Wednesday, October 3, 2012

ዊኪሊክስ በኢትዮጵያ አውሮፕላን ላይ ተፈጽሟል የተባለውን ሴራ አጋለጠ

ኢትዮጵያውያን የሂዝቦላ መረጃ አቀባዮች የቤት ሠራተኛ ተመስለው አታለዋል

በአስራት ሥዩም

በዓለም እጅግ አነጋጋሪና ገናና ለመሆን የበቃው የዊኪሊክስ ድረ ገጽ ይፋ ባወጣው አዲስ መረጃ የበረራ ቁጥር “ET-409” የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 አውሮፕላን፣ ከቤይሩት ራፊቅ ሐሪሪ አውሮፕላን ማረፊያ ጥር 17 ቀን 2002 ዓ.ም. ከመነሳቱ ወዲያው ሲከሰከስ፣ የእስራኤል የስለላ ድርጅት ሞሳድ በተሳተፈበት ምስጢራዊ የደኅንነት ሥራ ሳቢያ ሰለባ ሳይሆን እንዳልቀረ አመለከተ፡፡

በኢራን የደኅንነት መሥርያ ቤት የሚደገፈው ሂዝቦላም ተሳታፊ እንደነበር ይፋ አድርጓል፡፡
ስትራትፎር ግሎባል ኢንተለጀንስ ለተባለ ተቋም የሚሠሩ ተንታኞች የተለዋወጧቸውን የኢሜል መልዕክቶች ባለፈው ሐሙስ ይፋ ያወጣው ዊኪሊክስ፣ ከአደጋው ክስተት ጀምሮም ሆነ ቀድሞ የነበሩ የበረራ መረጃዎችን የመዘገበው የአውሮፕላኑ “ጥቁር ሳጥን” አደጋው የደረሰው በአብራሪዎች ስህተት ስለመሆኑ ምንም ዓይነት መረጃ እንዳልመዘገበ ተንታኞቹ መናገራቸውን አውጥቷል፡፡ ሆኖም የሊባኖስ የስለላ ተቋም በሞሳድ የተፈጸመ ቀድሞ የማጥቃት ዕርምጃና ሂዝቦላን የተካረረ ጠብ ውስጥ ለመክተት የተደረገ ሴራ ነው በማለት መረጃውን አጣጥሎታል፡፡


‹‹አውሮፕላኑ በተሳሳተ መረጃ እንዲከሰከስ የተደረገው የሐሰን ናስረላህ ወንድም ልጅ የሆነው ሀሺም ሰይፈዲን ወደ አዲስ አበባ ያመራ በነበረው የበረራ ቁጥር “ET-409” አውሮፕላን ተሳፍሯል በሚል ነው፤›› መባሉን ድረ ገጹ ይፋ አድርጓል፡፡ በሂዝቦላህ የአመራር ዕዝ ውስጥ ሰይፈዲን ሁለተኛ ሰው በመሆኑ፣ ይህንን ግለሰብ ማስወገድ ተገቢ መሆኑ ስለታመነበት ዕርምጃው ተወስዷል ብሏል፡፡ የአብራሪ ስህተት በዝቅተኛ የአየር ክልል ውስጥ እየበረረ የነበረን አውሮፕላን ሊያጋይ አይችልም ያሉት ተንታኞቹ፣ የአብራሪ ስህተት ቢሆን እንኳ ምናልባት ሚዛኑን ስቶ ይከሰከስ ይሆናል እንጂ እየበረረ ሳለ ሊጋይ አይችልም በማለት ይደመድማሉ፡፡

‹‹የሊባኖስ ባለሥልጣናት ትክክለኛውን የአደጋ መንስዔ ለማመን ያልፈለጉት በጣም የላላ የደኅንነት ሥርዓት እንዳላቸውና ፈንጂ በድብቅ ወደ ቤይሩት ኤርፖርት መግባቱን ስለሚያጋልጥባቸው ነው፤›› ሲሉ ተንታኞች የተለዋወጡትን መረጃ ዊኪሊክስ አስነብቧል፡፡

እስካለፈው የካቲት ወር ድረስ ዊኪሊክስ ‹‹የዓለም የስለላ ፋይሎች›› (Global Intelligence Files) የሚል ስያሜ ከሰጣቸው መረጃዎች ውስጥ በአሜሪካ ቴክሳስ መቀመጫውን ያደረገው የስትራትፎር ግሎባል ኢንተሊጀንስ ዶሴ አንዱ ነው፡፡ እንደ ዊኪሊክስ ማብራርያ ይህ የስለላ ተቋም ለአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት፣ ለባህር ኃይልና ለመከላከያ ደኅንነት ኤጀንሲ የስለላ መረጃዎች ምንጭ ሆኖ የሚያገለግል ነው፡፡ የስትራትፎር ተንታኞች ደግሞ በበርካታ አገሮች ውስጥ ከሚገኙ ከስለላና የደኅንነት ሰዎች ጋር የጠበቀ ግንኙነት አላቸው፡፡

ለዚህ ዋቢ የሚሆነው ደግሞ ከተንታኞቹ አንዷ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ሪቫ ባህላ በሚባል የኢሜል ስያሜዋ የምትታወቀው፣ የመጀመርያ ደረጃ የመረጃ ምንጮቹ የሊባኖስና የሂዝቦላ የስለላ መዋቅሮችን መጥቀሷ ነው፡፡ በባህላና በኩባንያው መካከል በተከታታይ የተደረጉ የኢሜል ምልልሶች በርካታ ዝርዝሮች ጉዳት የሚያስከትሉ መረጃዎችን ተለዋውጠዋል፡፡ የኢሜል ልውውጦቹ ከሦስት አቅጣጫ የሚመነጩና የተዓማኒነት ደረጃቸው ከከፍተኛ እስከ ዝቅተኛ ደረጃ የሚመደቡ ምንጮች እንዳሉ ይጠቁማል፡፡ በተጨማሪም ለተፈጸመው ሴራ ሦስት መነሻ ምክንያቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ባህላ ግምቷን አስፍራለች፡፡

የመጀመርያው የመረጃ ምንጭ የሊባኖስ ወታደራዊ ስለላ ባልደረባ ሲሆን፣ የሂዝቦላ ሁለተኛው ሰው አውሮፕላኑ ላይ ተሳፍሯል ከሚለው የሐሰት መረጃ በተጨማሪ፣ 20 ያህል የሂዝቦላ ሰላዮች እግረ መንገዳቸውን ወደ ኡጋንዳና ኬንያ ለማቅናት መሳፈራቸውንና ለጊዜው የስለላ ተግባር ላይ ያልነበሩ የሂዝቦላ ወኪሎችም እንደነበሩ ግምቱን አስፍሯል፡፡

‹‹እነዚህ ሰዎች ሂዝቦላ በአሜሪካና በእስራኤል ላይ ለነበረው ዒላማና ኢራን ላይ በሚወሰደው ወታደራዊ ዕርምጃ ላይ ለመሰለል ድርሻ የነበራቸው ናቸው፤›› በማለት ዶሴው አስፍሯል፡፡ የመረጃ ምንጩ እንደሚያምነው የሂዝቦላ ተባባሪ ሰላዮች ከባድ ፈንጂዎችን ወደ ሁለቱ አገሮች ለማስገባት ኢትዮጵያን እንደ መተላለፊያ መስመር ለመጠቀም አስበው ቢሳፈሩም፣ ከጥንቃቄ ጉድለት የተነሳ ፈንጂው አውሮፕላኑ ውስጥ ሊፈነዳ ችሏል፡፡ ይህንን የሚያጠናክረው ሌላኛው መረጃ ደግሞ ከቤይሩት ራፊቅ አል ሐሪሪ ሆስፒታል ዳይሬክተር የተገኘው ሲሆን፣ ተባባሪ ሰላዮቹ ወደ ምሥራቅ አፍሪካ ያመሩ እንደነበር መረጋገጡ ነው፡፡

ዳይሬክተሩ በባህላ እንደተመሰከረላቸው ከፍተኛ እምነት የሚጣልባቸው የመረጃ ምንጭ ሲሆኑ፣ አልማዝ ነጋዴውና ታዋቂው የሊባኖስ ሻይት ሙስሊም ሐሰን ታጅ አል ዲኒም ዕጣ ፈንታው መጋየት በሆነው አውሮፕላን ተሳፍረው እንደነበር መረጃ ሰጥተዋል፡፡ ሰውዬው ወደ ጋቦን ለመምራት በትራንዚት ሲሳፈሩ ከሂዝቦላ ሰላዮች ጋር አብረው እንደነበሩ ሲገለጽ፣ የሴራውን መላ ምቶች ይበልጥ የሚያጠናክር ሆኗል ይላል የዊኪሊክስ መረጃ፡፡

አዲስ አበባ የሂዝቦላ ሰላዮች ትራንዚት ስለመሆኗ በኢሜል ልውውጡ ተደጋግሞ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ተንታኞቹና የመረጃ ምንጮቹ የኢትዮጵያ ፀጥታ ሠራተኞችን በጉቦ አታለው በማለፍ በአገሪቱ ውስጥ ሰርገው እየገቡ ድጋፍ ማግኘታቸው ቀላል እንደነበርም በመረጃው ውስጥ ሰፍሯል፡፡ ‹‹የሂዝቦላ ወኪሎች በአዲስ አበባ የራሳቸው ሰዎች እንዳሏቸው ይታመናል፡፡ እዚያ የፀጥታ ሠራተኞችን በጉቦ ማታለል ከባድ አይደለም፤›› በማለት ባህላ ጽፋለች፡፡ ተንታኟ በሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ራሳቸውን የቤት ሠራተኛ በማስመሰል ለሂዝቦላ ተቀጥረው እንደሚሠሩ ማወቋንም አረጋግጣለች፡፡ ‹‹ሂዝቦላ የቤት ሠራተኛ ተመስለው ከኢትዮጵያ የሄዱ ወሬ አቀባዮችንና ወኪሎችን ይጠቀማል፤›› ብላለች፡፡

ከተጋለጡት የኢሜል መልዕክቶች ውስጥ ቢያንስ 4‚000 ያህሉ ስለዊኪሊክስ መሥራች ጁሊያን አሳንጄ የሚያወሱ ናቸው፡፡ እንደ ዊኪሊክስ ከሆነ፣ ስትራትፎር ራሱ ዊኪሊክስን ለማጥፋት ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በመጨረሻ ግን ስትራትፎር በድረ ገጹ የደንበኞቹ፣ የአጋሮቹና የተጠቃሚዎቹ ግላዊ መረጃዎች ባልታወቁ ሰርጎ ገቦች እንደተደረሰባቸውና ምስጢራዊ መረጃዎችም እንደተሰረቁበት ይፋ አድርጓል፡፡ ስትራትፎር የጂኦፖለቲካዊ ትንታኔዎችን በክፍያ የሚያቀርብ ተቋም ሲሆን፣ የተመሠረተውም በታዋቂው ጸሐፊ ጆርጅ ፍሬድማን እ.ኤ.አ. በ1996 ነበር፡፡

የበረራ ቁጥሩ “ET-409” የነበረውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አደጋን በተመለከተ የመጨረሻው ሪፖርት ባለፈው ዓመት ጥር ወር ይፋ ሲደረግ፣ የአደጋው መንስዔ የአብራሪ ስህተት ነው መባሉን ተከትሎ የኢትየጵያ አየር መንገድ ያለምንም ማቅማማት ሪፖርቱን ውድቅ እንዳደረገው የሚታወስ ነው፡፡ በወቅቱ በደረሰው አደጋ 82 መንገደኞችና ስምንት የአውሮፕላኑ ሠራተኞች መሞታቸው ይታወሳል፡፡

No comments:

Post a Comment