(ደጀ ሰላም ታኅሣሥ 1/2005 ዓ.ም፤ ዲሴምበር 10/2012/ READ THIS NEWS IN PDF)፦ ከኅዳር26 እስከ 30 (ዲሴምበር 5-9/2012) በሰሜን አሜሪካ ዳላስ ቴክሳስ ከተማ ሲካሄድ የሰነበተውበኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል የተፈጠረውን ልዩነት ለመፍታትየተደረገው ሦስተኛ ዙር የዕርቅ ድርድር ትናንት እሑድ መግለጫ በማውጣት እና ለሌላ ጉባዔ ቀነ ቀጠሮ በመስጠት ተጠናቋል። በመግባባት፣ በመከባበር እና በመደማመጥ ተደርጓል በተባለው በዚህ በአባቶች ውይይት ከቀደሙት ሁለት ጉባዔያት በተሻለ “ተስፋ ሰጪ” የአንድነት ምልክቶች የታዩበት መሆኑን ብዙዎች እየመሰከሩ ነው። ሙሉ መግለጫው በዳላስ ደ/ም/ቅ/ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በምዕመናን ፊት በተነበበበት ወቅት ከሁለቱ ወገን የመጡ ልዑካን ኮፒውን በእጃቸው ይዘው ታይቷል።
በዕለቱ የተነበበው መግለጫ በዋነኝነት በሚከተሉት ነጥቦች ላይ ሐሳብ ሰጥቶ ያለፈ ሲሆን እኛም እንደሚከተለው ጨምቀን እኛም አቅርበነዋል።
- መለያየቱ ሁሉንም ወገን በእጅጉ ያሳዘነ እንደመሆኑ ቀጣይ አራተኛ ጉባዔ እንዲካሄድ፣
- አራተኛው ፓትርያርክ ወደ አገራቸው ስለሚመለሱበት ሁኔታ በሁለቱም ወገን የቀረቡት ሐሳቦች በሁለቱም በኩል ባሉ ምልዓተ ጉባዔዎች ታይተው ወደ ውሳኔ እንዲደረስ፣
- የቤተ ክርስቲያኑን ሰላምና አንድነት ለሚናፍቀውና ውጤቱንም በጉጉት ለሚጠባበቀው ሕዝባችን የሚፈለገውን ውጤት ማስገኘት እንዲቻል ሁሉም ወገን የበኩሉን በጎ ድርሻ እንዲጫወት አደራ፣
- የሰላሙ ጥረት ከፍጻሜ እስከሚደርስ ድረስ ሁለቱም ወገን ለሰላሙ ዕንቅፋት ሊሆን የሚችል ማንኛውንም ነገር ከመሥራት እንዲቆጠቡና ውጤቱን በትዕግስት እንዲጠብቁ፣
- ይህንን ታላቅ የዕርቅ ሒደት ለማሳካት አላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኘውና የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ን የሰላምና አንድነት ጉባዔ ማመስገን፣
- የሰላምና የአንድነት ጉባዔው ባቀረበው ሐሳብ መሠረት ቀጣዩና አራተኛው ጉባዔ ከጥር 16-18/2005 ዓ.ም (ጃኑ. 24-26/2012) በሎስ አንጀለስ ካሊፎርኒያ እንዲካሔድ፤ ከሰላም ጉባዔው ወደ ሁለቱም ተወያይ ወገኖች ምልዓተ ጉባዔዎች ልዑካን እንዲላኩና ስለተደረሰበት የውይይት ሁናቴ ማብራሪያ እንዲሰጡ ተስማምተዋል።
- ይህ ጉባዔ ተጀምሮ እስኪፈጸም ድረስ በጸሎታቸው፣ በገንዘባቸው፣ በዕውቀታቸውና በጉልበታቸው የተባበሩትን የዳላስ ከተማና አካባቢውን ማኅበረ ካህናትንና ምእመናንን እንዲሁም የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችን አመስግነዋል።
- አንዳንድ መገናኛ ብዙኃን ስዚህ ተስፋ ሰጪ ውይይት በሚያቀርቡት አሉታዊ ዘገባ ምክንያት ምእመናን እንዳይረበሹ የሚሉት ይገኙባቸዋል።
ስለ ዕርቅ ሰላሙ የተሰማጨውን ሐሳብ እንዲያሰሙ ዕድል የተሰጣቸው የሰላምና የአንድነቱ ጉባዔ አባላት በበኩላቸው “የጥል ግርግዳው አልፈረሰም፣ ነገር ግን ተነቃንቋል”፤ እንዲሁም “የ20 ዓመት ችግር በአንድ ጊዜ ሊቀረፍ አይችልም ነገር ግን በትዕግስት ሁሉም ይፈታል”፤ “የሰይጣን ልቡ ተወግቷል ነገር ግን አልሞተም” የሚሉ አስተያየቶችን ሰጥተዋል።
ስለዚህ ታሪካዊ ጉባዔ አንዳንድ አስተያቶችና ቀጣይ ምልከታዎች በተመለከተ ደጀ ሰላም በሰፊው እንደምትመለስበት በማስታወስ የተስፋ፣ የአንድነትና የዕርቅ በር እንዲከፈት የጣሩትን ወገኖች ከልብ ታመሰግናለች።
“ጸልዩ በእንተ ሰላመ ቤተ ክርስቲያን - ስለ ቤተ ክርስቲያን ሰላም ጸልዩ”።
No comments:
Post a Comment