Sunday, July 22, 2012

አዜብ መስፍን ከአገር እንዳትወጣ ታገደች

አዜብ መስፍን ከአገር እንዳትወጣ ታገደች

(ኢ.ኤም.ኤፍ ሪፖርታዥ) የጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊን ድንገተኛ ህመም ተከትሎ፤ ከአገር እንዳትወጣ የታገደች መሆኑ ታውቋል። የመጀመሪያው እግድ የመጣው ከኢትዮጵያ ደህንነት ሃላፊ ጌታቸው አሰፋ ሲሆን፤ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ግን እገዳውን ሌሎች የህወሃት ከፍተኛ ባለስልጣናትም የተቀበሉት ይመስላል።
በተለይም በድንገተኛው የጠቅላይ ሚንስትሩ ህመም በትግራይ አካባቢ ሲሰማ፤ “አዜብ መስፍን ከምግብ ጋር መርዝ ሰጥታው ነው” የሚል ወሬ በሰፊው በአድዋ፣ በመቐለ እና በሌሎች የትግራይ ከተሞች ሲወራ ነበር። ይህም የትግራይ ህዝብ በሴትዮዋ ላይ ያለውን ጥላቻና ጥርጣሬ የሚያሳይ ሲሆን፤ የአዜብ መስፍንን መታገድ አስመልክቶ ህወሃትም ምንም ተቃውሞ አለማሰማቱ ሴትዮዋ በህወሃት አካባቢ የነበራትን ተደማጭነት እያጣች መሆኑን የሚያመላክት ነው።

የደህንነት ሃላፊውን የአቶ ጌታቸው አሰፋን እግድ ተከትሎ፤ ጠቅላይ ሚንስትሩ በውጭ አገር በህክምና ላይ በነበረበት ወቅት ሴትዮዋ ከአገር እንዳትወጣ ተደርጎ፤ በፓርላማው እና በአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ላይ እንድትገኝ የተደረገ መሆኑ የደረሰን መረጃ ያስረዳል። አዜብ መስፍን በተለይ ከነበረከት ስምኦን፣ ከአላሙዲን፣ ከጌታቸው አሰፋ፣ ከስብሃት ነጋ፣ ከአርከበ እቑባይ ጋር በግልጽ የታወቀ ጸብ እና ልዩነት ያላት ሲሆን፤ የሃይል ሚዛን ታግኝበታለች ተብሎ የሚጠበቀው ከህወሃት ጄነራሎች ጋር የነበራት መልካም ግንኙነትም ቀስ በቀስ እየላላ ሊመጣ እንደሚችል ከወዲሁ ግምት እየተሰጠ ነው።
ከጠቅላይ ሚንስትሩ መታመም እና ብሎም መሞት ጋር በተያያዘ ሊመጡ የሚችሉ አወዛጋቢ ጉዳዮች ከወዲሁ እየተነሱ ነው። መለስ ዜናዊም ሆኑ ባለቤታቸው ከአገር ቤት ውጭ በተለያዩ ባንኮች ገንዘብ ማስቀመጣቸው ይታወቃል። ከሁለት አመታት በፊት ባለስልጣናት ገቢያቸውን እንዲያስመዘግቡ አዲስ ህግ ወጥቶ ነበር። በዚህ ወቅት መለስ ዜናዊ ደሞዙ 6ሺህ አራት መቶ ብር መሆኑን አስመዝግቧል። በተዋረድ ሌሎች ሚንስትሮችም ደሞዝ እና ንብረታቸውን ያስመዘገቡ ሲሆን፤ ሴትዮዋ አዜብ መስፍን እና ጥቂት ጄነራሎች ሃብትና ንብረታቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
አሁን ከጠቅላይ ሚንስትሩ መታመም ወይም መሞት በኋላ ግን “አዜብ መስፍን ጉልበተኛ ሆና ትቀጥላለች ወይ? ንብረቷንስ ታስመዘግባለች ወይ” የሚለው አጠያያቂ ሆኖ ይቀጥላል። በተለይም ከ80 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ እንዲደረግ በማዘዝ በሚንልክ ቤተመንግስት ውስጥ ትልቅ ቪላ አሰርታለች። ጠቅላይ ሚንስትሩ ስራ ላይ ካልሆነ ወይም ከሞተ ደግሞ፤ ቤተ መንግስቱን መልቀቅ ይኖርባቸዋል። ከሴትዮዋ አምባገነን ባህሪ አንጻር ግን፤ ቤተ መንግስቱንም ሆነ በቤተመንግስቱ ውስጥ ያሰራችውን ቪላ ለቅቃ መውጣቷ በራሱ አጠራጣሪ ሊሆን ይችላል። በዚያም ተባለ በዚህ ግን ከመለስ ዜናዊ ሞት በኋላ በሴትዮዋ ዙሪያ ሊመጣ የሚችለው ውዝግብ ቀላል ሊመስለን ይችል ይሆናል… ነገር ግን በህወሃት ውስጥ ጭምር፤ ጥርስ የነከሱባትን ሰዎች መብዛት ስናይ የሃይል ሚዛኑ ወደሌላው ወገን ያደላ መሆኑን መታዘብ ይቻላል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአዜብ መስፍን የግል ሹፌር የነበረው ግለሰብ ከአገር ሸሽቶ መውጣቱ ተረጋግጧል።

No comments:

Post a Comment