Friday, September 6, 2013

በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ችግር አብረን እንፍታ!! ወገናዊ ጥሪ ከግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል

ስለ “ግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል” ምን ያህል ያውቃሉ?
ግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል፣ የሃገር ሉዓላዊነትና የህዝብ የሥልጣን ባለቤትነት የተረጋገጠባት፤ የዜጎች መብቶች፣ ሃገራዊ አንድነት፣ ደህንነትና ጥቅም የተከበሩባት ጠንካራና ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እውን ሆና የማየትን ራዕይ የሰነቀ ድርጅት ነው። የግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል ወያኔንን በኃይል የማስወገድ፤ ሰላማዊና ዲሞክራሲ የሥልጣን ሽግግር በሃገሪቱ እንዲኖር የማስቻል እና ከማንኛዉም የፓለቲካ ድርጅት ጋር ያልወገኑ ነፃ፣ ጠንካራና ብቃት ያላቸው ህገ-መንግሥታዊ የመከላከያ፣ የፓሊስና የደህንነት ተቋማት እንዲኖሩ አስተዋጽዖ የማድረግ ተልዕኮ ይዞ የተነሳ የኢትዮጵያ ሕዝብ አለኝታ ነው። በግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል ውስጥ የተሰባሰብን ዜጎች በደማችን ዉስጥ ያለ የቀደምቶቻችንን የነጻነት ቅርስ ተሸካሚዎች ነንና፣ ባርነትን አማራጭ አድርገን ለመቀበል ከቶውኑ አይቻለንም። ብቸኛው ምርጫ የወያኔን የባርነት ግብዣ በአመጽ መክተን በወያኔ መቃብር ላይ የነጻነትን ሰንደቅ ማውለብለብ ነው።
ዛሬ በሃገራችን በወያኔ አምባገነናዊ እብሪት ያልታፈነ፣ ያልተዋረደና ያልተዘረፈ የሃገሪቱ ዜጋ አይገኝም። የወያኔ ሹማምንት በሃብት ላይ ሃብት፤ በድሎት ላይ ድሎት ሲጨምሩ፣ የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ እጣ ፈንታ ግን መፈናቀል፣ መሰደድ፣ መንገላታት፣ መታሰር፣ መደብደብና መገደል ሆኗል። ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን እንደ ወያኔ ዘመን የተዋረዱበት፣ የተናቁበትና የተበደሉበት ጊዜ የለም። ወያኔ ከሥልጣን ሳይባረር አንዳችም በጎ ለውጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ማሰብ አይቻልም።
የማንኛውም ዜጋ የእኩልነት፣ የፍትህ፣ የነጻነት ጥያቄ ምላሹ ሞትና መታሰር ከሆነ እስከ መቼ ተራ እንጠብቃለን?
ዛሬ የወያኔ ጥቃት ሰለባ ያልሆነ፣ በወረፋው ያልተመታ፣ ያልተገደለ፣ ያልታሰረ፣ ያልተሰደደ፣ ከመኖሪያው ያልተፈናቀለ፣ ከስራው ያልተባረረ የህብረተሰብ ክፍል የለም። ሰራተኛ፣ ምሁራን፣ ገበሬዎች፣ ተማሪ፣ ወዘተ ጥቃት ያልደረሰበት የለም። ጥያቄው ለምን በወረፋ እንደበደባለን? እስከመቼስ ነው ወያኔ የአንዳንዶቻችንን ጥየቄ የሌሎቻችን ማስፈራሪያ እንዲያደርገውና የጥቃት እርምጃውን በየተራ እንዲያፈራረቅብን የምንፈቅድለት? የሚለው ነው።
በኢትዮጵያ ላይ እንደ ሰደድ እሳት እያቃጠለ የህዝቡን ደም እያፈሰሰ፣ እየገደለ፣ እያሰቃየና የፈለገውን እያደረገ ለሃያ ሁለት ዓመታት በሥልጣን ላይ የቆየው ጎሰኛው፣ አምባገነኑና ዘራፊው የህወሃት አገዘዝ ቁንጮ በስልጣን ላይ ቢቆይም ወይም በትረ ስልጣኑን ለሌላ ወያኔ ቢያስተላልፈው፣ አጠቃላዩ የአፈናውና የግፈኛው ሥርዓት ተገርስሶ እስካልወደቀ ደረስ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያመጣው አንዳችም ለውጥ አይኖርም። ሕወሃቶች ከደደቢት በረሃ ተማምለው የመጡበትን ታላቁንና ለብዙ ዘመናት የኖረውን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና አገራዊ አንድነት የማፈራረስና የማዳከም የጥፋት ዓላማቸውን ከሥልጣን እስካልተነቀሉ ድረስ እንደሚቀጥሉበት በሥልጣን ኮርቻ ላይ ከተፈናጠጡበት ጊዜ አንስቶ እየታየ ነው።
የህወሃት ቡድን ከመነሻው አንስቶ እስከአሁን ድረስ ከአርባ ዓመታት በላይ የሰራበትን ወደፊትም ለመቀጠል በዕቅድ ይዞ የሚንቀሳቀስበትን መሠረታዊ የኢትዮጵያን ብሔራዊና አገራዊ አንድነት የማፈራረስ እኩይ ዓላማ ኢትዮጵያዊያን እስካላስቆሙት ድረስ እንደሚቀጥልበት ምንም ዓይነት ብዥታ ሊኖር አይገባም። አንዳንድ የዋሆች የእባቡን የወያኔን ባሕርይ ካለመረዳት “መለስ በሌላ ወያኔ ቢተካ የተሻለ ጊዜ ሊመጣ ይችላል” ብለው ሲናገሩ ይደመጣሉ ነገር ግን እባብ የእባብነት ባህሪውን ምንጊዜም አይለቅም።
የወያኔ/ህውሃት ድርጅት እንደ ድርጅት አምባገነን፣ ጸረ-ዲምክራሲ፣ አፋኝ፣ ጎሰኛ፣የንጹሃን ደም አፍሳሽና ከሁሉም በላይ ጸረ ኢትዮጵያዊ ነው። ስለሆነም የወያኔን ድርጅት እንደ ድርጅትና ሥርዓት ከኢትዮጵያ ህዝብ ጭንቃ ላይ አወርዶ በማፈራረስ በምትኩ ኢትዮጵያዊ የሆነ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት መተካት እንጅአንዱን ወያኔ ከሌላው ወያኔ ጋር በማነጻጸር “እከሌ ከእከሌ ይሻላል» እያሉ ከእውነታው የተለየ ጉንጭ አልፋ ወሬ ማናፈስ፣ ወያኔዎችን መጥቀም እንጅ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ምንም ማለት አይደለም።
የሕዝባችን ችግርና ስቃይ እኛን ካላነቃን፤ ምን ሁኔታ እኛ በጽናት ሊያቆመንና ሊያስተባብረን ይችላል?
ክወያኔ/ሕወሃት ደርዝ የሳቱ የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ይልቅ ሀገራችን በብዙ አንገብጋቢና ያገጠጡ ችግሮች ተተብተባለች። ሕዝባችን በጎጠኝነት የአገዛዝ ቀንበር ስር ይማቅቃል። በየዓመቱ ባስር ሽዎች የሚቆጠሩ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በሕወሃት የተምታታ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ምክንያት ተስፋ አጥተው በስደት ዓለም እየተንከራተቱ ይገኛሉ። በሕወሃት ውስጠ ተንኮል የተነሳም የሀገር ውስጥ ስደተኛው የትየለሌ ሆኗል። ወደድንም ጠላንም ዛሬ በዓለም ፊት ከውርደት በታች ተዋርደን የዓለም መሳቂያዎች ሆነናል። ሕወሃት ግን በኛ ኪሳራ የንግድ ኢምፓየሩን በአፍሪካና በዓለም ደረጃ እያስፋፋ ቀጥሏል። ይህ የሀገራችን ቀውጢ ወቅት እኛን ካላስነሳን፤ ይህ የሕዝባችን ችግር እኛን ካላነቃን፤ ምን በጽናት ሊያቆመንና ሊያስተባብረን ይችላል? ይጠቅማል ባልነው መንገድና ወቅት ሁሉ የሕወሃትን ጎጠኛ አገዛዝ የሚያዳክም የሀገራችንን ሰላምና ጸጥታ የሚያስጠብቅና የሕዝባችንን ጥንካሬና ስነ ልቦና የሚያጠናክሩ እርምጃዎችን እንውሰድ። የኢትዮጵያዊነታችን ክብርና ኩራቱ ሀገራችን ከሕዝቧ ጋር በሰላም ተጠብቃ አስከኖረች ድረስ ብቻ ነው።
የኢትዮጵያ ህዝብ ከቀን ወደቀን ለነጻነቱና ለማንነቱ ሲል የሚያደርገው ትግልና እንቅስቃሴ እንቅልፍ የነሳቸው እና የእግር ዉስጥ እሳት የሆነባቸው ወያኔ/ህወሃቶች፤ የሀገራችንን አንድነት ህልውና እና ማንነት ለማጥፋት፣ ዜጎች ስለመብታቸው እንዳይጠይቁ እየነጣጠሉ እና እየከፋፈሉ በደም የተጨማለቀ እጃቸውን እንደገና በደም እያለቀለቁ ስለሃይማኖታቸው ነጻነት፣ ስለፍትህ እጦት፣ ስለዲሞክራሲ እጦት  የጮኹ አንደበቶችን በጥይት ሲዘጉ ማየት የተለመደ ነው።
ተቻችለንና ተከባብረን የኖርን ኢትዮጵያውያን ለወያኔ ከፋፍለህ ግዛዉ ፖሊሲ መመቸት የለብንም። በደስታና በሀዘን ሳንለያይ የዘለቀውን አንድነታችን አሁን በዚህ አስከፊና ጨካኝ ወያኔያዊ ድርጊት አዝነን ከንፈራችንን ለሞቱት እና ለታሰሩት በመምጠጥ አይደለም ቁጭታችንና ሀዘናችን መግለጽ ያለብን። ለተጠቁ ወገኖቻችን መከታና ጋሻ በመሆን ቁስላቸው ቁስላችን፣ ደማቸው ደማችን፣ ሀዘናቸው ሀዘናችን፣ በመሆኑ ነገ በኔ በማለት ሁሉንም የትግል ስልቶች ተጠቅመን ጎሳ ቋንቋና ሃይማኖት ሳይለያየን ከወያኔ ግፍ አገዛዝ ለመላቀቅ ሁላችንም በአንድነት በወያኔ ላይ እንነሳ ነው የወቅቱ ጥሪ!!
በአሁኑ ሰአት ግንቦት 7 ህዝባዊ ሃይል ለአገራችንና ህዝቧ ትልቅ ደወል ደውሏል። ይህም የነጻነት ደውል ነዉ:: በዚህም የነፃነት ጉዞ በመሳተፍና በመርዳት ለተደወለው ደውል መልስ መስጠት ያስፈልጋል። ግዜውም አሁን ነው!! የዘረኛው አገዛዝ ክዚህ በላይ ጊዜ ከተሰጠው የሚያደርሰውን ጉዳት ለመመለስ የማይቻል ነዉና።
ኢትዮጵያ አገራችንና ሁሉንም የሃገሪቱን ዜጋ ከዘረኛውና ከአምባገነን አገዛዝ ነፃ የማውጣትና ፍትህ፣ ነፃነት፣ ዲሞክራሲና እኩልነት የሰፈኑባት ሃገር የመገንባት ከፍተኛ ኃላፊነት በእኛ ትውልድ ላይ የወደቀ መሆኑን “የግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል”ተረድቷል፤ ይህ በመሆኑም ህይወታችንን፣ ንብረታችንና ጊዜዓችን ለትግሉ ለማዋል ቆርጠን መነሳት እንደሚኖርብን ጥሪዉን አስተላልፏል፤ በዲሞክራሲያዊ ሥርዓትና በኢትዮጵያ አንድነት ከሚያምኑ የፓለቲካ ድርጅቶችና ሲቪክ ማኅበራት ጋር በጋራ ለመሥራት እየተደረገ ያለውን ጥረት ማጠናከር ያለብን መሆኑን ተረድቷል፤ ድርጅቱን በማጠናከር የወያኔን ግብዓተ-መሬት ለማፋጠን በቁርጠኝነት ተነስቷል።
ኢትዮጵያ አገራችን በታሪኳ አጋጥሟት በማያውቅ የጠላት እጅ ውስጥ ወድቃለች። አገሪቷ ተከፋፍላ፤ ህዝቧ እርስ በርሱ ተቆራቁሶ፤ ለም መሬቷ የባዕዳን ቱጃሮች መፈንጫ ሆኖ ኢትዮጵያዊያን በገዛ አገራችን ባርነትን እንኳን የምናገኝበት እድል የሌለ በመሆኑ ይህ ዘረኛና ዘራፊ አገዛዝ ጊዜ ሳይሰጠው እንዲወገድ ሁላችንም በጋራ መነሳት እንዳለብን መገንዘብ ይኖርብናል።
ኢትዮጵያ ለዘለአለም በአንድነቷ ጸንታ ትኑር!!
ዛሬ ነገ ሳትሉ የግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይላችንን ተቀላቀሉ።
“የግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል” ለኢትዮጵያና ሕዝቦቿ መልካም ራዕይ አንግቦ የተነሳ ሠራዊት በተቻለ ሁሉ መደገፍና ደጀንነታችንን ማረጋገጥ የውዴታ ግዴታችን መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል!
ለነፃነት ታግሎ ነፃነት ማግኘት ከተጠያቂነት መዳን ነው።
“የግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል” ሀገራዊ ጥሪ በመርዳት የታሪክ ተዋናኝ በመሆን ታሪክ የማይሽረው አሻራ እናስቀምጥ!!!
ግፍ ይብቃን ካልን፣ውርደት ይብቃ ካልን፣ስደት ይብቃ ካልን፣እስራት ይብቃ ካልን  ለግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል ሀገራዊ ጥሪ አስቸኳይ መልስ በመስጠት ለወገን አለኝታነታችንን እናረጋግጥ!!!
በኖርዌይ የግንቦት 7 ህዝባዊ ሃይል ድጋፍ አሰባሳቢ ጊዜያዊ ኮሚቴ

No comments:

Post a Comment