Tuesday, March 26, 2013

እኛ ካልረዳን ማን ? አሁን ካልሆነ መቼ ? ከ ሰሜን አሜሪካ የፍኖተ ጋዜጣ ዝግጅትድጋፍ አስተባባሪ ኮሜቴ




አገር ዉስጥ ለበርካታ ወራት ስትታተም የነበረችዉና በሕዝብ ዘንድ ታላቅ ተወዳጅነትን ያተረፈችዉ፣ የፍኖት ጋዜጣ፣  በአገር ዉስጥ መታተም ካቆመች ብዙ ሳምንታት አሳልፋለች። አገር ቤት ያሉ ማተሚያ ቤቶች በሙሉ፣ ከኢሕአዴግ በተሰጣቸው መመሪያ፣  የፍኖት ጋዜጣን ለማስተናገድ ፍቃደኛ አልሆኑም። ኢሕአዴግ «የኢትዮጵያ ህዝብ መስማትና ማንበብ አለበት» ከሚላቸዉ ዜናዎችና ሃተታዎች ዉጭ የተለዩ ሌሎች የፖሊሲ አማራጮች እንዲስተናገዱ አይፈልግም።


መረጃ ኃይል ነዉ። ከዉጭ በቴለቭዥንና በራዲዮ የሚገኙ፣ ከኢሕአዴግ ገለልተኛ የሆኖ ዜናዎች የታፈኑ ናቸዉ። በርካታ ድህረ ገጾች ታግደዋል። በፌስ ቡክ፣ ትዊተር  በመሳሰሉት ሕዝብን ማደራጀት እንዳይቻል፣ የቴሌኮሚኒኬሽን ተቋማትን በመቆጣጠር ሕዝቡ በኢንተርኔት መረጃ እንዳይደርሰዉ ተደርጓል። የሚያሳዝነው የኢንተርኔት አገግልግሎት ተጠቃሚ የሆነው የሕዝባችን ክፍል ከ0.5 በመቶ በታች መሆኑ ነው።
ሕዝብ ካልነቃ፣ ካልተማረ፣ የተሻሉ አማራጮች በፊት ካልቀረቡለት፣ ከፍርሃትና ከተስፋ መቁረጥ እንዲወጣ ካልተደረገና ካልተደራጀ፣ በዉጭ አገር በሚደረግ ትግል ወይንም በዉጭ ኃይሎች ተጽእኖ ብቻ ፣ ለዉጥ ሊመጣ አይችልም። የለዉጥ ባለቤት አገር ዉስጥ የሚኖረው የኢትዮጵያ ሕዝብ እራሱ ነዉ። ይሄንን ሕዝብ ከማደራጀትና ከዚህ ሕዝብ ጋር አብሮ ከመስራት ዉጭ ሌላ አማራጭ አይኖርም።
በአገር ዉስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶ፣ ጋዜጠኞችና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ፣ የኢሕአዴግን ምንነት ጠንቅቀዉ ያውቃሉ። ብዙዎች ታስረዋል። ከሥራቸዉ ተባረዋል። ሕይወታቸዉን  ያጡ ፣ ከመኖሪያ ሰፈራቸውም  የተፈናቀሉ ጥቂቶች አይደሉም።
በአሁኑ ወቅትም ሊታሰሩና ዋጋ ሊከፍሉ እንደሚችሉ እያወቁም፣ ከራሳቸዉ ይልቅ የአገራቸውን ጥቅም አስቀድመዉ፣  ትልቅ ስራ እየሰሩ ያሉ የሚደነቁና አገር ወዳድ የሆኑ ታጋዮች በአገር ቤት አሉን። ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከኢሕአዴግ የተሻለ አማራጭ ለማቅረብ፣ ሕዝቡንም ለመብቱና ለነጻነነቱ እንዲነሳ ለማደራጀት የተቻላቸዉን እያደረጉ ነዉ።  «በማተሚያ ቤት አሳቦ ፍኖት እንዳትታተም ኢሕአዴግ ቢያደርግም፣ ተስፋ አንቆርጥም። ማተሚያ ማሺኑን ገዝተን ለሕዝቡ መረጃ እንዲደርስ እናደርጋለን» ብለዉ በሚያኮራና በሚያበረታታ መልኩ ተነስተዋል። ኢሕአዴግ ዝም እንዲሉ ቢፈልግም፣ «የኢሕአዴግ ዉሳኔ የኛን  አላማ አይገታዉም» በሚል ዝም ላለማለት ወስነዋል።  ትግል፣ የትግል ወኔ ማለት ይሄ ነዉ !!!!!
በዉጭ አገር የምንኖር ኢትዮጵያዉያን በተለያዩ ጊዜያት አስተዋጾዎች ማድረጋችን አይዘነጋም። ነገር ግን  የጠበቅነዉን ዉጤት ስላላገኘን ብዙዎቻችን  ተስፋ ቆርጠን ሊሆን ይችላል። ነገር ግን አንድ ማየት ያለብን ትልቅ ቁም ነገር  አለ። እኛ አልታሰርንም። እኛ አልተገደልንም። እኛ ከስራችን አልተባረርንም። እኛ ከቤታችን አልተፈናቀልንም። አገር  ቤት ያሉ ወገኖቻችን ብዙ መከራ እየደረሰባቸው፣  ተስፋ ካልቆረጡና ካልሸሹ፣ ጋዜጣችን ባይታተምም ማተሚያ ማሽኑን ገዝተን እንቀጥላለን ካሉ ፣ እኛ እንዴት ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን ? እነርሱ ሕይወታቸው ሲያቀርቡ እኛ እንዴት በገንዘብና በሞራል ትንሽ ድጋፍ መስጠት ያቅተናል? እኛ ካልረዳን ማን ? አሁን ካልሆነ መቼ ?
መዉደቅ መነሳት አለ። መሳሳት አለ። ከዚህ በፊት ወድቀናልና «አንነሳም» ማለት የለብንም። የትላንትናዉ ዉድቀታችንና ጠባሳችን  ወደፊት እንዳንገሰግስ ሊያስረን አየገባም። ከወደቅንበት ተነስተን፣  የምንችል እየሮጥን፣ የማንችል እያነከስን ወደፊት መሄድ ይኖርብናል። ተኝተንና ወድቀን ግን መቅረት የለብንም።
እንግዲህ የትግሉ አካል ለመሆን፣  ፍኖት ስራዋን እንድትቀጥልና ሕዝብ መረጃ እንዲያገኝ የምንፈልግ ካለን፣   በሚከትለዉ ሊንክ እንዴት መርዳት እንደምንችል መረጃዎችን  እናገኛለን።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር !

No comments:

Post a Comment