Tuesday, October 16, 2012

ከመለስ በኋላስ ? ፪

(በተመስገን ደሳለኝ)

መስከረም ጠባ፡፡ መስቀል ተተኮሰ፡፡ …ድንገትም ፓርላማው ከእረፍት ወደስብሰባ ለመመለስ ተገደደ፡፡ ህይወታቸው ባለፈው የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር ምትክም ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ‹‹ጠቅላይ ሚንስትር›› ሆነው ቃለ- መሀላ ፈፀሙ፡፡ ይህንንም ተከትሎ ‹‹ተተኪውን›› በተመለከተ ውስጥ ውስጡን ‹‹ሲጎሸም›› የነበረው እና ‹‹ሊሆን ይችላል›› በሚል የተናፈሱ በርካታ መላ-ምቶች ከሸፉ፡፡ ጥቂት የማይባሉ መላ- ምቶች ደግሞ ግባቸውን መቱ፡፡ …እነሆም መለስ ጥለውት የሄዱት ኢህአዴግ እና የአዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር የፖለቲካ ቁመናን በተመለከተ በርካታ መላ ምቶች መመታታቸውን ቀጠሉ፡፡ እኔም በጉዳዩ ላይ ምልከታዬን ለማቅረብ ወደድኩ፡፡

ይኸውም የኃይለማርያም ደሳለኝን ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት መምጣት አንዳች ለውጥ የለውም ብሎ በጭፍን መቃወምንም፣ በጭፍን መደገፍንም የሚመለከት ይሆናል፡፡ ምክንያቱም በግሌ ለውጡ ደካማ ጎን እንዳለው ሁሉ ጠንካራ ጎንም አለው ብዬ ስለማስብ ነው፡፡ ለዚህም እንደ ማሳያ የሚሆኑ አንዳንድ ነገሮችን እንይ፡፡

የለውጡ-ጠንካራ ጎን

የመጀመሪያው ኃይለማርያም ደሳለኝ ወደ ስልጣን በመምጣታቸው ከምንም በላይ ዋጋ ሊሰጠው የሚገባው ሀገሪቱም ሆነች የኢህአዴግ አመራር ከአንድ ሰው ‹‹ብቸኛ ፈላጭ ቆራጭነት›› (Strong man) ነፃ መውጣቱን አመላካች መሆኑ ነው፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው የአቶ መለስ የሃያ አንድ ዓመት የስልጣን ዘመን ሁለት ባህሪያት ነበረው፡፡ የመጀመሪያው ከግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. እስከ 1993 ዓ.ም /የህወሓት ክፍፍል/ ድረስ ያለውን ልናካተው እንችላለን፡፡ በእነዚህ ዓመታት መለስ የሀገሪቱን ፖለቲካ ብቻቸውን አይዘውሩም ነበር፡፡ ወሳኝ ሰውም አልነበሩም፡፡ በግልባጩ ዘመኑ ሊወከል የሚችለው በ‹‹ቡድናዊ አመራር›› (Collective leadership) ነበር፡፡ ይህ ግን መላውን የኢህአዴግ የአመራር አባላት አይመለከትም፡፡ ህወሓትን እንጂ፡፡

 ምክንያቱም መለስ በጋራ ይወስኑ፣ በጋራ ያቅዱ፣ በጋራ ያስፈፅሙ የነበረው ከህወሓት አመራር ጋር ብቻ ነውና፡፡ (በእርግጥ በዛን ዘመን ክንዳቸውን ከህወሓት አመራር ጋር የሚለኩ እንደ በረከት ስምኦን ዓይነት ባለስልጣን እንደነበሩ መካድ አይቻልም፡፡ በረከት በተወሰነ ደረጃ የህወሓት ‹‹የጋራ አመራር›› የስልጣን ንቅፈ-ክበባቸውን እንዳይደፍር ሲገዳደሩ ይታዩ ነበር) ሁለተኛው የአቶ መለስ የስልጣን ዘመን ከህወሓት ክፍፍል (ከ1993 ዓ.ም) በኋላ እስከ ህልፈታቸው ድረስ ያለውን የሚያካልል ነው፡፡ በእነዚህ 11 ዓመታትም መለስ የህወሓትም፣ የኢህአዴግም፣ የሀገሪቱም ብቸኛ ‹‹ፈላጭ ቆራጭ›› ገዥ ነበሩ፡፡ ይህንን ሁኔታ በፍትህ ጋዜጣ ላይ ደጋግመን በመፃፍ ኢህአዴግ የእርምት እርምጃ ይወስድ ዘንድ ብናሳስብም የሚሰማን አልነበረም፡፡ ነገር ግን አቶ መለስ ህይወታቸው ካለፈ በኋላ ሁሉም ባለስልጣናት በሚባል መልኩ መለስ ‹‹ብቸኛው ሰው›› እንደነበሩ እየነገሩን ነው፡፡

ለዚህም ነው ዛሬም ድረስ ‹‹ድርጅታችን ኢህአዴግ ባቀደው፣ በወሰነው… መሰረት›› ከማለት ይልቅ ‹‹መለስ ባስቀመጠልን››፣ ‹‹መለስ ባቀደልን…›› የሚሉ መግለጫዎችን እየሠማን ያለነው፡፡ እናም አሁን በአቶ መለስ ቦታ አቶ ኃይለማርያም መተካታቸው ያንን
‹‹የአንድ ሰው መንፈስ›› ከአራት ኪሎ ስላበረረው ሁሉም ባለስልጣናት ‹‹ራሳቸውን ለማውጣት›› (አቅማቸውን ለማሣየት) የሚጥሩበት ዕድል ተመቻችቷል፡፡ የዚህን አባባል አንድምታ ከተረዳነው አብዛኛው የፖለቲካ አመራር (የስርዓቱ አውራዎች) ‹‹አቻ›› የፖለቲካ ባርኔጣ ማጥለቃቸውን እንገነዘባለን፡፡ ለምሳሌም አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ ኃይለማርያም ደሳለኝን ‹‹ሊያመልኳቸው›› አይችሉም፡፡ ኃይለማርያምም የአባዱላን የስልጣን ድንበር የመዳፈር ዕድላቸው አናሳ ነው፡፡

 ይህን ትንተና ለጠጥ ካደረግነው ደግሞ የፓርላማው አባላትም በአንድ አጀንዳ ላይ አንድ አይነት አቋም በመያዝ ‹‹ከፋብሪካ የወጣ ሳሙና›› ሊሆኑ የማይገደዱበት አጋጣሚ እንደተፈጠረ አድርገን እንወስደዋለን፡፡ ምክንያቱም አረብቦባቸው ከነበረው ‹‹የአንድ ሰው አስገዳጅ›› መንፈስ ተላቀዋልና፡፡ ስለዚህም አንድም የፓርቲያቸው ስራ አስፈፃሚ ወስኖ የሚልክላቸውን በአቶ መለስ ዘመን በተለማመዱት ደረጃ ‹‹ሳያላምጡ ሊውጡ›› (ሊያፀድቁ) ላይችሉ ይችላሉ፡፡ ሁለትም የግንባሩ ስራ አስፈፃሚ ራሱ ከአንድ ሰው ውሳኔ ወደ ሰላሳ ስድስት ሰው ውሳኔ ተሸጋግሯልና የተለያዩ ሃሳቦች የሚንፀባረቁበት ምህዳር ይፈጠራል፡፡ በዚህ አንፃር የሚወሱ ውሳኔዎችም በፓርቲ የሚወሰኑ ይሆናሉ፡፡ ይህንም ‹‹ጥሩ›› ሊባል የሚችል ለውጥ ነው፡፡

ይህ ሁኔታ ጉጉት (ambition) እንዳልሆነ የሚያረጋግጡ አንዳንድ ምልክቶችም እየታዩ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህልም ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የስልጣን ዘመን በፓርቲው ህገ-ደንብ መሰረት ገደብ አልባ አንደነበረ እናስታውሳለን፡፡ በዚህ ምክንያትም አቶ መለስን ያለአንዳች ጭንቀት በአራት የስልጣን ዘመን ልናያቸው ችለናል፡፡ ምንአልባትም ድንገተኛው ህልፈታቸው፣ ድንገት ባይመጣ ኖሮ በ2007ቱም ምርጫ ለአምስተኛ ጊዜ በጠቅላይ ሚኒስትር ወንበራቸው ላይ ሲቀጥሉ ብናያቸው ህግ ጠቅሶ መከራከር አለመቻሉ እውነት ነው፡፡ ሌላው እውነት ደግሞ አቶ መለስ ህይወታቸው አልፎ ተተኪያቸው ከመመረጡ በፊት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የስልጣን ዘመን በሁለት የስልጣን የመቆያ ጊዜያቶች የተገደበ እንዲሆን ፓርቲያቸው ኢህአዴግ መወሰኑ ነው፡፡ ይህ በእሳቸው ዘመን ያልነበረ አዲስ ለውጥ ነው፡፡ (የሁኔታው ምፀት የሚገዝፍብን የፓርቲው አመራር በአቶ መለስ ቀብር ወቅት አቶ መለስ የዴሞክራሲ በር ከፋች ነበሩ፣ ዴሞክራት መሪም ናቸው ሲሉ የነበረውን ስናስታውሰው ነው)

የሆነ ሆኖ ኃይለማርያም ደሳለኝ ‹‹ቃለ-መሀላ›› ፈፅመው የተረከቡት ስልጣን ከፊት ለፊቱ በርካታ ተግዳሮቶች እንደሚጠብቁት ግልፅ ነው፡፡ በብዙ የፖለቲካ ተንታኞች እየተነገረ እንዳለው ‹‹አሻንጉሊት›› ሊሆኑ ይችላሉ ከሚለው ጀምሮ የነባር ታጋዮችን ‹‹እምቢተኝነት›› በምን ሁኔታ ሊያስተናግዱት ይችላሉ የሚለውን እንቆቅልሽ ለመፍታት ወራት ወይም ጥቂት አመታት ሊጠይቅ የሚችል ነው፡፡ አንዳንድ የዋሆች የሰውየውን የትምህርት ዝግጅት ብቻ በማየት አሻንጉሊት ሊሆኑ አይችሉም ይላሉ፡፡ ይህ ግን ስህተት ነው፡፡
 
አሻንጉሊት ለመሆን እና ላለመሆን ወሳኙ ‹‹ዲግሪ›› አይደለም፡፡ የፖለቲካ ስልጣን ነው፡፡ ያ ባይሆን ኖሮማ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በፕሬዝዳንትነት ዘመናቸው የሆኑትን ሁሉ አይሆኑም ነበር፡፡ ምክንያቱም ለምሁራዊ ሰውነትም ሆነ ራስን ችሎ ለመቆም ዶክተሩ የተሻሉ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ እናም ኃይለማሪያም የያዙትን የፖለቲካ ስልጣን የማጠናከር ስልት ቢከተሉ የተሻለ ያዋጣቸዋል፡፡ የግብፅ ፕሬዝዳንት የነበሩትን የአንዋር ሳዳት መንገድ መከተል ይችላሉ፡፡ ሳዳት ገማል አብዱል ናስር ህይወታቸው በማለፉ ነው ወደስልጣን የመጡት፡፡ ሆኖም ሳዳት ተተኪ እንዲሆን በወቅቱ የተመረጡት ‹‹ጭምት እና ትእዛዝ ተቀባይ›› በመሆናቸው ‹‹አሻንጉሊት›› ለማድረግ ባለሙ ጓደኞቻቸው ግፊት ነበር፡፡ የሆነው ግን በግልባጩ ነው፡፡

ምክንያቱም ሳዳት ስልጣን በእጃቸው ገብቶ በዝነኛው የፈርኦኖቹ ቤተ-መንግስት ከተደላደሉ በኋላ በሚገባ ተጠቀሙበት፡፡ እናም ከናስር የበለጠ ጉልቤ ሆኑ፡፡ ይህ ነው የሳዳት መንገድ፤ ሌላ አይደለም፡፡ …አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ስልጣን በመያዛቸው ‹‹በጎ ለውጦች›› ብዬ የጠቀስኳቸው ምልዑ የሚሆኑት ኃይለማርያም በስልጣናቸው ማዘዝ፣ መወሰን እና ተጠያቂ መሆን ሲችሉ ብቻ ነው፡፡

 የለውጡ ደካማ ጎን

እንደ ኢትዮጵያ ባለ ‹‹የህግ የበላይነት›› ባልተረጋገጠበት ሀገር እንዲህ አይነት ለውጥ ሲከሰት ‹‹የዕዝ ሠንሰለቱ›› (Hierarchy) መድከሙ አይቀሬ ነው፡፡ በተለይም በፍርሃት ቆፈን ውስጥ የነበሩ አመራሮች ከፍርሃታቸው ድንገት በመላቀቃቸው ኃላፊነታቸውን መወጣት ወይም የስልጣን ተዋረዱን ጠብቀው ለመሥራት ያለመፈለግን አዝማሚያ ሊያሳዩ ይችላሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ ስርዓት አልበኝነትን (Anarchism) ሊያስከትል መቻሉ አይቀሬ ነው፡፡ ለምሳሌም የስኳር ኮርፕሬሽንን በሚንስትር ማዕረግ የሚመሩት አባይ ፀሐዬ የስራቸውን የቀን ተቀን ሂደት ለኃይለማርያም ደሳለኝ ማቀረቡን ‹‹በትግሉ ዘመን ላልነበረ›› ወይም ‹‹ለተገኘው ስልጣን መስዕዋትነትን›› ላልከፈለ ሰው እንደ መታዘዝ አድርገው ሊወስዱት ይችላሉ፡፡

አይበለውና ይህ አይነቱ አጋጣሚ ቢፈጠር ኃይለማርያም ደሳለኝ ደፍረው ሊጫኗቸው ይችላሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡ የእነዚህ እና መሰል ሁኔታዎች ጥቅል ውጤት ደግሞ መንግሥታዊ ስርዓቱን ያልተረጋጋ ያደርገዋል፡፡ በዚህ መሀልም የተለያዩ ተጣራሽ ፍላጐቶች ያሏቸው ቡድኖች የየራሳቸውን ፍላጐት ለማስጠበቅ ሲሉ የሚወስዱት እርምጃ ሥርዓታዊ መፈራረስን ሊያስከትል ይችላል፡፡ ወይም ደግሞ ቢያንስ ኢህአዴግ የከፉ መንግስታዊ ውሳኔዎችን ጭምር ይወስን በነበረበት ፍጥነት እና ልማታዊ የሚላቸውን ፖሊሲዎቹን በለመዱት ሂደት እንዳይተገብር ሊገታ ይችላል፡፡ እናም ይህ ሁኔታ ‹‹ከፖለቲካው ስንክሳር›› ባሻገር በለውጡ የሚከሰት በጎ ያልሆነ ነገር ሊሆን ይችላል፡፡

የኃይለማርያም-የማርያም መንገድ

ኃይለማርያም ደሳለኝ በኢትዮጵያ ኦሪታዊውም ሆነ አዲሱ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሆኑባቸው መሰረታዊ መለያዎች አሏቸው፡፡ በተለይ ከብሔር እና ከሃይማኖት አንፃር፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ደግሞ ተመልሰው በአስተዳደራቸው ላይ ጥቂት የማይባሉ ተግዳሮቶች የመፍጠር አቅም አላቸው፡፡ በእርግጥም በጠቅላይ ሚንስትሩ ወንበር__ የተቀመጠውን አዲስ ሰው አዲስ ማንነት ለማጎን ከሞከሩ የሚያስነሳው አቧራን መገመት ከቻልን ኃይለማርያም ወደ ስልጣን እንዲመጡ ያመቻቹት ጓዶቻቸው በራሳቸው በኃይለማርያም ላይ ‹‹ለክፉ ቀን›› የሚሆን ቃጭል ማጥለቃቸውን አሊያም ድብቅ መግፍኤ እንዳላቸው መጠርጠር እንችላለን፡፡

 በ1995 ዓ.ም. ኃይለማርያም ደሳለኝ የደቡብ ክልል መስተዳደር ፕሬዝዳንት ሆነው ቢሮአቸውን በአዋሳ ከተማ አድርገው ነበር፡፡ እናስ! በወቅቱ ምን ተፈጠረ? የተፈጠረው የሲዳማ ልሂቃኖች ኃይለማርያም የወላይታ እንጂ የሲዳማ ተወላጅ ባለመሆናቸው የፖለቲካ ጉንተላ ማድረግ ጀመሩ፡፡ አያያዙናም ‹‹የሲዳም ህዝብ ከሶስት ሚሊዮን በላይ በመሆኑ ራሱን ችሎ ክልል ሊሆን ይገባል››፣ ‹‹በቁመታችን ልክ ውክልና አልተሰጠንም›› የሚል ጥያቄ አቀረቡ፡፡ በእነዚህ ጥያቄዎች እና በማዕከላዊ መንግስት ፍላጎት እንዲሁም በወላይታ እና በሲዳማ ተወላጆች መካከል ባለ ቅራኔ ቅርቃር ውስጥ የገቡትን ኃይለማሪያም ‹‹ሊያስተዳድሩን አይገባም›› አሉና ተቃውሞአቸውን አደባባይ በመውጣት ገለፁ፡፡

ያንጊዜም መንግሥት የሀይል እርምጃን ወሰደ፤ በርካታ የሲዳማ ተወላጆችም ህይወታቸው አለፈ፡፡ ሆኖም የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ከመዳከም ይልቅ መስፋት ጀመረ፤ ይህን ጊዜም መንግሥት ደነገጠ፡፡ በድንጋጤም ኃይለማርያም ላይ ‹‹ብቃት ማነስ›› የሚባል ታፔላ ለጠፈና ከቦታቸው እንደተነሱ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ይፋ አስደረገ፡፡ (ምንም እንኳን በሶተኛው ቀን ከኃላፊነታቸው የተነሱበት ምክንያት የብቃት ማነስ እንዳልሆነ ማስተባበያ ቢሰጥም) በኃይለማርያም ቦታም የሲዳማ ተወላጅ የሆኑት ሽፈራው ሽጉጤ ተተኩ፡፡ ይህ እንግዲህ ከዓመታት በኋላ የጠቅላይ ሚንስትሩን ወንበር በመረከባቸው ከጀርባቸው በማድፈጥ ‹‹ሚካኤል ሱሁል››ን (ሚካኤል ስዑል በ18ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ በጎንደር ንጉስ እንጋሽና አውራጅ በመሆን የስልጣን መዘውሩን የያዙ ኃያል ሰው ነበሩ) ለመሆን ለተዘጋጁ ሰዎች ‹‹የመጫወቻ ካርድ›› መሆኑ ነው፡፡

 የተዳፈነውን ‹‹የሲዳማ ፖለቲካ› በማናፈስ (የሲዳማ ልሂቃን ክልል ለመሆን ህግ-መንግስታዊ መስፈርቶችን አሟልተናል እያሉ መከራከራቸውን ልብ ይሏል) የሲዳማን ህዝብ ከኃይለማርያም በተቃራኒ በማቆም ከደኢህዴን ሊቀመንበርነት ማንሳት፡፡ ከዚህ ሀላፊነታቸው ከተነሱ ደግሞ በቀጥታ ከኢህአዴግ ሊቀመንበርነታቸው ይነሳሉ፡፡ ከኢህአዴግ ሊቀመንበርነታቸው ከተነሱ ደግሞ… የሃይማኖት ጉዳይም ቢሆን በቀላል የሚታይ አይደለም፡፡

ምክንያቱም የሀገሪቱ ስልጣን ለዘመናት ከ‹‹ኦርቶዶክሳዊ›› መለዮ ብዙ የራቀ አይደለም፡፡ ሌላው ቀርቶ በኃይማኖት ጉዳይ ‹‹ፀለምተኛ›› የሚባሉት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እንኳ ከሶስት አጋጣሚዎች በላይ በአደባባይ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ፓትርያርክከነበሩት አቡነ ጳውሎስ እጅ መስቀል መሳለማቸው የራሱ የሆነ ፖለቲካዊ አንድምታ አለው፡፡ ዙሩን ይበልጥ የሚያከረው ደግሞ በኃይለማርያም ለመጠቀም ያስባሉ የሚባሉት ብአዴን እና ህወሓት መሰረታቸውም ሆነ ሊያንቀሳቅሷቸው የሚችሏቸው ቡድኖች (Selectorate) የእምነቱ ተከታዮች ከሚበዙበት አካባቢ መሆኑ ነው፡፡ እናም ኃይለማርያም ቀጠሮ ባልተሰጠበት ሰአት ከእንዲህ አይነት ቦታ የሚነሳ ‹‹ሰው-ሰራሽ›› ማጉረምረምን እንዴት መሻገር እንዳለባቸው የቤት ሥራቸው መሆኑ አይቀርም፡፡

ወንዙን የሚያሻግር ጥቂት ምክር

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ምንአልባት ድፍረቱ ካላቸው ከህወሓት እና ብአዴን ‹‹የስልጣን እገታ›› ወደ አርነት የሚመሩ የፖለቲካ መንገድ ማግኘት ላይቸገሩ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ በዋናነት የአጋቾቹ ጉልበት በሰራዊቱ እና በደህንነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን አጢነው ‹‹የጠቅላይ ሚኒስቴር መንበራቸው››ን ስልታዊ ሆነው መጠቀም ከቻሉ ወንዙን ለመሻገር አይቸገሩም፡፡ በአናቱም አቶ መለስ ደህንነቱን እና ሰራዊቱን ሙሉ በሙሉ በግላቸው ከመቆጣጠራቸው በፊት (ከ1983ዓ.ም. -1993 ዓ.ም.) የ‹‹ጉልበተኛ ጓደኞቻቸውን አቅም›› ያፍረከረኩት መንግሥታዊ ስልጣናቸውን በመጠቀም በመሆኑ ከእሳቸው ስልት (ከመለስ አጠገብ ሆኜ ብዙ ተምሬአለሁ እንደሚለት) ትምህርት ወስደው ከሆነ ለብልህነታቸው እና ለአርቆ አሳቢነታቸው አድናቆት አለኝ፡፡

እንዲሁም ሕገ-መንግሥቱን በሚገባ ለመተግበር ከቆረጡም በራሱ በህገ- መንግስቱ ጡንቻቸው ከተገዳዳሪዎቻቸው ሊበረታ የሚችልበትን ዕድል አያጡም፡፡ ይኸውም በህገ መንግሥቱ ‹‹የመከላከያ መርሆች›› በሚል በአንቀጽ 87፣ በቁጥር 1 ላይ፡- ‹‹የሀገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት የብሔሮች የብሔረሰቦች እና የህዝቦችን ሚዛናዊ ተፅዕኖ__ ያካተተ ይሆናል›› የሚለውን ሊጠቀሙበት ይችላሉ፡፡ እናም ይህ አንቀጽ ይከበር ዘንድ ሠራዊቱ የብሔር ተዋፅኦን እንዲጠበቅ ‹‹የመዋቅር ማስተካከያ›› ካደረጉ ከሕገ-መንግሥቱ ይልቅ ለፓርቲ ታማኝ በሆነው ሠራዊት ላይ ድንገት ደርሰው የሀይል ሚዛኑን ማመጣጠን አይከብዳቸውም፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ የተጠቀሰው የህገ-መንግሥቱ አንቀፅም ድጋፍ ይሰጣቸዋል፡፡

በእርግጥ ይህንን ማድረግ ‹‹ራስንም ማደን›› መሆኑ የሚገባን አቶ መለስ ህይወታቸው ካለፈ በኋላ እና ተተኪያቸው ከመመረጡ በፊት በእሽቅድምድም ለ34 ኮሎኔሎች የተሠጠውን የብርጋዴል ጄኔራልነት ማዕረግ ከህጋዊነቱ አንፃር ስናየው ነው፡፡ ምክንያቱም ህገ-መንግሥቱ የጄኔራል ማዕረግ በምን መልኩ ሊሰጥ እንደሚገባው ይደነግጋል፡፡ ‹‹የፕሬዘዳንቱ ሥልጣንና ተግባር›› በሚለው ክፍል አንቀጽ 71 ቁጥር 6 ላይ እንዲህ ይላል፡- ‹‹በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በህግ በተወሰነው መሠረት ከፍተኛ የውትድርና ማዕረጎችን ይሰጣል›› ኃይለማርያም ሊያነሱት የሚችሉት ጥያቄም ‹‹የ34ቱ ጄኔራሎች ሹመት በማን አቅራቢነት የተካሄደ ነው?›› የሚል ይሆናል፡፡ ሆኖም ጠቅላይ ሚንስትሩ የሚጠበቅባቸው ጥያቄ ማንሳት ብቻ ሳይሆን ከሹመቱ አንድምታ ተነስተው በሰራዊቱ ለመጠቀም የሚሞክረው ኃይል ምን ያህል ደፋር እንደሆነ መረዳትም ይኖርባቸዋል፡፡

(በነገራችን ላይ ይህን ሹመት በህወሓት እና በብአዴን መካከል ተከሰተ ከተባለው ከስልጣን ፉክክር ጋር የሚያያይዙት የፖለቲካ ተንታኞች አሉ) ሌላው ኃይለማርያም ስልጣናቸውን ከዕገታ ነፃ ሊያወጡ የሚችሉበት አማራጭ ከፓርቲው ይልቅ (በይበልጥ) መንግሥታዊ ስርዓቱን በመጠቀም ሊሆን ይችላል፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት እጅግ ጠንካራ እና ሚሊተራይዝድ ሆኖ የተዋቀረ ነው፡፡ ይህን የሚያውቅ መሪ ደግሞ ከላይ እስከ ቀበሌ ድረስ ማዘዝ የሚቻልበትን ልማድ በሚገባ ይተገብራል፡፡

ይህን ዓይነቱን መንግሥታዊ መዋቅር የወረሱት አቶ መለስም በ1993ቱ ክፍፍል ወቅት ተገዳዳሪዎቻቸው በፓርቲ ህገ-ደንቦች አጥረው ሊያቆሟቸው ሲሞክሩ እርሳቸው ግን ይህን ተሻግረው መንግስታዊ መዋቅሩን በመጠቀም (ለስዬ ፍርድ ቤትን እንደተጠቀሙት) የሃይል ትንቅንቁን ተሻግረዋል። ኃይለማርያምም ይህን ሊያደርጉ የሚችሉበት ዕድል ሊኖር ይችላል፡፡ እርግጥ ነው ይህን ማድረግ የሚችሉት ጥቂት ዓመታት ሀገሪቷን መምራት ሲችሉ ብቻ ነው፡፡ በእንዲህ አይነት ሁኔታ ወንዙን መሻገር ከቻሉ ደግሞ ገላጣው ሜዳ ላይ ይደርሳሉ፡፡ ተጨማሪ የመለስን ስልትም ያገኛሉ፡፡ መለስ ከዚህ በፊት የውስጣዊ ኃይል መደላደላቸውን ከፓርቲ ፓርቲ ሲቀያይሩ ሚሊተሪውን እና ደህንነቱንም እንዲሁ እያፈራረቁ የተጠቀሙበትን ማለቴ ነው፡፡

በአናቱም ሊጫኗቸው የሚሞክሩትንም እንዲሁ መለስ እንዳደረጉት ‹‹ግራ-ዘመም ጠባብ ብሄርተኞች ናቸው›› የምትል ካርድ ለምዕራባውያኑ ማሳየት ይችላሉ (ምዕራባውያኑ ኃይለማርያምን Pragmatic፣ ነባሮቹን ደግሞ ማቻቻል የማያውቁ ከሚሉት አንፃር) እንግዲህ መጪዎቹ ጊዜያቶች ለኃይለማርያምም ሆነ ለነባር ታጋዮቹ ፈታኝ ይሆናሉ ብሎ መገምት አያስቸግርም፡፡ ከምንም በላይ እንዲህ ዘግይቶም ቢሆን ኢህአዴግ የእኛን የዜጎቹን ድምፅ መስማት ቢጀምር እጅግ የተሻለ እንደሆነም ማስታወስ ያሻል፡፡


                                                                                                                                                                               

No comments:

Post a Comment