Saturday, September 29, 2012

የጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሣለኝ ልዩ ቃለምልልስ ከቪኦኤ ጋር- ክፍል 1 ና ክፍል 2

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ለመሣተፍ በተገኙበት በኒው ዮርክ ከተማ ለቪኦኤ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡






አቶ ኃይለማርያም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መንበረ መራሂ መንግሥቱን ከተረከቡ ወዲህ ለውጭ መገናኛ ብዙኃን አካል ቃለምልልስ ሲሰጡ ይህ ለአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ጣቢያ የሰጡት ልዩ ቃለ-ምልልስ የመጀመሪያቸው ነው፡፡

በኢትዮጵያ የሃገር ውስጥ ጉዳዮቿ፣ በውጭ ፖሊሲዋና እንቅስቃሴዎቿ ላይ ያነጋገራቸው የቪኦኤ የአፍሪካ ቀንድ አገልግሎት ኃላፊ ፒተር ኃይንላይን ለአቶ ኃይለማርያም ካቀረባቸው ጥያቄዎች አንዱ ኢሕአዴግ የሕወሓት ተፅዕኖ እንዳለበት ይነገራል - የሚል ነበር፡፡

አቶ ኃይለማርያም ለጥያቄው መልስ መስጠት የጀመሩት የኢሕአዴግን የተፈጥሮ ሂደት በመተንተን ሲሆን የጥምረቱ አባል የሆኑት አራቱ ፓርቲዎች ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ - ሕወሓት፣ ብሔረ-አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ - ብአዴን፣ የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት - ኦሕዴድ እና የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ - ደኢሕዴን እንደአፈጣጠራቸውና በትግሉ ውስጥ እንዳሣለፉት ጊዜ ጥንካሬያቸው፣ አቅምና ልምዳቸው አንዱ ከሌላው እንደሚለይ አመልክተዋል፡፡
“ይሁን እንጂ - አሉ አቶ ኃይለማርያም - ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ የተካሄደው የሕዳሴ ሂደት አዲስና የነጠረ የፓርቲውን ፖሊሲ፣ ስትራተጂና አቅጣጫ እንዲወጣ አድርጓል፡፡…” ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጠሉና “… በዚህም መሠረት ሁሉም ፓርቲዎች ወደ አንድ ንቅናቄ ገቡና አንድ ዓይነት አቅጣጫን፣ አንድ ዓይነት ልምድና የአሠራር አካሄድ በፓርቲው የውስጥ ሥርዓት አሠፈኑና ተመጣጣኝ ሊባል የሚችል ሥፍራ ያዙ፡፡ በመሆኑም በሁሉም የኢሕአዴግ መዋቅሮች ውስጥ፤ ለምሣሌ በምክር ቤቱ ውስጥ፣ በፓርቲው ጉባዔ፣ በሁሉም ኃላፊነቶችና የሥራ ምደባዎች ላይ አራቱም ፓርቲዎች እኩል ናቸው፡፡ ለዚህ እማኙ እኔ የዚህ ሂደት ውጤት መሆኔ ነው፡፡ እኔ በሕይወት ያለሁ ማሣያ ነኝ፡፡ ኢሕአዴግ በዚህኛው ወይም በዚያኛው ቡድን ተፅዕኖ ምክንያት በተ ወሰኑ ቡድኖች ወይም የጎሣ ቡድኖች ላይ የተዛባ አያያዝ አለው ብለው ለሚገምቱ ይህ የሃሰት እና ተጨባጭነት የሌለው ግምት ነው፡፡ በመሆኑም በፓርቲያችን የውስጥ ሥርዓት ውስጥ የመጀመሪያው ጉዳይ ዴሞክራሲያዊ ግንኙት ነው፡፡ የጥንካሬአችን መሠረት የፓርቲው የውስጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ነው፡፡ ከውጭ ሆነው የሚያስቡት፤ የሚያስቡት ፓርቲውን የውስጡን ሳያውቁ ነው፡፡ በመሆኑም ይህንን የፓርቲውን አሠራርና ፓርቲው እንዴት እንደሚሠራ ብዥታ ላለባቸው ሰዎች ማስጨበጥ አለብን፡፡ ይህ ፓርቲ በውስጡ ዴሞክራሲያዊ ነው፤ ውሣኔዎቹና ሥራዎቹ የሚከናወኑት በዴሞክራሲያዊ አካሄድ ነው፡፡ በመሆኑም ይህኛው ወይም ሌላኛው ፓርቲ ተፅዕኖ ያደርጋል፤ ወይም ይጫናል ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም አራቱም አባል ፓርቲዎች እኩል ቁጥር ያለው ውክልና አላቸው፡፡ ከፈለጉም በዴሞክራሲያዊ ሂደት የሚፈልጉት ተፅዕኖ ሁሉ አላቸው፡፡ በመሆኑም ዋናው ጠቃሚ ጉዳይ በፓርቲው ውስጥ ዴሞክራሲ አለ፤ እየሠራ ያለ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ሰዎች ያላቸውን ግምት አልቀበልም፡፡ ለማሣያም እኔ የተመረጥኩት በአራቱም ፓርቲዎች ተወካዮች በሙሉ ድምፅ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በእኔ ፓርቲ በደኢሕዴን ብቻ ሣይሆን በሌሎቹም ጭምር ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ዴሞክራሲያዊ አካሄድ ባይኖረን ኖሮ ለየፓርቲያችን ወገናዊ ሆነን እንቀር ነበር፡፡ በመሆኑም የእኔ የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ሆኜ መመረጥ ዘግይቶም የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን የዚህ ሂደት ማሣያ ነው፡፡” ብለዋል፡፡

ቪኦኤ፡-

በሁለት ሺህ ሰባት በሚካሄደው ምርጫ በዕጩነት ይቀርባሉ? ማለት ከዚህ ካሁኑ የሽግግር ወቅት በኋላ የፓርቲው መሪ የመሆን ተስፋ አለዎት?

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፡-

የፓርቲው ጉባዔ ከመፍቀዱ በፊት፥ ለምሳሌ ልበል፥ ፕሬዚደንት ኦባማ የፓርቲያቸው አባላት ይሁንታ ሳይሰጡ “ፕሬዚደንታዊው ዕጩ እኔ ነኝ” ማለት ይችላሉ? አይችሉም። ልክ እንደዚያው ይሄም የፓርቲው ጉባዔ የፓርቲው ሂደት የሚወስነው ነው። ምክንያቱም ዴሞክራሲያዊ ነውና። ስለዚህ ፓርቲው ያንን ዕድል የሚሰጠኝ ከሆነ እወስደዋለሁ። ካልሰጠኝ ደግሞ ሌሎች መሠራት ያለባችውን ሥራዎች እሠራለሁ ማለት ነው። የዲሞክራሲ ሂደት ስለሆነ እኔ በግሌ ተነስቼ የፓርቲው ብዙኃን አባላት ነገ የሚመጡ ጉዳዮችን በሚመለከት የሚያደርጉትን ውሣኔ እኔ አሁን ልወስነው አልችልም። ስለሆነም ይህ ለዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የሚቀርብ ጥያቄ አይደለም። የፓርቲው አባላት ግምገማቸውን አካሂደው የሚወስኑትን “ይመርጡኛል፤ አይመርጡኝም” ብሎ ከወዲሁ መተንበይ አይቻልም።

ቪኦኤ፡-

ኢትዮጵያ ያለው የአውራ ፓርቲ ሥርዓት ነው ሲሉ ገልፀውታል። ኢሕአዲግ ሌሎች ፓርቲዎች እንዲያድጉ ለመቀበል በሚያስችልበት ደረጃ ለመለወጥ ምን ያህል ጊዜ የሚያስፈልገው ይመስልዎታል?

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፡-

ይህም በሂደት ላይ ያለ ነው። በዚህ ጊዜ ይሆናል ብዬ የተወሰነ ቀን ላስቀምጥለት አልችልም። በሂደት የሚለወጥ ነው የሚሆነው። የእኛ ፍላጎት ግን ባጭር ጊዜ ውስጥ እንዲሆን ነው። ምክንያቱም በዚህች ሀገር ንቁና ይበልጥ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲዎች በወጡ ቁጥር የሕዝቡም ውሣኔ የመስጠት አማራጭ የዚያኑ ያህል ያድጋልና ነው።
ለእኛ ግን አስፈላጊው የፓርቲዎች ቁጥር አይደለም። የሚያስፈልገው፥ ለሕዝብ የሚሠራው የትኛው ነው? የሕዝቦችንና የአባሎቹን ፍላጎትና ትልም የሚደግፉ ፖሊሲዎች ያሏቸው መሆናቸው ነው አስፈላጊው። ስለዚህ ይበልጥ ተመራጩ መንገድ የሚመስለኝ በሀገሪቱ ውስጥ ንቁና ጠንካራ ፓርቲዎች የመውጣታቸው ጉዳይ ነው። ያም ሲሆን ነው የአንድ ፓርቲ የበላይነት ከሌሎቹ ጋር አማራጭ ሆኖ ሊቀርብ እና ሕዝቡ የፈለገውን ለመምረጥ ዕድል ሊሆን የሚችለው። ይህ ማለት ግን ኢሕአዴግ የበላይነቱን ያጣል ማለት አይደለም። የሕዝቡ ምርጫ ነው ወሣኙ። ስለዚህ አንዳንድ የአውሮፓ ፓርቲዎችን ብናይ ለሃምሣና ስልሣ ዓመታት በበላይነት የቆዩ ናቸው። በጃፓንም እንዲሁ ለበርካታ ዓመታት ሠርተዋል። ስለዚህም ኢሕአዴግ እንደ ዱላ ቅብብሎሽ ሩጫ ከትውልድ ወደ ትውልድ ለረዥም ዓመታት ሊቆይ ይችላል። እንዳልኩት ግን ሁሉም በሂደት የሚለወጥ እንጂ ቀን ሊቆረጥለት የሚችል አይደለም፡፡»

ቪኦኤ፡-

ኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን ወይም መረጃ ፍሰትን በጥብቅ ትቆጣጣራለች ተብላ በአንድአንድ አካባቢዎች ትነቀፋለች። ነቀፋ የሚያቀርቡ ጋዜጦች ተዘግተዋል፤ ጋዜጠኞች ፀረ-ሽብር ህግ በመተላለፍ ተወንጅለዋል፤ ዌብሳይቶች ይዘጋሉ፤ የአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ሥርጭትም ሳይቀር ይታፈናል፤ የውጭ ሥርጭቶች ይታፈናሉ። የርስዎ መንግሥት በተለይ ትላልቆቹን ጉዳዮች በተመለከተ እንደተዘጋው ፍትህ ጋዜጣ እና የታሠረውን በጣም ነቃፊ የሆነ የብሎግ ጋዜጠኛ እክንድር ነጋን የመሣሱትን ጉዳዮች አስመልክቶ የርስዎ መንግሥት ምን ያደርጋል?

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፡-

ጓደኞችህ እንደሆኑና ስለእነርሱም የሚሰማህ ሕመም ሊኖር እንደሚችል አውቃለሁ፡፡ ፒተር! መረዳት ያለብህ፣ ሁለት ቆብ ያለው ማንም ሰው ሁት ቆብ ማጥለቁን ማቆም አለበት፡፡ አንዱን ብቻ ነው ማድረግ ያለበት፡፡ እነዚህ ሁለት ቆቦች አንዱ በሕጋዊ መንገድ መንቀሣቀስ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሕገወጥና የሁከት መንገድ፤ ከአመፀኛ ድርጅቶች ጋር መሥራት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የታሠሩት ሰዎች የታሠሩት ወይም የተከሰሱት በሕጋዊ መንገድ በመንቀሣቀሣቸው አይደለም፡፡ የታሠሩት ሰዎች ከአመፅ አራማጅ ድርጅቶች ጋር የተገናኙ ናቸው፡፡ በጋዜጠኝነት ሥራቸው ምክንያት አይደለም የታሠሩት፡፡ ይህ የተፈቀደ ነው፡፡ ታውቃለህ፤ አንተ እዚያ ነበርክ፤ እዚያ ሠርተሃል፤ ነገር ግን ቀዩን መሥመር ማለፍ የለብህም፡፡ አመፅ ቀስቃሽና የሽብር ፈጠራ ድርጅቶችን ማገዝን የመሣሰሉ አድራጎቶች ውስጥ መግባት የለብህም፡፡ የብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ጋዜጠኝነት አይደለም፡፡ ተቃዋሚ መሆንም አይደለም፡፡ ተቃዋሚ በሁከትና በሕገወጥ መንገድ አይንቀሣቀስም፡፡ ከሽብር ፈጠራ ቡድኖች ጋርም አይገናኝም፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች አይደሉም፤ ግለሰቦች ናቸው፡፡ እኛ ማንኛውንም ፓርቲ አልከሰስንም፡፡ ምክንያቱም በሕጋዊነት የተመዘገቡት ፓርቲዎች በሃገሪቱ ውስጥ በሕጋዊነት መንቀሣቀስ ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጂ በእነዚህ ፓርቲዎች ውስጥ በአባልነት የተመዘገቡ ግለሰቦች፤ ግን ሁለት ምዝገባ ያላቸው፤ አንዱ በሕጋዊ ፓርቲዎች ውስጥ፣ ሌላው ምዝገባ በሕገወጥና የሽብር ፈጠራ ፓርቲዎች ውስጥ የሆነ የሚከሰሱት በሕጋዊው ቆባቸው ሳይሆን በሌላኛው፣ በሕገወጡና ከሽብር ፈጠራ ጋር በተያያዘው ቆባቸው ነው፡፡ በሁለቱ መካከል ያለውን መለየት አለብን፡፡ በግልፅና ያለአንዳች ማወላወል ካቆሙና በሕጋዊ መንገድ ለመሥራት ከወሰኑ ሁልጊዜ መድረኩ አለ፡፡ ሁለቱንም የሚቀላቅሉ ከሆነ ሁለቱን ለይተን፤ ለሕገወጡ፣ ለአመፅና የሽብር ፈጠራ ግንኙነታቸው እንከስሣቸዋለን፡፡ ይህ በሃገሪቱ ሕግ መሠረት ይያዛል፤ ያስቀጣልም፡፡ እነዚህ ልዩነቶች ግንዛቤ ሊጨበጥባቸው ይገባል፡፡ ለእናንተ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ይህ ችግር አይደለም፡፡ ምክንያቱም ጋዜጠኞች በሕገወጥ መንገድ አይንቀሣቀሱም፡፡ የሚሠሩት በሕጋዊ መንገድ ነው፤ ያላቸውም አንድ ቆብ ብቻ ነው፡፡ በዚህና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ልዩነት ይኸው ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ምዕራብ ሃገሮች ይህንን ቅልቅል አይረዱም፡፡ ምክንያቱም ችግሩ የለባቸውም፡፡ ሁሉም ጋዜጠኞች በሕጋዊ መንገድ ሲሠሩ ነው የሚያዩት፡፡ ይህ የሕገወጡና የሌላኛው ቆብ ችግር የለባቸውም፡፡ ያ ልዩነት አንድንዴ ብዥታ ያለበት ነው፡፡ እኛን በሚመለከት በቅድሚያ የምናተኩረው በብሔራዊ ፀጥታ ጉዳዮቻችን ላይ ነው፡፡ ይህ የብሔራዊ ደህንነት ጥቅም ጉዳያችን ደግሞ አንድ ሰው ሁለት ቆብ ስላለው ብቻ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም፡፡ በሕጋዊ መንገድ ብቻ እንዲንቀሣቀሱ እንመክራቸዋለን፡፡ በጋዜጠኝነትም ቢሆን፣ ተቃዋሚዎችም ቢሆኑ፡፡

ቪኦኤ፣-

ባሁኑ ጊዜ መንግሥትዎ የፕሬስ ነፃነትን ምናልባት ትንሽ ለቀቅ ማድረግ ላይ ምን አቋም አለው? ባሁኑ ጊዜ ዌብሳይቶች ተዘግተዋል፤ የውጭ ሥርጭቶች ታፍነዋል፤ ጋዜጦች ተዘግተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፡-

ግልፅ መሆን ያለበት የእኔ መንግሥት እነዚህን ጉዳዮች የማገድ ፖሊሲዎች የሉትም፡፡ የሚወሰነው በዌብ ሣይቶቹም ይሁን በማንም፤ በማንነታቸው ነው፡፡ ከእንደዚህ ዓይነት ድርጅቶች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ካላቸው፣ ግልፅ ነው፤ ያ በሁሉም ሃገር ውስጥ ይደረጋል፡፡ የኦሣማ ቢን ላደንን ብሎግ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ መክፈት አትችልም፡፡

ቪኦኤ፡-

በመጨረሻም አንድ የውጭ ፓሊሲ ጥያቄ ላቅርብልዎ በማለት ፒተር ለአቶ ኃይለማርያም የሠነዘረው ጥያቄ ስለ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳንች ስምምነት ነው። የሁለቱ አገሮች መሪዎች ሰሞኑን አዲስ አበባ ላይ ሲደራደሩ ነበር፤ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ለድርድሩ ባደረጉት አስተዋጽዖ በጣም ሲመሰገኑ ነበር፡፡ እርስዎ ጉዳዩን ይከታተሉ ነበር?

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፡-

መልካም ዕድል ሆኖ ልክ ከአምስት ደቂቃ በፊት ነው ስምምነቱን የተፈራረሙት። ይህን ጥያቄ ስላነሳህ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ ስምምነቱ ሲካሄድ ኒው ዮርክ ሆኜ በቀጥታ ስከታተል ነበር።
ስምምነት ላይ ደርሰው ተፈራርመዋል። እንደሚታወቀው ፖሊሲአችን ከቀድሞው ያልተዛነፈ ነው። ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በሱዳን ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን እንዲፀናም አስተዋጽዖ አድርገዋል። ስምምነቱን ለማሣካት ትልቅ ጥረት አድርገዋል፤ ድጋፋቸው፣ የማደራደር ችሎታና ስልታቸው ውጤታማ ሆኗል። የርሳቸው ህይወት ካለፈ በኋላ ፈለጋቸውን በመከተል ከሁለቱም ሱዳኖች መሪዎች ጋር ስሠራ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ለድርድሩ ጥሩ መሠረት ስለጣሉ ኢትዮጵያ ተደማጭነት አግኝታለች። ለዚህም የደቡብና የሰሜን ሱዳን መሪዎችን አመሰግናለሁ።
መሪዎቹ ከአብዬይ ጉዳይ በስተቀር ሙሉ በሙሉ ለማለት ይቻላል በሁሉም ነጥቦች ላይ ተስማምተዋል። የአብዬይ ጉዳይም የአፍሪቃ ህብረት ሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት ኃላፊነት እንዲወስድና ውሳኔውን እንደሚቀበሉ ተስማምተዋል።
የእኛ ፖሊሲ ለአፍሪቃ ቀንድ ሠላምና መረጋጋት፣ እንዲሁም ብልፅግና እንዲሰፍን ለትብብር መሥራት ነው። እንደ ኢጋድ ሊቀ መንበርም ዓላማችን ይህ ነው። መልካም ዕድል ሆኖ ሶማሊያም የሽግግር ጊዜዋን አብቅታ ብቁ ፕሬዚደንት መርጣለች። ፓርላሜንታዊ ሥርዓት አስፍና በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ኢኮኖሚዋን እንደምታዳብር ተስፋ አለን።

ይቀጥላል…







 

No comments:

Post a Comment