ታስረው የተፈቱት ስዊድናዊ ጋዜጠኞች
ጋዜጠኞቹ ዮሃን ፐርሽንና ማርትን ሽቢይ ከስዊድን ለቪኦኤ እንዴት እንደተያዙ፣ በቀጣይነት ደረሰብን ያሉትን ሰቆቃ፣ የፍርድ ሂደትና የኢትዮጵያ የጸረ-ሽብር ህግና የመናገር መብት ጥሰቶችን አስመልክቶ ዝርዝር ለቪኦኤ መግለጫ ሰጥተዋል።
እንደ ጋዜጠኞቹ አባባል በሰኔ ወር ማብቂያ 2003 ዓ.ም. ሁለቱ ስዊድናዊያን ማለትም የፎቶ ጋዜጠኛው ዮሃን ፐርሽን እና ዘጋቢው ማርትን ሸቢይ በሰሜናዊቷ የሶማሊያ ራስ ገዝ ፑንትላንድ በኩል ድንበር ተሻግረው ወደ ኢትዮጵያ የሶማሊ ክልል አቀኑ። ማርትን ሸቢይ አላማቸው በኦጋዴን ግዛት ያለውን ሁኔታ ለመመልከትና ለመዘገብ እንደነበር ያስረዳል።
“አካባቢውን ለቀው የተሰደዱ ሰዎችን በጎረቤት አገሮች አግኝተን አነጋግረን ነበር፤ ኢትዮጵያን ለቀው የወጡበትን ዘግናኝ ታሪክ በስደተኛ ጣቢያዎች ተገኝተን ዘግበናል፤ ስለዚህ ማጣራት ፈለግን” ይላል ማርትን ሽብይ።
“ከዚሁም ጋር ተያይዞ የስዊድን የሉንዲን የነዳጅ ዘይት ኩባንያ አፍሪካ ኦይል ከሚባል ሌላ ኩባንያ ጋር በኦጋዴን አካባቢ የነዳጅ ዘይት የማፈላለግ ስራ እየጀመረ ስለነበር፤ በዚህም ላይ መዘገብ ፈልገን ነው ወደዚያ የተጓዝንው” ይላል ማርትን፡፡
ኮንትነንት የፎቶ ጆርናሊስት ኤጀንሲ ለሚባል ድርጅት የሚሰሩት የ29 ዓመቱ ዮሃን ፐርሽንና የ30 ዓመቱ ማትን ሽቢይ ከዚህ በፊት በተለያዩ አስቸጋሪና ህይወታቸውን አደጋ ላይ የጣሉ አካባቢዎች እየተዘዋወሩ ዘገባዎችን ሲያቀርቡ ቆይተዋል። ወደ ኢትዮጵያ ከመሻገራቸው በፊት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመተባበር አልሸባብን የሚወጉት አህሉ ሱና ዋጀማዓ የተባሉ ማእከላዊ የሶማሊያ መንግስትን የሚደግፉ ታጣቂዎች ጋር ተገናኝተው ሲዘግቡ ነበር።
የኢትዮጵያ መንግስት ጋዜጠኞች ወደ ሶማሊ ክልል በተለይ ወደ ኦጋዴን እንዲገቡ አይፈቅድም።
ከሶስት አመት በፊት በወጣ ሪፖርት በሶማሊ ክልል የሚደርሱ የመብት ጥሰቶችን፣ የጦር ወንጀልና በሰው ዘር ላይ የሚፈጸሙ ግፎች ያላቸውን ሂውማን ራይትስ ወች ዘርዝሯል። የተቃጠሉ መንደሮችን፣ የተደፈኑ የውሃ ጉድጓዶችን ሁሉ የሳተላይት ምስልን አስደግፎ መረጃውን አቅርቧል።
በዚሁ ተመሳሳይ አመት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ መንግስት ወደ ኦጋዴን የሚላከውን እርዳታ ማገዱን እና አንዳንድ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ስራ እንዲያቆሙ አስታውቋል።
እነዚህ ጋዜጠኞች ታዲያ ይሄንን ሁኔታ ማጣራት ፈለጉ። በአዲስ አበባ በኩል ፈቃድ ስለማይገኝ። እውነት ከሆነ ከራሳቸው ከተጠቂዎቹ ለመስማት በሶማሊያ በኩል ተሻግረው ወደ ኢትዮጵያ ኦጋዴን አቀኑ።
ማርቲን ሸቢይ ስለሁኔታው ሲያብራራ እንዲህ ይላል “ይሄንን ዜና መዘገባችን በጣም አስፈላጊ እንደሆነ በማመን፤ ከህጋዊ መንገድ ውጭ ያሉ አማራጮችን ማሰብ ጀመርን። ለዚህ ነው በሶማሊያ በኩል በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር የተሻገርንው። ሰኔ 20 ቀን 2003 ዓም አመሻሹ ላይ ድንበሩን ተሻግረን ወደ ኢትዮጵያ ገባን። በዚያን ወቅት አብሮን የነበረው አንድ ድንበር አሻጋሪ ሹፌር ነበር”
በመቀጠልም ማርትን እንዲህ ይላል “ሰኔ 20 ቀን በሽላቦ አካባቢ ስንጓዝ ወዲያውኑ ነበር በሁለት የኢትዮጵያ ጦር የወታደር ጂፕ መኪናዎች የታየንው። ድንበሩን ያሻገረን ሹፌር ከወታደሮቹ መኪናዎች አቅጣጫ ቀይሮ አመለጣቸው። ከዚያ ከአማጺያኑ ጋር የምንገናኝበት የቀጠሮ ቦታ ነበረን እዚያ ትቶን ተመለሰ”
ቀጥሎ ስለሆነው ሁኔታ ማርቲን ሲያስረዱ እንዲህ ይላሉ “እኛም ከዚያ ወዲያ ያለው ጉዞ በእግር እንደሆነ ተነግሮን፤ ከአማጺያኑ ጋር ወደ በረሃው የእግር ጉዞ ጀመርን። ለሶስት ቀናብ በእግር ተጓዝን። ሰኔ 23 ቀን ማምሻው ላይ ግን በኢትዮጵያ ጦር ድንገተኛ የደፈጣ ጥቃት ተሰነዘረብን።”
በዚያች የሀሙስ-ምሽት የነበረውን ሁኔታ ያስረዱት የኢትዮጵያ መንግስት ቃል አቀባይ አቶ በረከት ስምዖን የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች ተኩስ ከፍተው 15 የኦብነግ አማጺያንን ገድለው ስድስቱን ሲማርኩ፤ ጋዜጠኞቹም ቆስለው መያዛቸውን ተናግረዋል።
አቶ በረከት ስምዖን በጀሌዎና በሊወርድ የአካባቢው ፖሊስና የጸጥታ ሃይሎች ደረሰ ያሉት ጥቃት በጋዜጠኞቹ እይታ ትክክል ነው ወይ ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ ጋዜጠኞቹ ሲመልሱ እንዲህ ነበር ያሉት፡፡ “አይደለም! በአንዲት ዛፍ ስር ተቀምጠን ትኩስ ሻይ እየጠጣን ነበር። አማጺያኑ ዳቦ ጋግረው ሰጥተውን እየበላን ነበር። አብረውን የነበሩት አንደኛው አስተርጓሚ ነው ሌላ አንድ ሰው ነበር። ከዚያ የማስጠንቀቂያ ተኩስ ተሰማ። ከጥቂት ሰከንዶች በኋላ ወደ 150 የሚሆኑ የኢትዮጵያ ወታደሮችና ልዩ የፖሊስ ሃይል ጥቃት አደረሱብን”
“ወዲያውኑ ሁለታችንም በጥይት ተመታን። የኢትዮጵያ ጦር መጥቶ ሲይዘን አብረውን የተማረኩ ወታደሮች አልነበሩም፤ ወደ ጫካ ሮጠው አመለጧቸው። የተገደለም ሰው አልነበረም” ብለዋል፡፡
አቶ በርከት ስምዖን የገለጿቸው 15 የተገደሉና 6 የተማረኩ የተባሉትም ሰዎች ጋዜጠኞቹ ሲያዙ እንዳልነበሩ ይናገራሉ። ከዚያ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የተላለፈና በፍርድ ቤትም እንደማስረጃ የቀረበ የቪዲዮ ምስልም፤ የሚያሳየው ሁለት ሰዎች ሲማረኩና አንድ የሰነበተ አስከሬን ብቻ ነው።
ስለቪዲዮ ቀረጻው ፎቶ አንሽው ዮሀን ፐርሽን ሲናገር “በቁጥጥር ስር በዋልን በሁለተኛው ቀን። ከኢትዮጵያ የመንግስት ቴሌቪዥን የፊልም አንሽ ቡድን መጥቶ ቃለ-መጠይቅ እናድርግ አሉ። በዚህ አልተስማማንም ነበር። አስራችሁናል፣ ፍርድ ቤት አቅርቡን፣ ጠበቃ ማነጋገር እንሻለን፣ ከአገራችን ኢምባሲም ጋር መነጋገር እንፈልጋለን አልናቸው። ህይወታችሁን ለማዳን ከፈለጋችሁ የምንጠይቃችሁን መልሱ አሉን።” ብሏል።
“በወቅቱ ከሶማሊ ክልል ፕሬዝደንት ጋር ህክምና የሚያገኙበት መንገድ እንዲመቻች በስልክ መጠየቅ ከጀመርን ብንቆይም በወቅቱ የክልሉ ባለስልጣናት ትኩረታቸው የፊልም ስራ ላይ ነበር” ብሏል ማርትን ሽቢይ፡፡
በተጨማሪም በናንተ ዙሪያ በቀረጽንው ቪዲዮ የፊልም ስራ ደስተኞች አይደለንም በሚል ሰበብ በሽሎቦና ዋርደር መካከል ወደሚገኝ በርሃ ተወስደው በዚያ እንደ ሆሊውድ የተቀነባበረ ፊልም መስራት እንደጀመሩ እና በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የታየው ቪዲዮም ይሄንን ሁኔታ የሚያሳይ እንደነበረ ያብራል ማርትን ፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ጋዜጠኞቹን በአደባባይና በሚቆጣጠሯቸው የዜና አውታሮች ወንጀለኛ አድርገው ማቅረባቸው የክሱን ሂደት ተቀባይነት የሌለው ያደርጉታል ሲሉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅቱ ሲ.ፒ.ጄ፣ አምነስቲ፣ ሂውማን ራይትስ ወችና ሌሎችም ተቃውመውታል። በተለይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በፓርላማ ጋዜጠኞቹ ሽብርተኛ ድርጅቶችን ያገዙ ናቸው፤ የጦር መሳሪያ አንግበውም ታይተዋል ሲሉ ማብራሪያ ሰጥተዋል። የመብት ድርጅቶቹ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር አንድ ግለሰብ በፍርድ ቤት ጥፋተኛ ሳይባል ነጻነቱ እንዲታሰብለት የሚደነግገውን ህገመንግስታዊ መብት ይጻረራል፤ የአቶ መለስን ቃልም የሚቀለብስ ፍርድ ቤት አይኖርም በሚል ተቃውመውት ነበር።
ጋዜጠኞቹ ከሶማሊ ክልል ወደ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ ክስ ተመስረተባቸው። በህገወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ በመግባትና አሸባሪ ድርጅቶችን የመርዳት ወንጀሎች እያንዳንዳቸው በስተመጨረሻ የ11ዓመት እስራት ተበየነባቸው።
ስዊድናዊያኑ ለቪኦኤ ሲናገሩ፤ በተለይ በማእከላዊ በታሰሩበት ወቅት፤ ዙሪያቸውን የነበሩት ጋዜጠኞችና የፖለቲካ ተቃዋሚዎች በመሆናቸው፤ ችግሩ ከነሱ ጋር ሳይሆን፤ የትልቅ አፈና አካል መሆናቸውን እንደተገነዘቡ ይዘረዝራሉ።
ከቀረቡባቸው ክሶች በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን አምነው-ጥፋተኛነታቸውን ተቀብለዋል። አሸባሪዎችን በመርዳት ወንጀል ግን፤ ጥፋተኛ አለሆናቸውን ይናገራሉ።
ጋዜጠኞቹ በእስር በቆዩባቸው 14 ወራት መጀመሪያ በማእከላዊ፤ ከዚያ በቃሊቲ ታስረዋል። ስለቃሊቲ እስር ቤት አስከፊ የአያያዝ ሁኔታ እና ስለተመለከቱት የእስረኞች ሰቆቃ አብራርተዋል፡፡
“ዋናው ፈተና በጤና መቆየት ነው። በቅርበት ከምናውቃቸው ታሳሪ ጓዶቻችን ቃሊቲ ታመው የሞቱ አሉ። ስለዚህ ከታመምክ አለቀልህ። ስለዚህ ዋናው ነገር በደምብ መመገብ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዘውተርና እራስን መጠበቅ ነው” ብሏል ማርትን ሽቢይ።
በዚህ ሁኔታ 11 ዓመት በቃሊቲ መቆይት እንደማይችሉ የተገነዘቡት ጋዜጠኞች፤ ከመሞት መሰንበት ብለው የይቅርታ ደብዳቤ መጻፍ መጀመራቸውን ይናገራሉ። የይቅርታ ደብዳቢያቸው አራት ነጥቦች የያዘ ነው።
1ኛ- ተግባራቸው የተሳሳተ እንደነበረ ማመንና በድርጊታቸው መጸጸታቸውን መግለጽ።
2ኛ ከኦብነግ ጋር ያደረጉት ትብብር ስህተት እንደነበረና መጸጸታቸውን።
3ኛ ሃላፊነት፣ ቤተሰብ፣ ወዳጅ ዘመድ ያላቸው መሆናቸውን ተመልክቶ የኢትዮጵያ መንግስት ይቅርታውን እንዲያወርድ መለመን
4ኛ ይሄንን ይቅርታ በጽሁፍና በቃልም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቀርቦ ለመናገር ቃል መግባትን ያካትታል።
ስለ ውሳኔው ፈታኝነት ጋዜጠኞቹ ሲናገሩ “… ምን ለማለት ይቻላል…እጅግ ከባድ ውሳኔ ነው። አስገዳጅ ሁኔታዎች አሉ፤ በቃሊቲ እስር ቤት 11ዓመት አንኖርም፤ የሞት ፍርድ ማለት ነው፤ አስከሬናችን ነበር የሚወጣው። ስለዚህ መወሰን ነበረብን” ብለዋል፡፡
ከእስር ከወጡ በኋላ ጋዜጠኞቹ የሚሰጧቸው አስተያየቶች እንዳሳዘነው የገለጸው የኢትዮጵያ መንግስት በአገሪቱ የተድረገላቸው እንክብካቤ፣ በርህራሄ ይቅርታ ከእስር ተፈተው ሳለ የተሳሳተ መረጃ መስጠታቸው ትልቅ ማጋነንና ይሉኝታ ቢስነት ነው ሲል በዚህ ሳምንት ምላሹን ሰጥቷል።
ካሸባሪዎች ጋር ተባብረው መስራታቸውን አምነዋል ያለው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ምንስቴር መግለጫ፤ ከተፈቱ በኋላ የማናምንበትን ነገር ነው የተናገርንው ማለት “ተራ የጋዜጠኞች ማጋነን” ነው ብሏል።
ሁለቱ ስዊድናዊ ጋዜጠኞች በአሁኑ ወቅት በስቶክሆልም ከቤተሰቦቻቸውና ከስራ ባልደረቦቻቸው ጋር ኑሯቸውን ቀጥለዋል፤ ስራቸውንም እንዲሁ።
ኢትዮጵያ የነዳጅ ዘይትና የአማጺያን ቃለመጠይቅ ፍለጋ መሄዳቸውን አይሸሽጉም። “ዘይት ፍለጋ ሄደን ቀለም አግኝተን መጣን” ብለዋል። ወደፊት ቀለሙን ምን እንደሚያደርጉበትም ወስነዋል። ይጽፋሉ፣ ታሪካቸውን፣ ዘገባቸውን። ከዚያም አልፈው ግን ለአውሮፓ ህብረትና ለዩናይትድ ስቴይትስ መንግስት ባለስልጣናትም መጻፍ ጀምረዋል። “የኢትዮጵያ መንግስት የመናገር ነጻነትን ያክብር! የታሰሩ ጋዜጠኞችን ይፍታ! አፋኙ የጸረ ሽብር ህጉን ይሰርዝ” እያሉ-ይጽፋሉ።
ቃሊቲ ትተዋቸው ለወጡ ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ እስረኞችና በክብር ለተቀበሏቸው ተራ ወንጀለኞችም አይዞህ ወንድሜ
No comments:
Post a Comment