውጪ ባልፈረፀምኩት ወንጀል ማቅለያ የመጠየቅን አማራጭ ህሊናዬ ስላልተወልኝ አዝናለሁ።
የአቶ አንዱዓለም አራጌ እያንዳንዱ ዓረፍተ ነገር ከፍተኛ ያለ ዋጋ ያለው መልዕክት ነው። በልበ ሙሉነት “ለራሴ፣ ለልጆቼና ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ዴሞክራሲና ነፃነት እንደሚገባን በማመን አቅሜ በፈቀደው መጠን ታግያለሁ” ማለት መቻል መታደል ነው። ለእንዲህ ዓይነቱ ክብር የታደለ ሰው በአፈና ውስጥ ሆኖ እንኳን ውስጣዊ ሰላም አለው። እሱም “ፍጹም ሰላም ይሰማኛል” ነው ያለው።
የአቶ አንዱዓለም መልዕክት የመለስ ዜናዊን ውሳኔ ለማንበብ የተሰሙት ሃሳዊያን ዳኞችን እረፍት የሚነሳ ነገር ነው። በዚህም ምክንያት ነው የመሃል ዳኛው አቶ አንዱዓለምን ለማስቆም የሞከረው። ሆኖም ግን አንዱዓለም ንግግሩን ቀጠለ። “እኔን እዚህ ያቆመኝ የነፃነት ናፍቆት ነው” በማለት የቆመበትን ዓላማ በአንዲት ዓረፍተ ነገር አጠቃሎ አቀረበ። ሃሳዊያኑ ዳኞች ከዚህ በላይ መስማት አልቻሉምና አቶ አንዱዓለምን አስቆሙት። ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና አቶ ናትናኤል ብርሃኑ ደግሞ ተመሳሳይ መግለጫ ይሰጣሉ በሚል ፍርሃት “የቅጣት ማቅለያ” በግልጽ በችሎቱ ውስጥ እንዳያቀርቡ ተከለከሉ። ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ አቶ ናትናኤል ብርሃኑ እና ሌሎችም እድል በማጣታቸው ቢቆጩም መልዕክታቸው በአቶ አንዱዓለም አራጌ አጭር መልዕክት ተጠቃሎ ቀርቧል።
የአቶ አንዱዓለም መልዕክት የተላለፈው ለህሊና ቢሶች የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ዳኞች ቢመስልም በዳኞቹ አስመስሎ የተናገረው ለኢትዮጵያዊያን በሙሉ ነው። የአቶ አንዱዓለም ንግግርም የእሱ ብቻ ሳይሆን በእለቱ የመናገር እድል የተነፈጋቸው የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ሰለባዎች ጭምርም እንደሆነ እንገነዘባለን።
የመልዕክታቸው ፍሬሃሳብ
እኛ ኢፍትሃዊነትን፣ አምባገነንነትን፣ ዘረኝነትን ፊት ለፊት በመጋፈጥ እዚህ ድረስ ደርሰናል። እናንተስ ምን እያደረጋችሁ ነው?
የሚል ነው። መልሳችን ምንድነው?
የኢትዮጵያ ሕዝብ እስከ መቼ ጀግኖቹን ለእስር እየገበረ ይኖራል? ግንባር ቀደም መሪዎቻቸው እየታሰሩባቸው በተቃዋሚ ፓርቲዎች ድክመት እንደምን ማማረር ይቻላል? በየጊዜው አንገታቸውን ብቅ የሚያደርጉ መሪዎቹ እንዲህ እየተቀነደቡ እስከመቼ ይዘለቃል?
ግንቦት 7፡ የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ በአቶ አንዱዓለም አራጌ መዝገብ ላይ በተከሰሱ ዜጎች ላይ የተሰጠውን ብይን ያወግዛል። የገጠመን ጠላት ፍጹም አምባገነንና ዘረኛ ብቻ ሳይሆን ጨካኝም ጭምር በመሆኑ ትግላችንም ጠላታችንን በሚመጥን መጠን መምረርና መጨከን ይገባዋል ብሎ ያምናል። ስለሆነም ወያኔን ለማስወገድ የተገኙ እና ወደፊትም የሚገኙ አማራጮችን ሁሉ መጠቀም ተገቢ ነው ብሎ ያምናል።
ለእነ አቶ አንድዓለም ጥሪ የግንቦት ምላሽ የሚከተለው ነው።
የመለስ ዜናዊ አገዛዝ መወገድ ይኖርበታል። የፍልሚያ ስልትም የሚመርጥልን እሱ አይደለም። በተመቸን መንገድ ሁሉ ተጉዘን አገዛዙን እናስወግዳለን።
በግንቦት 7 እምነት፣ በወያኔ መዳፍ ውስጥ ያሉ ወገኖቻችን በእስር ላይ የሚቆዩበት የስቃይና የመከራ ዘመን የእኛ – ኢትዮጵያዊያን – የመከራና የስቃይ ዘመን ነው።

ኃላፊነቱ ይሰማን። ወያኔን ለማስወገድ ቆርጠን እንነሳ።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

No comments:

Post a Comment