Sunday, May 26, 2013

የታሰረው ሦስት ትውልድ


ትላንት ግንቦት 16 ቀን 2005 ዓ.ም ከቀኑ 6 ሰዓት ሲል የአውራምባ ልጆች (እኔ፣ አቤል አለማየሁ እና ኤልያስ ገብሩ) ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ቅጥር ግቢ ተገኘን፡- ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙን ለመጠየቅ፡፡ ርዕዮትን ከሰኞ እስከአርብ ለ10 ደቂቃ መጠየቅ ይቻላል፡፡ በዚያች 10 ደቂቃ ከሴቶች ክልል ለጥየቃ የሚወጡት ሁለት እስረኞች ብቻ ናቸው፡፡ ርዕዮት ዓለሙ እና ወ/ሮ እማዋይሽ ዓለሙ፡፡ እናም ታሳሪዎቹ ከውስጥ ወደ መጠየቂያው አጥር መጡ፡፡ በተወሰነ ርቀት ቆመው ጠያቂዮቻቸውን ያነጋግሩ ጀመር፡፡

Photoከርዕዮት ዓለሙ በስተግራ በኩል ፈንጠር ብለው ጠያቂዎቻቸውን የሚያነጋግሩት ወ/ሮ እማዋሽ “ከግንቦት 7 ፓርቲ ጋር በመመሳጠር ሕገ-መንግስታዊውን ሥርዓት ለመናድ” አሲረዋል ከተባሉት የኢህአዴግ ጄኔራሉች ጋር የተከሰሱ ናቸው፡፡ በዚህ ክስ የተነሳ ነው ሚያዝያ 16 ቀን 2001 ዓም የ25 ዓምት እስር የተፈረደባቸው፡፡

እናም ትናንትም የዘወትር ጠያቂዎቻዋው ከፊት ለፊታቸው ቆመዋል፡፡ አንደኛዋ ጠያቂያቸው እማሆይ ናቸው፤ የመነኩሴ ቆብ አድርገዋል፣ ነጠላቸውን እንደነገሩ አጣፍተዋል፣ መቋሚያ ተመርኩዘዋል፡፡ በግምት ዕድሜያቸው ወደ 90 ዓመት ይጠጋል፡፡

 የታሳሪዋ የወ/ሮ እማዋይሽ ወላጅ እናት ናቸው፡፡ ከእሳቸው ጎን “የወርቅ ፍልቃቂ” የምትመስል ለጋ ወጣት ቆማለች፡፡ ናርዶስ ዘሪሁን ትባላለች፡፡ (ፎቶዋን ይመልከቱ፡፡) እማሆይ እና ናርዶስ ያለቅሳሉ፡፡ ታሳሪዋ ወ/ሮ እማዋይሽ እንባቸውን ወደውስጥ እያመቁ እነሱን ያፅናናሉ፡፡፡፡ እናት፣ ልጅ እና የልጅ ልጅ በቃሊቲ ቅጥር ግቢ በዚህ መልኩ ማዶ ለማዶ ቆመው ሲላቀሱ ማየት ልብ ያደማል፡፡ እናም ሃዘናቸውን እያየሁ ለራሴ “እነዚህ ሰዎች የታሰረው ሦስት ትውልድ ተምሳሌት ናቸው” አልኩ፡፡ ( በወቅቱ ያየሁትንና የሰማሁትን ሁሉ በሌላ ቀን “የታሰረው ሦስት ትውልድ” በሚል ርዕስ በዝርዝር ተርከዋለሁ- አሁን ወደ ተነሳሁበት ዋንኛ ጉዳይ ላምራ)

ከላይ እንደነገርኳችሁ የተመደበልን የጥየቃ ደቂቃ ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂያ ያህል ሲቀር የ25 ዓመቷ ፍርደኛ ወ/ሮ እማዋይሽ፣ ለልጃቸው ናርዶስ ሙሉጌታ የጆሮ ጌጥ በስጦታ አበረከቱላት፡፡ እናም “መልካም ልደት!” አሏት፡፡ ናርዶስ ስጦታዋን ተቀብላ እንባዋን እንደጅረት ለቀቀችው፡፡ አ…..ህ!! ከዚህ በኋላ የተሰማኝን ስሜት ለመናገር ቃል ያጥረኛል፡፡ የሆነ ሆኖ ትናንት ግንቦት 16 ቀን 2005 ናርዶስ 19ኛ ዓመት የልደት በዓሏን የምታከብርበት ቀን ነበረ፡፡ እሷ ግን “መልካም ልደት” የማይባልበት ቃሊቲ ናት፤ እያለቀሰች፡፡

እናም ለዚህች ለጋ ወጣት ምንድነው የሚባለው!? መልካም ልደት!?….እን…ጃ!? ከዚህ በኋላ ስንት ልደት ይሆን በዚህ መልኩ የምታከብረው?! አላውቅም! ማንም አያውቅም!…እናም ለዚች ልጅ ልደት ምንድነው!? ወዘተ…. ይኼ ለራሴ ያቀረብኩት ጥያቄ ነው፡፡ ለማንኛውም ወግ ነውና “መልካም ልደት!” ማለት ነው የሚሻለው!!

(በነገራችን ላይ በትናንትናው ዕለት በመብራት መጥፋት ምክንያት ይህንን ማስታወሻ ልፅፍ አልቻልኩም ነበር፡፡ ፎቶዋን ብቻ ነበር በሞባይል ፖስት ያደረኩት፡፡ እናም ፎቶዋን ብቻ አይታችሁ ለናርዲ መልካም ልደት ለተመኛችኋላት የፌስቡክ ሸሪኮቼ ሁሉ በእሷ ስም ታላቅ ምስጋና አቀርባለሁ፡፡) መ – ል – ካ – ም ልደት ናርዲ!!!!

የሚቀጥሉት ዓመታት የደስታ ልደት በዓል የምታከብሪበት ይሆኑልሽ ዘንድ በፅኑ እመኝልሻለሁ!!

No comments:

Post a Comment