Wednesday, December 19, 2012

ሳይንስና የኅልፈተ- ዓለም ትንቢቶች፣


ሳይንስ/ቴክኒክ

ሳይንስና የኅልፈተ- ዓለም ትንቢቶች፣

በዚህ ቀን ብሎ! ቀን ቆርጦ ፣ ዘመን ፣ ቀንና ሰዓት ጠቅሶ--- ፕላኔታችን ትጠፋለች! ብሎ ለመናገር ትክክለኛ መረጃ ሊኖር ይገባል። በየዘመናቱ ስለምድር መጥፋት ብዙ ተተንብዮአል፤ ግን እንደሚባለው ዓይነት የዓለምን ክፍሎች የሚያዳርስ ብርቱ የሚባል አደጋም
ሆነ አጠቃላይ ጥፋት አላጋጠመም(የበረዶ ዘመን፤ እንዲሁም ከ 65 ሚሊዮን ዓመት ገደማ በፊት ዳይኖሰርስ የጠፉበት ስባሪ ኮከብ በምድራችን ላይ አደረሰ ከሚባለው ጥፋት በስተቀር!)። የአሁኑን ፣ ማለትም የማያዎችን ትንቢት ምንድን ነው የተለየ የሚያደርገው? በአሁኑ ማዕከላዊ አሜሪካና ሜክሲኮ ይኖሩ የነበሩ የጥንት የአካባቢው ነባር ተወላጆች (ማያስ)አሁንም ዘሮቻቸው ፣ በተጠቀሰው የዓለም ክፍል ይገኛሉ፤ በዑደታዊ የዘመን አቆጣጠራቸው «ባክቱን» ፤ ዓለም የፊታችን ዓርብ ፤ ታኅሳስ 12 ቀን 2005 ዓ ም (21 12 2012)ትጠፋለች የሚል ትንቢት ስለመተንበያቸው ብዙ ሲነገርና በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን ሲስተጋባ መቆየቱ የታወቀ ነው። አንድ ባክቱን = 20 ካቱን ነው። አንድ ካቱን 7,200 ቀናት አሉት። 20 ው ካቱን ወይም አንዱ ባክቱን 144,000 ቀናት ወይም 394,26 ዓመታት አሉት፣ ወደ 400 ዓመት የሚጠጋ ነው ማለት ነው።
የማያዎች ዘመን አቆጣጠር በ 300 ዓመተ ዓለም ገደማ ሲጀመር 3114 ዓመተ- ዓለምን አንድ ብሎ መነሻ እንዳደረገ ይነገራል ። ያኔ የዘመን ቆጠራው አንድ ተብሎ ከመጀመሩ በፊት በዋዜማው፤ የማያዎች አፈ ታሪክ፣ ዓለም የጥፋት ውሃ ደርሶባት ነበረ ይላል። ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያወሳው በኖኅ ዘመን ከደረሰው የጥፋት ውሃ ጋር አንድ ይሁን የተለየ በግልፅ የተጠቀሰ ነገር የለም። እንደ ጥንታውያኑ ማያዎች ትንቢት፤ የከነገ በስቲያው ጥፋትም በተመሳሳይ መልኩ በውሃ አማካኝነት ነው የሚከናወነው! በሌላም በኩል ጥፋቱን የሚያስከትለው፤ አንድ ምኅዋር የሳተ ፕላኔት ፤ ከኛዋ ፕላኔት ጋር በመላተም ይሆናል የሚሉም አልታጡም። ታዲያ 13ኛው «ባክቱን » ማለት ለ 13 ጊዜ ተጀምሮ 144,000 ቀናት ወይም 394,26 ዓመታት የሚያከትሙበት ዕለት የሚውለው እንዳልነው ዓርብ ታኅሳስ 12 ቀን 2005 ነው። 14ኛው ባክቱን ማለት ለ ቀጣዮቹ 144 ዓመታት አዲስ የቀን አቆጣጠር ዙር ሀ ተብሎ የሚጀመረው ቅዳሜ ታኅሳስ 13 ቀን ነው ማለት ነው። 19 ኛው ባክቱን ካበቃ በኋላ ደግሞ 20 ባክቱን መባሉ ቀርቶ 0 ባክቱን ይሆናል ። በዚህም ፣ የቀን አቆጣጠሩ ፣ አንድ ዑደት ይደፍንና እንደገና አንድ ተብሎ ይጀመራል ማለት ነው። ባጭሩ እንግዲህ የማያዎች የቀን መቁጠሪያ ይህን ነው የሚመስለው።


ታዲያ ፤ በማያዎች 13ኛ ባክቱን መደምደሚያ ላይ ፤ ከነገ በስቲያ መሆኑ ነው፤ ዓለም ትጠፋለች የተባለበት ትንቢት መነጋገሪያ ሆኗል ። እኛም ፣ ሳይንስ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚለውን ይዘን ቀርበናል።
በየዘመናቱ ሰዎች ለእንዲህ ዓይነቱ የጥፋት ትንቢት ትልቅ ግምት የሰጡበት ሁኔታ አለ። ሳይንስና ሥነ ቴክኒክ በተስፋፉበት በአሁኑ ዘመን ፤ በተለይ ባለፉት 40 እና 50 ዓመታት ዓለም ትጠፋለች በሚባልበት ትንቢት የሚያምኑት ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣት በጣም ነው የሚያስገርመው! ምክንያቱ ምን ይሆን?
ታሪክ ን መለስ ብለን ስንዳስስ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ስለመሬት መጥፋት የሚያወሱ ትንቢቶች መኖራቸውን እንገነዘባለን። ግን አንዱም አልያዘም ።
የቅርብ ጊዜዎቹን ትንቢቶችና ውጤታቸውን እናስታውስ።
David Wilkerson የተባሉ በኒው ዮርክ ከተማ የ «ታይምስ እስኩየር » ቤተክርስቲያን ሰባኪ ፤ በአሸባሪዎች ሳይሆን በእግዚአብሔር የሚመጣ መሬትን የሚያጥለቀልቅ መቅሠፍት ይደርሳል ሲሉ ከ 3 ዓመት ከ 10 ወር ገደማ በፊት አስጠንቅቀው ነበር። እርሳቸው ያሉት መቅሠፍት፣ ኒው ዮርክን ብቻ ሳይሆን፤ ንው ጀርሲንና ኮኔክትከትን እንደሚጨምርም ነበረ ያኔ የተናገሩት። በያመቱ በተደጋጋሚ ከውቅያኖስ የሚነሣ ማዕበል እንደሚያጠቃት በየጊዜው ለሚነገርላት ዩናይትድ እስቴትስ ፤ የሰባኪውን ማስጠንቀቂያ ትንቢት ብሎ መውሰድ ያስቸግራል ። እንደሚታወሰው ባለፈው ጥቅምት በዩናይትድ እስቴትስ ምስራቃዊ የጠረፍ ግዛቶችና ኒውዮርክ «ሣንዲ »



የሚል ሥያሜ የተሰጣት ማዕበል ቢያንስ ለ 30 ሰዎች ህልፈተ ህይወትና ለ 65,6 ቢሊዮን ዶላር ያህል የንብረት ኪሣራ ሰበብ መሆኗ አይታበልም። በተመሳሳይ ሁኔታ ጥፋት እንደሚከተል ያስጠነቀቁ ሌሎች ሰባክያንም ነበሩ። በዓለም ዙሪያ በተለያዩ አካባቢዎች፤ የምድር ነውጥ፤ እሳተ ገሞራ፣ የጎርፍ ማጥለቅለቅ ፤ በውቅያኖስ ወለል በሚፈጠር የምድር ነውጥ ሳቢያ የሚፈጠር ብርቱ የውቅያኖስ ማዕበል(ሱናሚ )በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት መቅጠፋቸውን ባለፉት 50 ዓመታት ገደማ የተስተዋለና የተመዘገበ ሐቅ ነው። በፕላኔታችን የሚገኘውን ህይወት ያለውን ነገር ሁሉ የሚያጠፋ አደጋ ስለመከሠቱ ግን ፣ ሳይንስ ፣ የበረዶ ዘመን ስለሚባለው ፤ እንዲሁም ዳይኖሰርስ የተባሉት ዐራዊት ፤ ከ 65 ሚሊዮን ዓመታት ገደማ በፊት ፤ ከምድራችን ጋር በተላተመ ስባሪ ኮከብ ሳቢያ ስለመጥፋታቸው ከሚያወሳው ሌላ በፕላኔታችን ላይ ብርቱ ጥፋት አልደረሰም። ታዲያ ፍርሃቱ ከምን የመጣ ነው?
የጥፋት ትንቢት አማኞችን ጉዳይ በተመለከተ ምርምር ያደረጉት ፣ በሞንትሪአል ፤ ካናዳ ፣ ኮንኮርዲያ ዩንቨርስቲ ፕሮፌሰር ሎሬንሶ ዲቶማሶ፤
«መፍትኄ የሚገኝላቸው ያልመሰሉ ችግሮች አለቅጥ ተንዛዝተዋል። እንደ ሰዎች፤ ለነዚህ ችግሮች መፍትኄ ማግኘት አንችልም ከሚል የሐሳብ ድምዳሜ ስንደርስ ፣ ለሌላ መፍትኄ ፈላጊ እናስረክባለን። በመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት እግዚአብሔር ነው ለከባዶቹ ችግሮች መፍትኄ የሚሰጠው። ድቀት ፤ ጥፋት፣ እንደመፍትኄ መድርሱ አስፈላጊ ነው የሚሉ ሌሎችም አሉ» ሲሉ ተናግረዋል።
በምድራችን የሚገኙ ህይወት ያላቸውን ፍጡራን ሊያጠፉ የሚችሉ አደጋዎች ወይም መንስዔዎች ምንድን ናቸው?




--አንደኛ ፣ ፕላኔታችንና በውስጧየሚገኙ ህይወት ያላቸውን ነገሮች ሁሉ በአንድ ጊዜ ሊያጠፋ የሚችል የተፈጥሮ አደጋ ፣ እስካሁን በፍጥረተ ዓለም እምብዛም ተመርምሮ ምሥጢሩ ያልተደረሰበት ሥፍር ቁጥር የሌላቸውን ከዋክብትና ፕላኔቶች ባንዴ መሰልቀጥ ይችላል እየተባለ የሚነገርለት ጥቁር ጉድጓድ የሚሰኘው ኃይል ነው። ይህ አደጋ ሊያጋጥም ይችላል ቢባል እንኳ ከዐሠርተ- ዓመታት በፊት ምልክቱን ማውቅ እንደማያዳግት ነው የሥነ ፈለክ ጠበብት የሚናገሩት።

--የስባሪ ኮክብ ከምድራችን ጋር መላተም--ከ 65 ሚሊዮን ዓመት በፊት 10 ኪሎሜትር ያህል ስፋት የነበረው ስባሪ ኮከብ ከምድራችን ጋር ሲጋጭ የተነሣው አቧራ፣ 
ከባቢ አየርንበመሸፈን መሬት ድቅድቅ ጨለማ እንዲውጣትና በብርቱ ቅዝቃዜ እንድትጠቃ ማድረጉ የሚወሳ ነባቤ ቃል ነው።
ሌላው የማያወላዳው የጥፋት መንገድ የአቶም ጦርነት ሊሆን ይችላል ፤ የዛሬው ዘመንም ሆነ የወደፊት የፓላኔታችን ኑዋሪዎች ለቀጣይ ትውልድ ፍጹም ደንታቢስ በመሆን ያን ዓይነት የእብደት እርምጃ ይወስዳሉ ተብሎ አይታሰብም። አደገኛነቱ ግን የሚያጠራጥር አይደለም።

እጅግ ኃይለኛ እሳተ ገሞራ ፤ የምድር ነውጥ፤ የጎርፍ ማጥለቅለቅ፤ በዓለም ዙሪያ የኃይለኛ ሙቀትና ቅዝቃዜ መዛመት ፤ እነዚህና የመሳሰሉትም የሚያደርሱት ጥፋት በቀላሉ የሚገመት አይሆንም። ተዛማች ኃይለኛ ተቅማጥ ፤
ኃይለኛ ጉንፋን ትኩሳት፤ የተለያዩ በሽታዎችን መከላከያ መድኃኒቶች የማዳን ኃይላቸው ዋጋ ማጣት---ይህም ለእልቂት ሰበብ ሊሆን ይችላል።



ሰው ሠራሽ የሥነ ቴክኒክ ውጤቶች ፣ ለምሳሌ ግዙፍ ኮምፒዩተሮችም በመሣከር ጦርነት እንዲቀሰቀስ ሊያደርጉና ያልታሰበ ዕልቂትም ሆነ ጥፋት ሊደርስ የሚችልበት አደጋም አለ።

የፀሐይን አደገኛ ጨረር የሚከላከሉ የምድር ዋልታዎች መግነጢሳዊ ቀጣናዎችተግባር መሣከርም እጅግ አሠቃቂ ዕልቂት ሊያስከትል እንደሚችል ነው የሚነገረው።

ሌላው እና ዋናው የህልፈተ ዓለም መንስዔ ሊሆን የሚችለው የፀሐይ ሙቀትና ብርሃን ሰጪ ማገዶዋ ተቃጥሎ ሲያልቅ ይሆናል። ይህ ግን ገና ከ 4 ወይም ከ 6 ቢሊዮን ዓመት በፊት ሊከሠት አይችልም ነው የሚባለው።
የአሁኑ ዘመን ሰዎች የሚያስፈራም የማያስፈራም በመሳሳሉ ጉዳዮች ይጨነቃሉ።

እንዲያው ከአንድ ሺ ዓመት በኋላ በዝች ፕላኔት ላይ የሚገኙ ሰዎች እጅግ የሚያስፈራቸው የዕልቂት አደጋ ምን ይሆን??


የፊታችን ዓርብ በማያዎች ትንቢት መሠረት ኅልፈተ ዓለም ያጋጥማል ቢባልም፤ የዛሬው ዘመን ማያዎች ተጨባጩን የፕላኔታችን ችግር ያወሳሉ እንጂ፣ ዓለም ትጠፋለች ብለው የሚጨነቁ አይደሉም። በደቡባዊው ሜክሲኮ የማያዎች ክፍለ ሀገር አንድ አነስተኛ ማሣ ያላቸው ማኑኤል አንጉሎ የተባሉ አርሶ አደር እንዲህ ብለዋል።
«በቀውስ ላይ ነው የምንገኘው። እግዚአብሔርም ሰዎችን በአየር ንብረት መዛባት እየቀጣ ነው። ዝናሙም ወቅቱን ጠብቆ አይመጣም።»

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሰ

No comments:

Post a Comment