Friday, December 21, 2012

መጪውን እሑድ - ከቅዳሴ በኋላ “ከፓትርያርክ ምርጫ ዕርቅና ሰላም ይቅደም” የምንልበት ቀን ስለማድረግ



(ደጀ ሰላም ታኅሣሥ 12/2005 ዓ.ም፤ ዲሴምበር 21/2012/ READ IN PDF)፦ ቤተ ክርስቲያናችን በመስቀልያ መንገድ ላይ እንድትቆም ያደረጉ ዋነኛዎቹ ርዕሰ ጉዳዮች ሁለት ናቸው። የመጀመሪያው ለ20 ዓመታት በውግዘት የተለያዩ አባቶች አንድ እንዲሆኑ፣ አንዲት ቤተ ክርስቲያን፣ አንድ አስተዳደር፣ አንድ ቅ/ሲኖዶስ እንዲኖረን ለማድረግ ያልቻልነው ለምንድነው? የሚለው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ 20 ዓመት ለቆየው የአባቶች በውግዘት መለያየት ዓምድና ምልክት የነበረው የፕትርክናው ሥልጣን ጉዳይ ነው።


እንደ እግዚአብሔር ፈቃድም ይህ ልዩነቱ ሊፈታ የሚችልበት ጭላንጭል ታይቶ ነበር። ነገር ግን ይህንን የተስፋ ጭላንጭል በሚያዳፍን መልኩ በጥቂት የቅ/ሲኖዶስ አባላት ግፊት 6ኛ ፓትርያርክ ለመሾም “አስመራጭ ኮሚቴ” ተቋቁሟል። “የቤተ ክርስቲያኔ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ ምእመናን በሙሉ ውሳኔውን በጽኑዕ በመቃወም ላይ ይገኛሉ። ይህንን “ከኮምፒውተር ጀርባ”ና በስልክ የሚደረግ የኢንተርኔት ተቃውሞ መልክ ለመስጠት በመጪው እሑድ፣ ቅዳሴ ካለቀ በኋላ በየአጥቢያችን በመሰባሰብ ይህንን ሐዘናችንንና መከፋታችንን እንዲሁም በውሳኔው ማዘናችንን ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ለመግለጽ መሰባሰብ ይኖርብናል።

ሰንበት ት/ቤቶች፣ ማኅበራት፣ ሰንበቴዎች እና ምእመናን በሙሉ ከሚያውቋቸው ሰዎች በመጀመር ለእሑዱ ቀጠሮ መያዝ እና የመሰባሰቡን ሁናቴ መልክ መስጠት መጀመር ይኖርባቸዋል። ዓላማችን አንድ ነው። እርሱም “ሃይማኖታችንን እና ሃይማኖታችንን ብቻ የተመለከተ ነው”። ስብስባችንን የሚጠሉ ሰዎች በፖለቲካ በማሳበብ በመንግሥት ዱላ ለማስደብደብ የሚያደርጉት ሙከራ እንደሚኖር ስለምናውቅ ከወዲሁ ለሚመለከተው ሁሉ ዓላማችንን መግለጽ እንፈልጋለን። መነጋገር የምንፈልገው ከቅ/ሲኖዶስ አባላት ብፁዓን አባቶች ጋር ነው። ይህንን በተመለከተ ሁላችሁም ሐሳባችሁን በመጨመርና በማስፋፋት መልክ ትሰጡት ዘንድ ደጀ ሰላም በትህትና ጥሪዋን ታቀርባለች።

ይህንን ፍፁም ሃይማኖታዊ ጥያቄ ሌላ መልክ ለመስጠት፣ ኢሕአዴግ ላይ የተነሣ ሰላማዊ ሰልፍ ለማስመሰል የሚሞክሩትን በግልጽ ከወዲሁ መልስ ልንሰጣቸው ያስፈልጋል። በሃይማኖት ስም ፖለቲካ አንነግደም። ፖለቲካውን በራሱ በፖለቲካነቱ የማራመድ ሙሉ ኢትዮጵያዊ መብት አለን። በዜግነታችን እርሱን በቦታው ማድረግ እንችላለን። አሁን የምንጠይቀው ጥያቄ ሃይማኖታዊ ነው፤ ማቅረብም የምንፈልገው ለቅ/ሲኖዶስ ነው ማለት ይገባናል።

እስካሁን ባየነው፣ ክርስቲያኑ ማንኛውንም ጥያቄ ለማንሣት ሲነሣ “በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ” ጭንቅላት ጭንቅላቱን በማለት ክርስቲያኑ እንዳይተባበር፣ እንዳይሰባሰብ፣ እንዳያውቅ፣ እንዳይጠይቅ የሚያደርጉ የተደራጁ ክፍሎች እንዳሉ ደጀ ሰላም ለማሳሰብ ትፈልጋለች። እነዚህ ሰዎች ፌስቡክን በመሳሰሉ ቦታዎች በመበተን ለሁሉም የክርስቲያኑ ጥያቄ የተጣመመ ሃይማኖት ቀመስ ማብራሪያ በመስጠት የሰዉን አፍ ያስዘጋሉ።

ለምሳሌ በተደጋጋሚ ከሚያነሷቸው አስተያየቶች አንዱ “ዋናው ጸሎት ነው፤ ሌላ ምንም ነገር አያስፈልግም” የሚል ነው። ጸሎት የሁሉ ነገር መጀመሪያና መጨረሻ ነው። ወሳኝ ነው። በጸሎት የማይለወጥ ነገር የለም። የኤርትራ ባሕር የተከፈለው፣ የኢያሪኮ ግንብ የፈረሰው፣ የአናብስት አፍ የተዘጋው ወዘተ በጸሎት ነው። ነገር ግን ጸሎት ያለ ሥራ/ምግባር ብቻውን አልነበረም። ሙሴ ከግብጽ እስከ ከነዓን ተጉዟል፣ ኢያሱ ኢያሪኮን ግንብ እየዞረ እንጂ ቁጭ ብሎ አልጮኸም፣ ዳንኤል ቀን ከሌሊት ወደ እግዚአብሔር ተማጠነ፤ ጉድጓዱ ከለከለው እንጂ። ስለዚህ “ጸሎት ብቻ” በሚል የክርስቲያኑን ልብ ከሥራ የሚያቀዘቅዙትን ልንነቃባቸው ይገባል።

ከዚህም በላይ የክርስቲያኑ ጥያቄ “አመጽ” የሆነ ይመስል ክርስቲያን አያምጽም በሚል ለማቀዝቀዝ ይፈልጋሉ። አመጽ የሰይጣን ነው። ነገር ግን ክፉ ነገርን መቃወም ግዴታችን ነው። ሰው ባንጎዳም ራሳችን ለሰማዕትነት ለማቅረብ ማን ይከለክለናል። “እክህደከ ሰይጣን” ብለን እንነሳለን። የተጣመመ ሃይማኖታዊ ትምህርት የምታስተምሩትን ነቅተንባችኋል እንላችኋለን።

እስከ እሑድ ባለው ጊዜ ለመነሻ እንዲሆን ይህንን ለማድረግ እንሞክር፦  
  • መረጃውን ለመላው ሕዝበ ክርስቲያን እናድርስ፣ (በስልክ የኤስ.ኤም.ኤስ መልእክቶች፣ በፌስቡክ፣ በትዊተር)፣
  • ዜናውን ለመገናኛ ብዙኃን እናድርስ፣
  • ብፁዓን አባቶችን በስልክም በአካልም በመቅረብ ስለ ጉዳዩ ማነጋገር፣ በውሳኔው እንደማንስማማ እናሳውቅ፣
  • ጉዳያችን እና ዓላማችን “ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳ” ሳይሆን የቤተ ክርስቲያናችን አባት የመምረጥ ጉዳይ መሆኑን ለሚመለከታቸው አካላት አለ ፍርሃትና ያለ ሥጋት እንግለጽ፣
  • ከመንግሥት አካላት የተደበቀ የመሥራት ፍላጎት እንደሌለን ከወዲሁ በተደጋጋሚ እንግለጽ፣
  • በአገር ውስጥ ያሉ ጋዜጦችና መጽሔቶች ለጉዳዩ ሽፋን እንዲሰጡት እናበረታታ፣
  • የውጪ አገር ኢትዮጵያውያን ሚዲያዎችም በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ በሚል በዚሁ ሰበብ ኢሕአዴግን ለመተቸት ሳይሆን ጉዳዩን ለክርስቲያኑ ሕዝብ በማይጎረብት መልክ እንዲያቀርቡት እናግዝ፣
  • ኦርቶዶክሳውያን ጡመራ መድረኮችም ዜናዎችን በትብብርና በኅብረት ለምእመኑ እናድርስ፣
  • እሑድን ለቤተ ክርስቲያን ጥያቄ ማቅረብ የምንጀምርበት የመጀመሪያው ቀን እናድርገው።

No comments:

Post a Comment