Thursday, June 21, 2012

በፍርድ ቤት ዳኞች ቁጣ ሕብረተሰቡ መማረሩ ተገለፀ


  • በፍርድ ቤት ዳኞች ቁጣ ሕብረተሰቡ መማረሩ ተገለፀ

    ሰኔ አስራ አራት ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
    ኢሳት ዜና:- በአገራችን በሚገኙ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ውስጥ የተሰየሙ ዳኞች በባለጉዳዮች ላይ በሚያሰሙት ቁጣና ሃይለ ቃል በመረበሽ ባለጉዳዮች በችሎት ውስጥ ባግባቡ ሃሳባቸውን ባግባቡ ሳይገልፁ መመለሳቸው እውነት መሆኑን የጠቅላይ ፍ/ቤቱ ፕሬዚዳንት አመኑ።
    እንደ ሪፖርተር ዘገባ፤- ከትናንት በስቲያ በፓርላማው ተገኝተው የ2004 ዓመት ሪፖርት ያቀረቡት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ተገኔ ጌታነህ፤ ይህንኑ አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ “የፍርድ ቤቶች ዳኞች የሕዝብ አገልጋዮች መሆናቸውን ተገንዝበው ኅብረተሰቡ የሚፈልገውን አ...ገልግሎት በመስጠት ፋንታ መቆጣታቸው አግባብነት የጐደለው ድርጊት መሆኑን በመግለጽ መታረም እንዳለበት ገልፀዋል።
    በቅርቡ የፀረ-ሙስና ኮሚሽን በአንድ የውጭ አገር ድርጅት አማካኝነት ያስጠናው ጥናት እንደሚጠቁመው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በሕዝብ አመኔታ ከማይጣልባቸው መንግስታዊ ተቋማት ውስጥ ፍርድ ቤቶችን በመጀመሪያው ረድፍ ላይ እንደሚገኙ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። ይህንኑ በመንተራስ በፓርላማው ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይና የአንድነት ፓርቲ ም/ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ በበኩላቸው ‹‹እምነት የማይጣልበትን ተቋም መምራትን እንዴት ያዩታል? ይህንን የተዓማኒነት ጉድለት ለማሻሻል ምን እየተደረገ ነው? የዳኝነት ሥርዓቱስ ምን ያህል ነፃ ነው?›› የሚሉ ጥያቄዎችን ለፕሬዚዳንቱ አቅርበው፣ አቶ ተገኔ ጌታነህ “ጥናቱ ያለውን እውነታ ያሳያል ብለን አናምንም” በማለት በፍርድ ቤቶች የሚከፈቱ ፋይሎች እየጨመሩ መምጣታቸው ሕዝቡ በፍርድ ቤቶች ላይ ያለውን እምነት ያሳያል” በማለት ለማስተባበል ሞክረዋል።
    ምንም እንኳን በአዋጅ ቁጥር 24/88 አንቀጽ 8/2 ላይ «ማንኛውም ሰው፤ በመንግሥት ሕግ አውጭ፤ ወይም አስፈፃሚ ውስጥ ወይም በማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት በአባልነት በሚያገለግልበት ጊዜ፤ አጣምሮ የዳኝነት ስራ ሊሰራ አይችልም።» በማለት ቢደነግግም፣ ከ7 ዓመት በፊት በአገራችን የተደረገ ጥናት ግን እንደሚጠቁመው፣ በኢትዮጵያ ከሚገኙት ዳኞች ከ82% በላይ የሚሆኑት የኢህአዴግ አባላት ብቻ ከሚሰለጥኑበትና፣ በማህበረሰባችን ዘንድ “ድንጋይ ማምረቻ” በመባል ከሚታወቀው ከሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ የሚወጡ የአገዛዙ ካድሬዎች ሲሆኑ ከነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ ከዚያ በፊት በሕግ ስራ ምንም አይነት ልምድ የሌላቸው መሆኑን ይጠቁማል ሲል ቅዱስ ሀብት በላቸው ዘግቧል

No comments:

Post a Comment