Friday, April 20, 2012

ዲያስፖራው ለአባይ ግድብ ግንባታ ያሳየው ተነሳሽነት መንግስትን ማሳዘኑ ታወቀ

ሚያዚያ ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሰሞኑን ይፋ ባወጣው መረጃ መሰረት በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለአባይ ግድብ ግንባታ ያሳዩት ተነሳሽነት ዝቀተኛ መሆን፣ መንግስትን በእጅጉ ያበሳጨ ጉዳይ ሆኗል በማለት ዘጋቢያችን ከአዲስ አበባ መልእክቱን አስተላልፎአል። መንግስት ለግንባታው የሚውለውን አብዛኛውን የውጭ ምንዛሬ ከዲያስፖራው ለመሰብሰብ አቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ ዲያስፖራው እስከ ዛሬ ያዋጣው ገንዘብ ከ7 ሚሊዮን ዶላር በታች መሆን መንግስት በዲያስፖራው ላይ የነበረውን እምነት እንዲያጣ አድርጎታል። አንድ የውጭ ጉዳይ ሰራተኛ ” ዘ ጋቨርመንት ኢዝ ፒስድ ኦፍ” በማለት የመንግስትን ስሜት ለማንጸባረቅ መሞከሩን የደረሰን ዜና ያመለክታል ።
መንግስት ለዲያስፖራው ምላሽ መቀዝቀዝ ተጠያቂ ያደረገው የተቃዋሚ ሀይሎችን ሲሆን፣ ኢሳት ቴሌቪዥን፣ ግንቦት7 ፣  የአሜሪካ ድምጽ፣ እንዲሁም ከድረገጽ ኢትዮሚዲያ፣  ከፓልቶክ ወቅታዊ የመወያያ መድረክ አፍራሽ ሚና መጫወታቸውን የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሰራተኛው ለዘጋቢአችን ቃል በቃል ተናግሯል።
የአባይ ግንባታ ኮሚቴ ከውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ጋር በመተባበር የፋሲካ በአልን ምክንያት በማድረግ ወደ አገራቸው የገቡ ኢትዮጵያውያንን ለማወያየት ማቀዱም ተስምቷል።
በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ በአገር ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም በአባይ ግንባታ ዙሪያ የሚያሳዩት የስሜት መቀዛቀዝ መንግስትን ያስደነገጠው ጉዳይ ሆኗል። አቶ መለስ ዜናዊ ከአመት በፊት መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ በማስተባበር ግድቡን እንደሚጨርሱት ተናግረው የነበረ ቢሆንም፣ ከአመት በሁዋላ ኢትዮጵያዊያን ከ15 እስከ 20 በመቶ የሚሆነውን ወጪ ከሸፈኑ እንደ ትልቅ ስኬት እናየዋለን በማለት፣ በተዘዋዋሪ መንገድ በህዝቡ ምላሽ አለመርካታቸውን መግለጻቸው ይታወሳል። በርካታ ኢትዮጵያውያን አባይ አፈራችንን ብቻ ሳይሆን ኪሳችንን ጭምር ጠራርጎ እየወሰደው ነው በማለት ስሜታቸውን ሲገልጹ ይሰማል።
በአማራ ክልል የሚገኙ አርሶአደሮች ለአባይ ግድብ ቦንድ እንዲገዙ መገደዳቸው ከኢህአዴግ ካድሬዎች ጋር እያላተማቸው እንደሚገኝ መዘገባችን ይታወሳል። ብአዴን የአማራ አርሶ አደሮች እስከ ያዝነው ወር መጨረሻ ድረስ የ1 ቢሊዮን ብር ቦንድ መግዛት አለባቸው የሚል መመሪያ አውርዷል። መመሪያውን ተግባራዊ ለማድረግ የተንቀሳቀሱት ካድሬዎች ከገበሬው ያገኙት ምላሽ አሉታዊ በመሆኑ፣ ገበሬውን ማስፈራራት መጀመራቸውን ነው ደረሱን መረጃዎች የሚያመለክቱት።

No comments:

Post a Comment