Sunday, July 14, 2013

ለምን እኔ? እኔ ማነኝ?“አንተ ማነህ?

 
 


ይህን አነስተኛ ሰነድ የተወሰደው ከ220 ገጾች በላይ ርዝማኔ ካለው ‪#‎የግንቦት7ህዝባዊሃይል‬ የፖለቲካ ስልጠና ሰነድ ነው።
የፖለቲካ ስልጠና
ምእራፍ 1- እኔ

የፖለቲካ ሥልጠና ትምህርታችን የሚጀምረው እኔ በሚለው ርዕስ ነው። ለምን ይህ ርዕስ ከሁሉም ርዕሶች ቀደመ? በዚህ ርዕስ ሥር ምን ጉዳዮች እናነሳለን? በመጨረሻም የዚህን ርዕስ ወይይት ስንጨርስ ምን መጨበጥ ወይም ማግኘት ይቻላል ብለን እናምናለን? የሚቀጥለው

1. ለምን እኔ በሚለው ርዕስ ጀመርን?

መልሱ ቀላል ነው። ሁላችንም ወደ ግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል ስንመጣ በግላችን ነው የመጣነው። ከሌሎች ጓደኞቻችን ጋር ብንመጣም ሕዝባዊ ኃይሉን እንቀላቀል የሚለውን ውሳኔ የወሰንነው እያንዳንዳችን በተናጠል ነው። ብዙዎቻችን ከዚህ በፊት አንተዋወቅም። የመጣነው እያንዳንዳችን ከሌላው ጋር ሆነን፣ ድርጅት ፈጥረን፣ ወያኔን ተዋግተን እናስወግዳለን ብለን አስበን ነው። ከተሰባሰብን በኋላ ከተናጠል ወደ ብዙሃን ተቀይረናል። ከእኔ እኛ ሆነናል። የእኛነታችን መሠረት ግን እኔ ነው። የእኛነታችን መነሻ እኔ ሆኖ መድረሻችን ደግሞ እኛ ሆኗል። መነሻውን የማያውቅ መድረሻውን አያውቅም ይባላል። እኔን ሳናውቅ እኛን ማወቅና እኛን መሆን አይቻልም። በመሆኑም እኔ ማነኝ የሚለውን ጥያቄ በቅድሚያ በሚገባ ለራሴ መመለስ መቻል ይኖርብኛል።
 
ከሌሎቹ ጓዶቼ የሚቀርብልኝ አንተ ማነህ የሚል ጥያቄ በሚገባ መመለስ የምችለው ስለራሴ ከሚኖረኝ ጥልቅ እውቀት በመነሳት ብቻ ነው። እውን ስንቶቻችን ነን እራሳችን በደንብ የምናውቅ? እኔ ማነኝ ለሚለው ጥያቄ የተሟላ መልስ ለመስጠት ትልቅ ድፍረትና ከራስ ጋር መፋጠጥን ይጠይቃል። ጀግንነትን ይጠይቃል። ከራስ ስሜት፣ ዝንባሌና ፍላጎት ጋር መሟገት ያስፈልጋል። የእኔ ማነኝ ለሚለው ጥያቄ በሚገባ መልስ ስሰጥ ነው ነገ በጦር ሜዳ ጓዴን ጥዬ እንደማልሸሽ፣ ወንድሜን በሰላሳ ሽልንግ እንደማልሸጥ እርግጠኛ የምሆነው። ወያኔ እንዳደረገው ነፃ አወጣዋለሁ የምለውን ሕዝብ መልሼ ረጋጭ መሆን እንደማልችል የማውቀው። ዘራፊ፣ ገፋፊ፣ አስገድዶደፋሪ እንደማልሆን እርግጠኛ መሆን የምችለው።
 
 ሰለ ሀገሬ ስለወገኔ መዋረድ የማነበንባቸውን ቃላት፣ ጉልበቱ እድሉ ስልጣኑ ሲኖረኝ ወደ በጎ ተግባራት እንደምቀይራቸው እርግጠኛ የምሆነው ራሴን በሚገባ ሳውቅ ነው። ጽናት ኖሮኝ የምዘልቅ፣ ምንም ፈተናና ችግር ወያኔን ከመደምሰስ ሊያስቆመኝ እንደማይችል እርግጠኛ የምሆነው እራሴን በሚገባ ሳውቅ ብቻ ነው:: ለጓዴ፣ ለድርጅቴ ለሃገሬ ሰዎችና ለሃገሬ የገባሁትን ቃል የማላጥፍ እንደሆነ እርግጠኛ የምሆነው እኔ ማነኝ ለሚለው ጥያቄ አጥጋቢ መልስ ስሰጥ ነው።

እኔ ማነኝ የሚለውን ጥያቄ በሚገባ ለራሴ ስመልስ ከጓዶቼ የሚቀርብልኝን አንተ ማነህ የሚል ጥያቄ በቀላሉና በእርግጠኛነት መመለስ እችላለሁ። እኔ፣ የእኛ የግንቦት 7 ሕዝባዊ አባላት ስብስብና ድርጅት፣ ከዛም አልፎ የማኅበረሰባችንና የሀገራችን የመሠረት ድንጋይ ነው። የመሠረት ድንጋይ ብቻ አይደለም። ድርጅታችንን፣ ማኅበረሰባችንና ሀገራችንን የምንገነባበት እያንዳንዱ ጡብ እኔ ነው። እኔ በደንብ ካልተገነባ፣ እኔ በደንብ ካልታነጸ፣ እኔ ነካ ሲያደርጉት የሚፈርስ፣ እፍ ሲሉት ብን የሚል ከሆነ፣ እኔ የሚያዝ የሚጨበጥ የሌለው ሙልጭልጭ፣ እኔ መርህ- የለሽ ልክስክስ፣ አከርካሪ የለሽ ልምጥምጥ ከሆነ እኛም የለንም። ድርጅት አይኖርም። ማኅበረሰብ መማቀቁ፣ ሀገር መውደሙ አይቀርም።

እንደ ወያኔ ድርጅት በሚያጭበረብሩ መሪዎችና ተከታዮች የተገነባ ድርጅት በለስ ቀንቶት ወያኔን ቢያስወግድ የሚፈጥረው ሀገራዊና መንግሥታዊ ሥርዓት የአጭበርባሪዎች ይሆናል። አድሎን፣ የድርጅትን ንብረት እንደራስ አድርጎ አለማየትን፣ ራስ ማስቀደምን፣ መስገብገብን፣ ወታደራዊ ፖሊስ ወይ ጓዶቼ አያዩኝም በሚል በጋራ ያጸደቁትን ሕግ ሥርዓትና ደንብ የሚጥሱ፣ ለጓዶቻቸው ደህንነትና ጤንነት የማይጨነቁ፣ እርስ በርስ የማይፋቀሩ፣ የግል ድሎትንና ምቾትን ብቻ ማሰላሰልን ሥራዬ ብለው የያዙ አባላት የተሰባሰቡበት ድርጅት ታግሎ አታጋይ መሆን አይችልም። እንደ ድርጅትም መዝለቅ አይችልም። ነጻ ወጥቶ ሌላውን ነጻ ማውጣት አይችልም። በአንድ ተአምር ወያኔን ማስወገድ ቢሳካለት ከወያኔ በላይሕዝብ አስመርሮ ወያኔ ማረኝ የሚል ዘመን እንዲመጣ ማድረጉ አይቀርም። በሀገራችን ታሪክ የሆነው ይህ ነው። ደርግን ያየ ሃይለስላሴ ማረኝ አለ።
 
 ወያኔን ያየ ደርግ ማረኝ አለ። እኛን ያየ ወያኔ ማረኝ የሚልበትን ሁኔታ ልንፈጥር አይደለም ትግል ውስጥ የገባነው። እኛ ትግል ውስጥ የገባነው መንግሥት ተቀይሮ መንግሥት በመጣ ቁጥር ካለፈው ሥርዓት አዲሱ እየባሰበት የሕዝብ ስቃይ የረዘመበትን የታሪክ ጉዞ ለመቅጨት ነው። እያንዳንዳችን ወደ ትግል የገባነው የሕዝብ እሮሮና ስቃይን ለአንዴና ለመጨረሻው እልባት ወይም መቋጫ ልናበጅለት ነው። ይህ ማድረግ የምንችለው በምንገነባው ድርጅት አማካይነት ነው። የምንገነባው ድርጅት የሚሰራው ከሲሚንቶና ከአሸዋ ወይም ከሌሎች ቁሳቁሶች አይደለም። በሰው ነው። በእኔ ነው። ሰው እንደሸክላ እንደ ብሎኬት ከአሸዋና ከሲሚንቶ የሚሰራ ወይም እንደ እንስሳ የምናራባው ፍጥረት አይደለም።ሰውን ሌላው ሰው አይሰራውም።
 
ሰው ራሱን በራሱ ብቻ የሚሰራ ፍጥረት ነው። እኔ ፈቃደኛ ካልሆንኩ፣ ለመማር ዝግጁ ካልሆንኩ ሌላው ሰው ላስተምርህ፣ ልምከርህ ቢለኝ ዋጋ የለውም።ዛሬ እኔነታችንን ወደፊት ለማምጣት ለምንፈልገው ሀገራዊና ማኅበረሰባዊ ለውጥ እንዲመች አድርገን በሚገባ እዚሁ ካላነጽነው መጨረሻችን አሳፋሪ ውድቀት ነው። የሀገር እጣ፣ የ90 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን እጣ የሚወሰነው እዚህ እኛ መሃል እያንዳንዳችን በምንላበሰው ስብእና፣ በሚኖረን ሰብአዊ ሥነሥርዓትና ጥብቅነት፣ በምንገነባው የአብሮነትና የአንድነት ስሜት፣ በምንሸምተው እውቀትና ክህሎት ላይ ተመስረቶ ነው። እባብ ከሆነን የርግብ እንቁላል አንጥልም። የእባብ ፍልፈሎች እንጂ። ለዚህ ነው ከማናቸውም ጉዳዮች በላይ በግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል ውስጥ እኔ ማነኝ ለሚለው ጥያቄ ቅድሚያ የሰጠነው። እኔ ማነኝ ወይም አንተ ማነህ ለሚለው ጥያቄ በጣም ቀላል ከሆኑ ነገሮች ተነስተን መልስ መስጠት እንችላለን። የእኔ ማነኝ ጥያቄ ምላሽ ግን እንደምናስበው ቀላል እንዳልሆነ ቀጥለን እንመለከታለን።
2. እኔ ማነኝ
“አንተ ማነህ?
“እኔ?”
“አወን፣ አንተ”
“እኔማ ከበደ አበበ ነኝ፣ እንደ ሰው በማልቆጠርበት ኢትዮጵያ በምትባል ሀገር የምኖር ሰው ነኝ”
“ሰው መሆንክን አውቃለሁ። እሱ ምን ችግር አለው። ስምም የሁላችንም ነው። ሃገርም እንደዛው። ከዚህ ውጭ ሌላ ነገር ስለራስህ ንገረኝ።”
“እንደምታየኝ ወጣት ኢትዮጵያዊ ነኝ። እድሜዬ 30 አመት ነው። የተወለድኩት ጎንደር፣ አዲስ ዘመን ነው። እስከ 12ኝ ክፍል ተምሬአለሁ። በውትድርና ሙያ ሰርቻለሁ። 3 ወንድሞች 2 እህቶች አሉኝ። እኔ የመጨረሻው ልጅ ነኝ። የመጀመሪያው ወንድሜ ታላቃችን አዲስ አበባ ውስጥ በምርጫ 97 ወቅት በወያኔ ተገድሏል። ሁለቱ እህቶቼ በሃገራቸው ስራ አጥተው አረብ ሀገር ሥራ ብለው ሄደዋል። እናቴ በውንድሜ ሞት ሃዘን የተነሳ ብዙም ሳትቆይ አርፋላች። አባቴ ነጋዴ ነው። በሕይወት አለ። ወያኔ ከምርጫ 97 በኋላ ተቃዋሚ ትደግፋለህ ብሎ አሰረኝ። ከዛም ከሠራዊቱ ተባረሃል ብሎ ፈታኝ። መጀመሪያውኑ የወያኔ ወታደር መሆን አልነበረብኝም። በሠራዊቱ ውስጥ ያየሁት የዘር አድሎና መጠቃቀም ቆሽቴን ያበግነው ነበር። የከፍተኛ መኮንኖቹ እጅግ የሚገርም በዘር ላይ የተመሰረተ የዘረፋና የቅንጦት ህይወትና የተራው ወታደር ሬት ሬት የሚል ህይወት አንገሽግሾኝ ነበር። መባረሩን በደስታ ነው የተቀበልኩት። ችግሩ ሌላ ሥራ ማግኘት አልቻኩም። በመንግሥት መስሪያ ቤት እንዳልቀጠር በጸረ_መንግሥትነት የሚፈርጅ ደብዳቤ ሰጥተው ነው ከሰራዊቱ ያባረሩኝ። ያንን ደብዳቤ እያየ ማንም የሚቀጥረኝ ጠፋ። በግል ሥራ እዛም እዚህም ሁሉን ነገር ሞከርኩት። ነገር ግን የኑሮ ውድነቱ፣ መተንፈሻ የነሳኝ የሰላዩ ብዛትና አፈናው፣ የወንድሜና የናቴ ደም መና ሆኖ መቅረቱ፣ በአረብ ሃገር በእህቶቼ ላይ የሚደርሰው ውርደትና ስቃይ፣ ወያኔዎች ሲፋፉ እኔ እንደ ስልክ እንጨት መድረቄ ሌላውም ተደራርቦ ወያኔን መታገልአለብኝ ወደሚል መደምደሚያ አደረሰኝ። የግንቦት7 ሕዝባዊ ኃይል መቋቋሙን ሰማሁ። መጣሁ። ተቀላቀልኩ።
 
የግንቦት 7ሕዝባዊ ኃይል አባል ነኝ”

ከዚህ በላይ እንደተመለከትነው እኔ ማነኝ ወይም አንተ ማነህ የሚለው ጥያቄ በዚህ መልኩ ሊመለስ ይችላል። ይህ ምላሽ ግን ሁላችንም በየግላችን እንደማንነታችን የምንመልሰው ምላሽ ነው። ይህን አይነት ምላሽ ለመስጠት ሁላችንም ብዙ አይቸግረንም። ሁላችንም በየግላችን ስለራሳችን ታሪክ በቀላሉ የምናየው ጭብጥ ነው። ስማችን፣ የተወለድንበት ቦታ፣ እድሜያችን ወዘተ አይቀየርም። ስለወያኔም ሥርዓት የምንናገረው ጭብጥ እንዲሁ ለሁላችንም አንድ ነው። በወያኔ የደረሰብን በደል ይለያይ እንጂ ሁላችንም በደል ደርሶብናል። የምሬታችን ደረጃ ይለያይ እንጂ ሁላችንም መሮናል። ይህ ምሬት ሁላችንንም ወያኔን እንድንታገለው ገፍቶን በግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል ውስጥ አሰባስቦናል። ወደ ግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል ስንመጣ ደረቅ ስማችን፣ የግልና የቤተሰብ ታሪካችንን፣ የግል ብሶታችንን ብቻ ግን ይዘን አልመጣንም። ቀጥለን እንደምንመለከተው ብዙ ነገር ይዘን መጥተናል።
እኔ ማነኝ?

ወደ ግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል ስመጣ ምን ይዤ መጣሁ? ስሜን ብቻ ነውን? በወያኔ ላይ ያለኝ ምሬትና ጥላቻ ብቻ ነውን? በደል የወለደው ምሬትንና መንገፍገፍ ብቻ ነውን? መንገፍገፍ የወለደው እልህና ቁጭት ብቻ ነውን? እነዚህ ብቻ አይደሉም። ሌሎችም ነገሮች ይዤ መጥቻለሁ።እያንዳንዳችን የተለያዩ ሙያዎቻችንን ይዘን መጥተናል። የወታደራዊ፣ የሂሳብ ሠራተኛነት፣ የጋዜጠኛነት፣ የሃኪምነት፣ የግንበኛነት፣ የገበሬነትና የአስተማሪነት ወዘተ የመሳሰሉትን ሙያዎች ይዘን መጥተናል። ግን እነዚህን ብቻ ነውን ይዘን የመጣነው? የለበስኩትን ልብስ ብቻ ነው ወይስ መቀየሪያ ጭምር፣ ገንዘብ፣ መሣሪያ፣ ሞባይል፣ መጽሃፍ ይዤ መጥቻለሁን? በሽታ፣ ህመምና ቁስል ይዤ መጥቻለሁን? የሲጋራ፣ የመጠጥ፣ የጫት ሱስ ይዜ መጥቻለሁን? ሌላም ጥያቄ ማንሳት ይቻላል።ከዚህ በላይ የተጠቀሱት እኔ ወደ ግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል ይዣቸው የመጣኋቸው ወይም ላመጣቸው የሚችሉ ነገሮች ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህ ነገሮች የተለያዩ ጥቅምና ጉዳት አላቸው። ስሜ ታሪኬ ማንም አይጎዳም። ሙያዬ ይዤ የመጣሁት ንብረት ገንዘብ ወዘተ የኃይሉን አባላትና ድርጅታችንን ይጠቅማል። በሽታ፣ ህመም ቁስል ይዤ ከመጣሁ ቆራጥነቱና ጽናቱ እስካለኝ ድረስ ጤናዬንና አቅሜን የሚመጥን ተግባር እያከናወንኩ ለትግሉ የድርሻየን አበረክታለሁ። ከነህመሜ የጓዶቼ መመኪያ መሆን እችላለሁ። ይዤ የመጣሁት ሱስ ካለ ግን ምንም ጠቀሜታ የለውም። በዚህ ሱስ የተነሳ እራሴን እጎዳለሁ። ጓዶቼን እጎዳለሁ።
 
 የሱስ ምርኮኛ መሆን ሱስ ለማርካት ሲባል የማያመጣብኝ ፈተና አይኖርም።ሱስ አላስፈላጊ የደህንነት አደጋ ያለበት ሁኔታ ውስጥ ይጨምረኛል። ሱስ ልመናን ውርደት ያስከትላል። ሱስ የድርጅትን የአደራን ገንዘብና ንብረት ማባከንንና ሌባ መባልን ያስከትላል። ሱሱ ምሱን ካላገኘ ማንቀላፋት፣ መንገላጀጅ፣ ትእግስት የሌለን፣ የምንነጫነጭ፣ የምንቀዠቀዠ ወይንም የምንደበት ያደርገናል። ሱስ ሰው እራሱ ጥሮ ግሮ ወይም ሌሎች ጓዶቹ ጥረው ግረው ላባቸውን አንቆርቁረው ያሰባሰቡትን ሃብት በከንቱ እንዲባክን የሚያስደርግ ነው። እንኳን ለትልቅ ዓላማ አባላት በተሰባሰቡበት ድርጅት ውስጥ ቀርቶ የግል ሕይወት በሚኖርበት ሁኔታ ይህ ብክነት አሳዛኝ ነው። ከዚህም በተጨማሪ የተጠቀሱት ሱሶች በተለያየ ደረጃ በጤንነታችን ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ናቸው። ሲጋር በቀጥታ ከሳምባናከልብ ጋር፣ መጠጥ ከልብ፣ ከጉበት፣ ከኩላሊት ወዘተ ጋር፣ ጫት ከሆድ ከአእምሮ ጋር የተያዙ የጤንነት ጉዳት አላቸው። ይህ ጉዳት እያንዳንዱ ሱስ ያለበትን ሰው በተለየ የሚጎዳ ቢሆንም የርሱ መጎዳት በሌሎች ላይ ጉዳት ያስከትላል። ጤና የሌለው፣ የአእምሮና የአካል ብቃት የሌለው ታጋይ ከሌሎች ጓዶቹ ጋር በእኩልነት መንቀሳቀስ አይችልም። በጉዞ መድከም፣ መፍዘዝ ይመጣል። እነዚህ ሱሶች የየግለሰቡ ናቸው ብለን የማንተዋቸው ለዚህ ነው። ሌሎችንም ጉዳት ላይ የሚጥሉ መዘዞች አላቸው። እኔ ማነኝ ስንል እነዚህ አይነት ሱሶች ካሉን እነዚህ ሱሶች ያሉኝ ግለሰብ ነኝ የሚል ተጨማሪ ምላሽ ይኖረዋል። እኔ ማነኝ የሚለው ጥያቄ ግን በነዚህ ስለራሴ ባቀርብኳቸው ጭብጦች ብቻ የሚጠቃለል አይደለም። የተሟላ ምላሽ ለማግኘት ብዙ የሚቀረው ነጥቦች አሉ።

እኔ ማነኝ?

እኔ ማለት ስሜ፣ ንብረቴ፣ ሱሶቼ፣ እድሜ፣ የትውልድ ቦታዬ፣ ጎሳዬ ዘሬ፣ ሃይማኖቴ ብቻ ናቸው ወይ? ወይንስ ሌሎች ጓዶቼ በቀላሉ ሊደርሱባቸው የማይቹላቸውና የማያዩዋቸው እኔ ግን ለብቻዬ የማውቃቸው ነገሮችም ይዤ መጥቻለሁ። እነዚህ ጓዶቼ በቀላሉ ለማየት የማይችሏቸው ነገሮች ግን እኔ የማውቃቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? ድፍረት፣ ጀግንነት፣ ቆራጥነት፣ ታማኝነት፣ ፍቅርን፣ ትእግስትን፣ ጽናትን ወዘተ ይዤ መጥቻለሁ? ሌሎችስ የነዚህ ተቃራኒ የሆኑ። ፈሪነትን መሠሪነትን፣ ክፋትን፣ ተንኮልን፣ መዋሸትን፣ ወላዋይነትን፣ ተራ ቅናትን፣ አሉባልተኛነትን ወሬኛነትን፣ አጭበርባሪነትን፣ ተላታሚነትን፣ ጠብ ጫሪነትን፣ መለገምን፣ መስገብገብንስ፣ ቱግ ማለትን ግብዝነትን ይዤ መጥቻለሁ? እየዋልን እያደርን መተዋወቅ ስንጀምር ለነዚህ ጥያቄዎች አንዳችን ስለ አንዳችን የምንለው ነገር ይኖረን ይሆናል። ገና ሕዝባዊ ኃይሉን ስንቀላቀል ግን በነዚህ ጉዳዮች ላይ ስለእኔ ከኔ በስተቀር ማንም የሚያውቅ ሰው አይኖርም። ፈሪ ልሁን ደፋር፣ ሃቀኛ ልሁን አጭበርባሪ የማውቀው እኔ ብቻ ነኝ። ደፋር፣ ሃቀኛ፣ ጀግና፣ ታማኝ፣ ጓዱን አፍቃሪ የሆኑ ባህሪዎቼ ለጎዶቼና ለድርጅቴ ጥንካሬዎች ናቸው።
 
 ሌሎች ባህሪዎቼ፣ ለምሳሌ መዋሸት፣ መወላወል፣ ተላታሚነት፣ አምባገነንነት፣ ሌብነት፣ ስግብግብነት ግለሰበኛነት፣ ወዘተ የሕዝባዊ አባላቱንና ድርጅቱን የሚጎዱ አደጋ ላይ የሚጥሉ መጥፎ ባህሪዎች ናቸው። ቀደም ብለን ከጠቀስናቸው ከሱስ ጋር ተያያዥነት ካላቸው ችግሮች እጅግ የከፉ ናቸው። ለምን ብለን እንጠይቅ።አሉባልተኛ ሰው ድርጅት ያምሳል። በአሉባልታው የተነሳ ግለሰቦችና ቡድኖች እርስበርሳቸው ሊጋጩ፣ በመሃከላቸው መተማመን ሊጠፋ ይችላል። ብሎም ድርጅት እስከማፍረስ ሊደርስ ይችላል። የሲጋራ ሱስ ወይም የመጠጥ ሱስ ያለበት ሰው ራሱን በቅድሚያ ይጎዳል። ድርጅቱንም ይጎዳል ግን ድርጊቱ ድርጅት የሚያፈርስ አይሆንም። ሲጋራ የሚያጨስ ሰው በጀግንነት ሊዋጋ ይችላል። ወላዋይ ሰው ግን ጓዶቹን በጦር ሜዳ ጥሎ ሊፈረጥጥ ይችላል። ሌሎችም ጎጂ የሆኑ ባህርይዎቻችንና ባህሎቻችን እያንዳንዳንችን ቤተስብ፣ ሃብት፣ ቤትና ንብረት በትነን እዚህ የተሰባሰብንለትን ዓላማ እንዳናሳካ የሚያደርግ አቅም አላቸው። ዋናውን ጠላት ወያኔን ትተን እርስ በርስ እንድንባላ፣ ወያኔ እስካሁን ካደረሰብን በደል በላይ የከፋ በደል እንዲያደርስብን የሚያደርጉ ናቸው። ይህ የከፋ በደልና ጥቃት ምን ሊመስል እንደሚችል ሁላችንም በቀላሉ ልንገምተውየምንችለው ነው።ይህ በመሆኑም እያንዳንዳችን ወደ ሕዝባዊ ኃይሉ ስንመጣ ይዘናቸው የመጣናቸውን ጎጂ ባህሎችና ባህርይዎች ያለምንም መወላወል መጋፈጥና ከሁላችንም ውስጥ አጥበን ማውጣት ይኖርብናል።

የግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል እነዚህን አይነት ጎጂ ባህሎች እንታገል ሲል የመጀመሪያው ድርጅት አይደለም። በሀገራችን የፖለቲካ ድርጅቶች ከተፈጠሩ ጀምሮ እነዚህ ጎጂ ባህሎች በየፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ ተነግሮ የማያልቅ ውድመት አስከትለዋል። እየዋለ እያደረ በበርካታ የሀገራችን የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ የእነዚህን ጎጂ ባህሎች አውዳሚነት እየታወቀ መጥቷል። ሆኖም ግን ተገቢውን ትኩረት በመስጠት እነዚህ ባህሎች በየድርጅቱ ውስጥ እንዳይሳፋፉና ሥር እንዳይሰዱ ማድረግ የቻለ ድርጅት እስካሁን የለም። በየመድረኩ የተለያዩ ድርጅቶች መሪዎች እነዚህን ጎጂ ባህሎችና ባህሪዎች እንታገላላን በማለት ቃል ቢገቡም እስካሁን ግን አንድም የተሳካለት ድርጅት አልተገኘም። ይህ ትግል ቀላል ስላልሆነብዙዎቹ ድርጅቶች በገዛ አባሎቻቸው የውስጥ ሽኩቻ፣ የርስበርስ መጠላለፍ፣ ሲወድሙ ሲሰነጣጠቁ ሥራ የማይሰሩ በድኖች ሆነው ሲቀሩ አይተናል።ከ1966ቱ አብዮት ጋር ብቅ ካሉት ድርጅቶች ጀምረን ታሪካቸውን መቃኘት እንችላለን። ኢህአፓ፣ ኢዲዩ፣ መኢሶን፣ ኢሰፓ፣ ኦነግ ወዘተ በራሳቸው ድርጅትና ከሌሎች ድርጅቶችጋር የገቡበት ሽኩቻና መጠላለፍ ነው ያወደማቸው ወይም ከሞት አፋፍ ላይ ያስቀመጣቸው። የወያኔ አይነት ድርጅት ዘረኛነትን መሰባሰቢያ በማድረጉና የሰዎችን ግንኙነት በዘር ሙጫ ለማጣበቅ በመቻሉ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ሲወዳደር ብዙም የውስጥ መጠላለፍ አልታየበትም። በሌሎችም ላይ የበላይነት ያገኘው ዘረኛ በሆነ ዓላማ ዙሪያ የተሰባሰቡት ከፍተኛ መሪዎች ለዘር አጀንዳቸው ቅድሚያ ሰጥተው አንድ ሆነው እንዲንቀሳቀሱ በማስቻሉ ነው።
 
 ይህም ሆኖም ወያኔም ቢሆን የድርጅት ውስጥ ሽኩቻና ሴራ መጠላለፍ ያልነበረበትድርጅት አይደለም። አሁንም ቢሆን መጠላለፉ የሌለበት ድርጅት ነው ማለት አይደለም። በቅረቡ እየታየ ያለው የወያኔ መዳከም በተቃዋሚ ጥንካሬ የመጣ አይደለም። የድርጅቱ ውስጣዊ መበስበስ፣ የቡድኖችና የግለሰቦች የሥልጣን፣ የጥቅም፣ የከንቱ ክብርና ዝና ሸኩቻ ነው።በወቅቱ በሚገኙት የተቃዋሚ ድርጅቶች ጎራ ያለውን ጉድ ሁላችንም እናውቀዋለን። ዛሬ ትብብር፣ ቅንጅትና ኅብረት ፈጥሮ ነገ መበታተን የተለመደ ነው። በየቀኑ ድርጅት መፈልፈል ነው። ዛሬ ተመሥርተው፣ በማግስቱ መሰነጣጠቅ መፍረስ እጣቸው የሆነው የሀገራችን ድርጅቶች ይህን መራራ ጽዋ በመጎንጨት ላይ ያሉት በወያኔ የስለላ ችሎታና ሌላም ክህሎት አይደለም። የየድርጅቶቹ መሪዎችና አባላት ደካማና ጎጂየሆኑ ባህሎቻቸውንና ባህሪዎቻቸውን በደንብ መገንዘብና ማስወገድ ስላልቻሉ ነው። ሃገርና ወገን የመሳሰሉ እጅግ ክቡር የሆኑ ነገሮችን ከተራ የግል ስም፣ ክብር ጥቅምና ፍላጎት በታች አድርጎ ለማየት የማይፈልጉ አባላት ድርጅቶች በማቀፋቸው እነዚህ አሳፋሪና አሳዛኝ የመሰነጣጠቅ ችግሮች ሲከሰቱ አይተናል። እኛስ? እነዚህን ከየአንዳንዳችን ማንነት የሚፈልቁትን ጎጂ ባህሎች አስወግደን የጓዶቻችን የወገናችን የሕዝባችን ተስፋመሆን እንችላለን? የግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል ትልቁ ፈተና ይህ ነው።አናሳ ቁጥራችንን በሂደት ማብዛት እንችላለን። ወታደራዊ ሙያ የሌላቸውን ጓዶቻችንን ከፍተኛ ወታደራዊ ሥልጠና እንዲወስዱ ማድረግ እንችላለን። የታሪክ፣ የፖለቲካና የሥነ መራር እውቀት የሌላቸውን እውቀቱን በቀላሉ እንዲላበሱ ማድረግ እንችላለን። የቀለም ትምህርት ለሌላቸው እዚሁ በረሃ ውስጥ ከየትኛውም የሀገራችን ት/ቤት ወይም ኮሌጅ በላይ ጥራቱ የጠበቀ ትምህርት መስጠት እንችላለን። ይህን ሁሉ ማድረግ መቻላችን ግን ጎጂ ባህሎቻችን ከሚያስከትሉብን ውድቀት አያተርፉንም። ብዙ የወታደራዊ ሳይንስ እውቀት የነበራቸው፣ ወታደራዊ መሪዎች የያዘ መንግሥት አነስተኛ ወታደራዊ እውቀትና ልምድ ባላቸው ግለሰቦችና መሃይሞች በሚመራ ጦር ሲፈታ አይተናል።
 
በተለያዩ የእውቀት ዘርፎች ሊቃውንት ሊባሉና እንዲሁም በእድሜና በተመክሮ በከበዱ ምሁራን የታጨቁ ድርጅቶች ወያኔን የመሰለ የሀገር ተምች አስቀምጠው እንደ ባለጌ ኮማሪት በአደባባይ ሲዘላላፉ፣ ሲዘራጠጡ፣ ራሳቸውን አዋርደው የኛ ናቸው ያላቸውን ሕዝብ ሲያዋርዱ አይተናል።ለድርጅቶች መዳከም ወይም መውደም ምክንያቶቹ ክህደት፣ ጭቅጭቅ፣ መጠላለፍ የመሳሰሉት በሰዎች መሃከል መልካም ግንኙነት እንዳይኖር እንቅፋት የሆኑ ባህሪዎች ብቻ አይደሉም ። አድርባይነት፣ አጎብዳጅነት፣ ዝርክርክነት፣ ተጨንቆና ተጠቦ አለማቀድ፣ የግብር ይውጣ አሰራር ፣ጀብደኛነትና ወዘተ የመሳሰሉት ባህሎቻችን ለድርጅቶች መዳከም መውደም የራሳቸው አስተዋጸኦ አድርገዋል።እኛስ የግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል አባላት እስካሁን በሀገራችን ውስጥ ከበቀሉት ድርጅቶች የተሻለ እጣና ታሪክ እንዲኖረን ምን ማድረግ አለብን? መልሱ በሌሎች ጥያቄዎችና ምለሾች የሚገኝ ነው።
 
 በቅድሚያ ራሳችንን መጠየቅ የሚገባን፣ ቀደም ብለን የጠቀስናቸውና ሌሎችም ጎጂ እና አፍራሽ ባህርያት በተለያየ ደረጃም ቢሆን በውስጣችን እንዳሉ እንገነዘባለን ወይ? ለዚህ ጥያቄ የሉም የሚል ምላሽ መስጠት አንችልም። ምንም ያህል ብጹእና የበቃን ብንሆንም ህጸጽና ድክመት አያጡንም። የሰው መሆን አንዱ ትርጉሙ የሚሳሳት የሚያጠፋ የሚል ነውና። እነዚህ ጎጂ የምንላቸው የግለሰቦች የቡድኖች ባህርያትና ልምዶች ምንድን ናቸው? እውን በደንብ እናውቃቸዋለን? ለምንድነው እነዚህ ባህርያት ልምዶች በማኅበራችንና በሀገራችን ውስጥ ከሌላው ማኅበረሰብና ሀገር ውስጥ ከሚታየው በላይ ሥር ሰደውና ደንድነው የሚገኙት? የግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል ከዚህ የባህልና የባህርይ ነቀርሳ ለማምለጥ ምን ማድረግ አለበት? ለመሆኑ እነዚህን ጎጂ የምንላቸውን ባህርያትና ልምዶች በደንብ እናውቃቸዋለን? — with Revoultion Soon and 19 others in Addis Ababa, Addis Abeba

No comments:

Post a Comment