Saturday, September 15, 2012

በወያነ እስር ቤት ሲማቅቁ የነበሩ ሁለቱ ሲውዲናዊያን ጋዘጠኞች የተፈጸመባቸውን ሰቆቃ በማጋለጥ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጡ


በወያኔ ፍርድ ቤት የአሥራ አንድ አመት እስራት ተፈርዶባቸው ከአንድ አመት በላይ በቃሊቲ እስር ቤት ሲማቅቁ የቆዩት ሁለቱ ስዊዲናዊያን ጋዜጠኞች ማርቲን ሽበየ እና ጆን ፐርሰን በይቅርታ ሥም ተፈተው አገራቸው ምድር በደረሱ የመጀመሪያው ቀን ላይ በስቶክሆልም ሲውዲን ተሰብስቦ ይጠባበቃቸው ለነበሩ የአገሩ ጋዜጠኞች መግለጫ መስጠታቸውን የግንቦት 7 ተባባሪ ዘጋቢ ከስቶክሆለም በላከልን ዘግባ ገለጸ።

ሁለቱ ጋዜጠኞች አዳራሹን ሞልቶ ይጠባበቃቸው ለነበሩ ጋዜጠኞች ለእስር የዳረጋቸውንና እስር ላይ በነበሩበት ወቅት የተፈጸመባቸውን ሰቆቃ ለመግለጽ ወደ አዳራሹ ሲገቡ ደማቅና በጋለ ጭብጨባ የታጀበ የጀግና አቀባበል ነው የተደረገላቸው እንደተባባሪ ዘጋቢያችን ሪፖርት።

የወያኔ አገዛዝ በኦጋዴን ንጹሃን ዜጎቻችን ላይ የሚፈጽመውን የጅምላ ጭፍጨፋ ለመዘገብ ሱማሊያን አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ እንደተያዙ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ወቅት የተናገሩት ጋዜኛ ማርቲን ሽበየና ጋዜጠኛ ጆን ፐርሰን በቁጥጥር ሥር ባዋሉዋቸው የወያኔ ሰራዊት ክፉኛ ድብደባ እንደተፈጸመባቸውና በዚህም ድብደባ ምክንያት ብዙ ደም እንደፈሰሳቸው እንቧ እየተናነቃቸው ገልጸዋል።

ሁለቱም ጋዜጠኞች ድብደባው የተፈጸመባቸው ድንበሩን አቋርጠው እንደተያዙ በህይወት ዘመናቸው የማይተዋወቁትን ጥይት የጎረሰ የጦር መሳሪያ ይዘው ሲተኩሱ ፊልም እንዲቀረጹ የተሰጣቸውን ት ዕዛዝ ለመተግበር በማቅማማታቸው እንደሆነ ገልጸዋል። ድብደባውን የፈጸሙባቸው የመከላኪያ ሠራዊት አባላት የተሰጣቸውን ጠመንጃ ይዘው ፊልሙን የማይቀረጹና ጥፋተኞች ነን በማለት የምስክርነት ቃል የማይሰጡ ከሆነ በታጠቁት መሳሪያ እዚያው እንደሚገድሉዋቸው እንደዛቱባቸው እነርሱም በተፈጸመባቸው ማስፈራራት ተገደው ጥፋተኛ ነን ለማለት እንደቻሉና ወደ ኋላ ፍርድ ቤት ሲደርሱ ማስረጃ ሆኖ የቀረበባቸውን ቪዲዮ ተገደው እንደተቀረጹ አጋልጠዋል።

በትናትናው ዕለት መስከረም 4 ቀን ስቶክሆለም ውስጥ ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡት ሁለቱም ጋዜጠኞች የደረሰባቸውን ሰቆቃ ሲናገሩ ስሜት በሚቆረቁር ሁኔታ ስለነበር አዳራሹ ውስጥ የነበሩት ሁሉ በሃዘን ተውጠው ነበር ተብሎአል። በተለይ ጋዜጠኛ ማርቲን ሽበየ በወቅቱ የደረሰባቸውን ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ሲናገር በሃሰት የተቀነባበረባቸውን ውንጀላ በማስረጃ ለማስደገፍ ሲሉ የፈጠሩትን የውሽት ፊልም ለመቅረጽ በረሃ ውስጥ ብዙ ቀናት እንዳቆዩቸውና መንገላታት እንደደረሰባቸው በመጨረሻም ያንን ፊልም ለፍርድ በየት እንደማስረጃ እነደተጠቀሙበት አስረድቶ ፊልሙን ለመቀረጽ ፈቃደኛ የሆንነው ህይወታችንን ለማቆየት ስንል ነው በማለት በምን አይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዳለፉ ሲቃ እየተናነቀው ገልጾአል። ጋዜጠኛ ማርቲን አሳሪዎቻቸው የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ንቅናቄን ONLFን እነዲናወግዝላቸው ተጠይቀን ፈቃደኛ ሳንሆን ቀርተናል ብሎአል።

ፍትህ በሌለበት ፍርድ ቤት ከቀረቡ ቦኋላ የአሥራ አንድ አመት እስራት ተፈርዶባቸው ቃሊቲ ወህኒ ከወረዱ ቦሃአላ በአንድ ክፍል ውስጥ እስከ 250 ዕስረኞች ታጉረው እንደሚገኙ፤ በእስር ቤት ቆይታቸው የተለያዩ ሰዎች እንደሚገረፉ ያውቁ እንደነበር የመሰከሩ ሲሆን ሃሳብን መግለጽ እንሽብርተኝነት የሚቆጠርበት አገር ውስጥ በሰዎች ላይ የሚፈጸመው ሰቆቃ ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ የአይን ምስክር ለመሆን በመብቃታቸው ይህ እንዲቆም ከአሁን ቦኋላ ተግተው ለመታገል የሚችሉበትን ወኔና ድፍረት ሰንገው እንደወጡ ገልጸዋል።

በመጨረሻም በአሁኑ ሰዓት በቃሊቲ እስር ቤት ታጉረው የሚገኙ በርካታ እስረኞች በተፈታንበት ወቅት እየደረሰባቸው ያለውን ግፍና መከራ ለአለም ህዝብ እንድናሳውቅላቸው አደራ ስላሉን በቅርቡ በምናሳትመው መጽሃፍ ዝርዝሩን ይፋ እናደጋለን በማለት ቃል ገብተዋል።

ጋዜጠኞቹ ከእስር ለመፈታት ጽፈው አስገብተዋል ስለተባለው የይቅርታ ደብዳቤ ጉዳይ ተጥይቀው በሰጡት ምላሽ ምንም ወንጀል ሳንፈጽም በሃሰት በተቀነባበረብን ክስ የአስራ አንድ አመት እስራት ስለተፈረደብን ለመገላገል ስንል ያደረግነው ነው በማለት ወያኔ በሃሰት ወንጅሎ ይቅርታ በማስጠየቅ የሚመጻደቅበትን የጅሎች ጥበብ እርቃኑን አውጥተዋል።

ሁለቱ ጋዜጠኞች የሰጡትን ጋዜጣዊ መግለጫ በርካታ ኢትዮጵያዊያን አዳራሽ ውስጥ ገብተው እንደተከታተሉና የወያኔን አምባገነንነት በማጋለጥ ላሳዩት ጀግንነት ምስጋናቸውን እንዳቀረቡላቸው ተያይዞ የደርሰን ዜና ያስረዳል።

አድማጮቻችን በሲውድንኛ ቋንቋ የተሰጠውን የሁለቱ ጋዜጠኞች መግለጫ ሙሉ ትርጉም ጊዜ ካገኘን ወደፊት ይዘን የምንቀርብ መሆናችንን ከወዲሁ እንገልጻለን።

No comments:

Post a Comment