Thursday, May 3, 2012


ኢትዮጵያዊ ዲያስፖራ ሲፈተሽና ሲጋለጥ

በአለማችን በቀደምት ታሪካቸው ከሚታወቁት አምስት ሃገሮች መካከል አንድዋ ኢትዮጵያ ናት:: ኢትዮጵያ በራስዋ ታሪክ ወግና
ባህል ስትኩራራና ስትመጻደቅ ይሕው ከ 3,000 ዘመን በላይ አስቆጠረች::
ኢትዮጵያኖች በሰፊው ከምንኩርራባቸው ዋና ዋናወቹ የራስ ፊደልና ቋንቋ ፥ ታሪካዊ ሃውልቶች ፥ የክርስትናና እስልምና
እምነቶችን ተቀብለን የባህልችን አካል ያደረግን ፥ ቅኝ ግዛትን አፈርድሜ ያገባን ፥ በውበታችንና በባህላችን ስብጥርነት የምንኮራ
፥ የሃገር አንድነትን ለበዙ ዘመናት የጠበቅን፥ የህግ የበላይነትን ጠንቅቀን የተረዳን ወዘተ ይገኙበታል:: እነኝህ ኩራቶች ግን
ከታሪክነት አልፈው ዳቦ አልባሳትና መጠለያ ሊሆኑን አልቻሉም::
ሊቃውንት እንደሚሉት ከሆነ በጥሩ ታሪክ ላይ የተገነባ ማህበረሰብና ሃገር ለፖለቲካዊ፥ ኢኮኖሚያዊና ሕብረሰባዊ እድገት
የተዘጋጀ ሊሆን ይገባዋል ይሉናል:: በእኛ ሃገር ሁኔታ ግን ይህ መላምትና አስተሳሰብ በተቃራኒው ያለ ይመስላል::
የሀገራችን ስልጣኔና እድገት በአስከፊ ሁኔታ እንደግመል ሽንት ወደ ሗዋላ የሚሂድ፥ ተሻለ ሲባል ደግሞ እንደ ውታደር እርግጫ
ባላበት የሚረግጥ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም:: ለዚህ ሁሉ ችግር ተጠያቂው ማነው ያልን እንደሆነ መልሱ እኛ ይሆናል::
ምክኒያቶችስ ምን ሊሆኑ ይችላሉ ለሚሉት ግን መልሱ እንደዚህ ቀላል አይሆንም:: ይህን ከባድ ጥያቄ ለመመለስ ራሱን የቻለ የስነ
ማህበር፥ የስነ ፖለቲካ ፥ የስነ ኢኮኖሚ ምርምርና ጥናት ያስፈልገዋል:: መጠናትም አለበት:: ለምን ያልን እንደሆነ በሽታው
ካልታወቀ መፍትሔውን ማግኘት ያስቸግራል እና ነው:: ምርምሩና ጥናቱ እስኪደረግ ግን ተጨባጩን ሁኔታ በመዳሰስ መሰረታዊ
የሆኑትን መተንተን ይቻል ይሆናል:: ከሁሉ መቅደም ያለበት ተግባር ግን ራስን መፈተሹ ላይ ማተኮሩ ይጠቅማል:: እራሱን ያላወቀ
ሌላውን አውቆ መለወጥ ያስቸግረዋልና:
:
ለዛሪው ፍተሻ ሊረዱ የሚችሉ ሁለት ታሳቢወችን እንመልከትና ራስችንን እንታዘበው:: መታዘብ ከቻላን ደግሞ ይህን ለመቀየር እኔ
ምን ሰራሁ በማለት እራሳችንን እንሞግተው:: በዚህ ሙግት ደግሞ መልሱን ከውስጣችን ፈልቅቆ ማውጣት አያዳግተንም:: አሸናፊና
ተሸናፊውም ራሳችንና ህበረተሰባችን ይሆናል::
እድገት በጰሎትና በልመና አይገኝም
የማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እድገት በጰሎት ጉንብስ ቀና፥ ተቀምጦ በመመኘት፥ ሌላውን በማወደስና በማድነቅ ፥ ወይም
በመተቸት የሚገኝ አይደለም:: እድገት በአርቆ አስትዋይነት፥ እውቀትን በተግባር በመተርጎም፥ ከሊሎች በማጥናትና ጠቃሚውን
ገነዘባችን አርገን በመጠቀም፥ የምርምርን ግኝት በስራ በመተርጎም፥ እርስበርስ ተመካክሮ ለህዝብ በመስራት የሚገኝ የስራ
ትሩፋት/ረድኤት ነው::
ካለፉት ተምሮ የወቅቱን ሁኔታ ከመጭው እራይ ጋር አገናዝቦና አልሞ የማይሰራ ህብረተሰብ በቁሙ የሞተ ለምሆኑ ጥርጥር
የለውም:: ሃይማኖት የሚረዳው የመንፈሳዊ ህይወታችንን ሃያሉ እግዚአብሔር እንዲቀድሰው ለማድረግ እንጅ የህብረተሰብን
የእድገት ጎዳና እንዲቀድ/እንዲቀይስ አይደለም:: እትዮጵያኖችን እጅግ ከተጠናወተን አጉል ልማድ አንዱ ለችግራችን፥
ለኋዋላቀርነታችን፥ ለድንቁርናችን፥ ለመጨቆናችን የምንሰጠው መፍትሄ እሱ ወይም እግዚአብሔር ያውቃል ሆኖዋል::
እግዚአብሔር የስንፍናችንና የኋላቀርነታችን መሸሸጊያ ደን አይደለም:: ሊሆንም አይችልም:: እግዚአብሔርማ አውቆ የሚአስብ
ዐእምሮ፥ የሚያዩ አይኖች፥ የሚሰሩ እጆችና እግሮች ወዘተ ሰጦናል:: ሃያሉማ በራሱ አምሳል ፈጥሮ ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሏት
ብሎናል:: የምንባዛውና መሬትን የምንሞላው የቀንና የማታ ስራ ሲሰራ እንጅ ስለተመኘነውና ስለለመነው ብቻ አይመጣም::
ሊመጣም አይችልም:: ይህን የምንመኝ ከሆነ ደግሞ በሰማይ ላይ ከመትኖርዋ የትንቢት ላም ወተት እንደመጠበቅ ይቆጠራል::
የምንበላው ምግብ፥ የምንለብሰው ልብስ፥ የምንኖርበት ቤት የሚገኘው የተፈጥሮ ሃብትን ተጠቅመን ስናመርት ብቻ ነው:: ስራ
ካልፈለግን እንደሌሎቹ የዱር አራዊት/እንስሣት አውሪ ሆነን ጫካ ውስጥ በመኖር አድነን መብላት ይኖርብናል:: አደንም ቢሆን ቁጭ
1
በማለት አይገኝም:: ብዙ መጓዝን፥ የአደን መሳሪያ መፍጠርን፥ ታድኖ የተያዘውን አርዶና ጠብሶ የመብላት ስራን ይጠይቃል::
እንድናድግና ድህነትን አጥፍተን ከተመጽዋችነት ለመላቀቅ የስራን ክቡርነት በማስቀደም ከዚያም እግዚአብሔር ያውቃልን
በማስከተል ቢሆን ይመረጣል::
ንቀት
ኢትዮጵያዊያኖችን የተጠናወተን መጥፎ በሽታ አንዱ ንቀት ነው:: ነጮችን፥ ፈረንጆችን፥ ቻይናወችን፥ ጥቅሮችን ፥እራሳችንን ወዘተ
መናቅና ማጣጣል እንደትልቅ ኩራት አድርገን ይዘነዋል:: በመሰረቱ ሌላውን የሚንቅ ሁልጊዜ አስተሳስበ ድሃ የሆነ ሰው ውይም
ለራሱ ከሚገባው በላይ ከፍተኛ ግምት የሚሰጥ ሰውና ማህበረሰብ ነው:: ይህ ደግሞ ለእድገት እንቅፋት ነው:: በእጅጉም
የሗዋላቀርነት ምልክት እንጅ ሌላ ትርጉም የለውም:: ለመጀመሪያ ጊዜ የመንግስት ስራ እንደጀመርሁ አንድ ወንድሜ እንዲህ ሲል
መከሮኝ ነበር:: ሁልግዜ መማር፥ ማወቅ፥ መጠየቅና መመራመር እንዳለብኝ አለቃን መፍራት ሳይሆን ማክበር የስራ ባልደረቦቸን
መናቅ ሳይሆን ከነሱ መማር እንዳልረሳ አስታውሶኝ ነበር:: አለቃን መፍራት ሳይሆን ማክበርን ፥ የስራ ባልደረቦችን መናቅ ሳይሆን
ከነሱ መማር፥ የራስንም ትንሽ እውቀት ለማካፈል መዘጋጀት አዋቂነት ነው:: ከሃያ አመት በሗዋላም ይህ አውነታ አልተለወጠም::
የሚለወጥም አይሆንም:: ትምህርት ተጨረሰ፥ ዲግሪ ተገኘ ማለት መማር፥ መመራመር፥ መጠየቅ ቆመ ማለት አይደለም:: መጠየቅ
ምንጊዚም ያደርጋል ሊቅ:: ፕሮፊሰር መስፍን መጠየቅና መጠራጠር ወደእውቀት ያመራል ይሉናል::
በማህበራዊና በህግ ፍልስፍና መርህ መሰረት እውነት ሁልጊዚ ያድናል፥ መናቅ ያስገምታል ያዋርዳል ይላሉ:: ሌላውን መናቅ
እስካላቆምን ድረስ እድገታችን ባለበት የሚሄድ ወይም ወደ ኋዋላ የሚአፈገፍግ ይሆናል:: ከግለሰቦች፥ ከህብረተሰብ፥ ከድሃ
ሃገሮችም ሆነ ከበለጸጉት ብዙ የምንማረው አለ ይኖራልም:: እንክርዳዱን ከፍሪው ለይቶ የሚጠቅመውን የራስ ማድረግ ብልህነት
ነው:: እርግጥ ንቀን የምንተዋቸው ነገሮች የሉም ማልት ግን አይደለም:: የማይጠቅመውን ከሚጠቅመው ለይቶና አበጥሮ
ለማውጣት መጀመሪያ ማወቅና መመራመርን ይጠይቃል::
የስአት ክቡርነት
በስደት አለም ላይ ባሉ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ እየተለመደ የመጣ ባህሪ እንመልከት:: በተለያዩ ምክንያቶች ኢትዮጵያዊያን ሃገራቸውን
ለቀው በመውጣት በአምስቱም አሃጉራት ተበትነው ይገኛሉ:: በአብዛኛው ለስደት የዳረጓቸው ምክንያቶች ኢኮኖሚያዊ ፥
ፖለቲካዊና ማህበራዊ ናቸው:: በሃገራችን ባህል ዘመድ ከዘመዱ፥ ጓደኛ ከጓደኛው ፥ ህብረተሰብ ከህብረተሰብ በችግር፥ በደስትና
በሃዘን ተረዳድቶ ፥ ተጠያይቆና ተደጋግፎ ይኖራል:: በውጭ ሃገር ግን ሁኔታው ከዚህ ይቃረናል:: ሰው ካልሰራ ማንም ቀና ብሎ
የሚያየው የለም:: በካናዳ፥ በአሜሪካ፥ በአውሮፓ፥ በአውስትራሊያ፥ ወዘተ ያየነውና የሰማናው ነው:: ካልተሰራ ደግሞ በዌልፊር
ተስፈኛ ሆኖ መኖር ሲሆን ይህ ደግሞ እጅግ ያዋርዳል::
ከሞላጎደል ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች የተሰደዱበትን ሃገር ባህልና ወግ ለምደው ጥሩ የመስራት ባህልን አካብተው ይገኛሉ:: ብዙዎቹ
በስደት አለም ላይ ሆነው የሚሰሩትን ያህል በሃገራቸው ቢሰሩ ኢትዮጵያ የትበደረሰች ያስብላል (በርግጥ ሃገራችን ዚጎችዋን
ለማሰራት የሚአስችል የስራ ህግና ስነስራት ስላልገነባች በዚጎችዋ ተጠቃሚ መሆን አልቻለችም:: ሊላም ሊላም ምክንያት…)::
ስለሆነም በብዙ የውጭ ሃገር ከተሞች እንደምናየውና እንደምንሰማው የኢትዮጵያኖች የስራ ችሎታ፥ ብቃትና ዲሲፕሊን ከማንም
የማይተናነስ (ሲሆን ባይበልጥ) ሆኖ እናገኘዋለን:: ይህ ይበል ይበርታ ያሰኛል:: በአንጻሩ ደግሞ በሰለጠነ አለም ተቀምጠው
ወደሗዋላ የሚሔዱበትና የሚአሳፍር ስራ የሚያከናውኑበት ሆኖ ይገኛል::
ግብዣ ተጠርቶ በሰአቱ አለመገኘት የስልጣኔና የኩራት መለያ እየሆነ ከመጣ አመታት አስቆጥሯል:: በነዚህ ሃገሮች ህይወት
የሚሽከረከረው በሶስት አብይት ነገሮች ነው:: እነዚሁም ገንዘብ ጊዜና ስራ ናቸው:: የስራ ዋጋ ደሞዝ የፓርኪንግ ተመን በአጠቃላይ
ኑሮ የሚተመነው በጊዜ ተሰልቶ በሚሰጥ ገቢ ነው:: የህዝብ መጓጓዣ ባቡር፥ አየር፥ ኦውቶብስ ፥መርከብ፥ወዘተ በስአት ይነሳሉ
በስአት ይደርሳሉ:: ስአት ያላከበረ ሰው ወይም በስአቱ ያልተገኘ ተሳፋሪ ብቻውን ይቀራል:: ለዚህ ነው ባቡር ቆሞ
ኦይጠብቅም የሚባልው : :
2
የጊዜንና ስአትን ክቡርነት የማይረዳ ግለሰብም ሆነ ህብረተሰብ ከጊዜው የኢኮኖሚ፥ የፓለቲካና የማህበራዊ ባቡር ጋር አብሮ መጓዝ
ያቅተዋል:: በነዚህ ሃገሮች በስአትና በቀጠሮ የማይገኝ ሰው ወይም አለመገኝት ሶስት ባህሪያትን የሚገል ጹ ናቸው::
ደንታቢስነት / ግድየለሽነት ፥ የዋሾነት / የምነተቢስነት ፥ የድንቁርና ባህሪያት መግለጫዎች ናቸው::
ስለዚህ ሗላቀር አስተሳሰብ ትቂት አሳፋሪዎችን በተጨባጭ በካናዳ ዋና ከተማ ኦታዋ የሆኑትን በናሙናነት እንመልከት::
በከተማይቱ ከ 3-4 ሽህ ኢትዮጵያዊያን ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል:: ከከተማዋ ማነስ የተነሳ ኢትዮጵያኖቹ ከሞላጎደል ይተዋወቃሉ
ማለት ይቻላል:: ሁሉም የለት ጉርሱን የአመት ልብሱን ለማምረት ሲኳትን ጊዜው ያልፋል:: በአንጻሩ ኢትዮጵያዊያኖች
የሚገናኙባቸው ብዙ እድሎችም አሉአቸው:: ከነዚህም ዋና ዋናወቹ በደስታ፥ በሃዘን፥ በጸሎት ቤት፥ በህረተሰብ ስብሰባወች፥
በግብዣወች ወዘተ ላይ ነው:: በተለያዩ የመህበራዊ ጥሪዎችና ግብዣዎች ያለማጋነን አንድም ጊዝ ተጋባዥ ህብረተሰብ ስአቱን
አክብሮ የተገኘበትን ለአብነት መጥቀስ ያስቸግራል::
ከችግሩ አሳሳቢነት የተነሳ የሃይማኖት አባቶችና አለቆች ውግዘት በተሞላበት ሁኔታ፥ የኮሚኒቲ መሪዎች፥ በድሜአቸውና
በተመክሮአቸው አንቱ የተባሉ ግለሰቦች እንዲሁም ምሁራን ስለስአት ይከበር ሲአስተምሩና ሲወቅሱ ይደመጣል:: ምክሩም ሆነ
ትምህርቱ ሁሉም ገደል ገብቷዋል:: ህብረተሰቡም ጀሮ ዳባ ልበስ በሎ በዚህ አሳዛኝና ሗላቀር ድርጊቱ ቀጥሎበታል:: ይህን አስነዋሪ
ባህሪና ልምድ ቢቻል ከነአካቲው ለማስወገድ ባይቻል ለማሻሻል ጥረት ሲአደርግም አይታይም:: የጉዳይ አሳሳቢነት እጅግ ከፍተኛ
ቢሆንም ይባስ ብሎ ከመጥፎ ልምድነት አልፎ እንደኩራትና እንደስልጣኔ እየታየ መጥቷል:: ያደቆነ ባህሪ ሳያቀስ አይተውም
አንደተባለው : :
በአንድ ወቅት ሁለት ተጋቢወች ለሰርጋቸው እራት ግብዣ እንግዶቻቸውን ከምሽቱ ሰባት ስአት እንዲገኙላቸው ይጠራሉ::
ሙሽሮቹ ከምሽቱ ስምንት ሳት አካባቢ በለሞዚናቸው ወደግብዣው ይመጣሉ:: ባለሊሞውን ከምሽቱ/ከለሊቱ አስራሁለት ሳት ላይ
ተመልሶ እንዲወስዳቸው ተስማምተው ያሰናብቱታል:: ይህ ሊሞዝን በስአትና በፕሮግራም የሚሰራ በመሆኑ ወዲያው ወደሌላው
ስራው ይፈተለካል:: ሙሽሮችም አንግዶቻቸው እንዳልመጡ ይነገራቸዋል:: የጝደኛ መኪና አስጠርተው ወደቢታቸው ይመለሳሉ::
ካልጋ ወርዶ አመድ ማለት ይህ ነው:: እንግዶቻቸው ከምሽቱ ዘጠኝ ስአት አካባቢ እየተንጠባጠቡ ይደርሳሉ:: አብዛኛው እንግዳ
(80%)የሚሆነው አስር ስአት ላይ ይገባል:: ከዛም ሙሽሮቹ ተጠርተው ይመጣሉ:: ያው የተለመደው ተዝፍኖ ተበልቶ ተጠጥቶ
ግብዣው ወደ አስራሁለት ሳአት ገደማ ይጠናቀቃል:: ከሁሉ የሚገርመው ነገር ቢኖር ስአት አክባሪ ፋረንጆችም አብረው ሲንቃቁ
መዋላቸው ነው::
ይህ ብዙ ሳይቆይ እንደገና በዚህ ሰሞን በዚሁ ከተማ ሌላ ሰርግ ይደረጋል:: የጥሪ ወረቀቱና ፕሮግራሙ የሚለው ከቀኑ አራት
ተኩል ስአት ላይ ይገኙልን ይላል:: ተጋባዥ አዳራሹ የመጣው ግን ከመሽቱ ሰባት ስአት ጀምሮ ነው:: ሙሽሮቹ የገቡት ከምሽቱ
ስምንት ሳት ላይ ሲሆን የራት ግብዣው የተጀመረው ከዘጠኝ ስአት ላይ ነው:: ይህማለት ደግሞ ስአት አክባሪ ተጋባዥ ካለ አራት
ስአት ተኩል ሙሉ ተቀምጦ ሲጠብቅና መቀመጫውን ከወንበር ጋር ሲአለፋ ውልዋል ማለት ይቻላል:: የሚገርመው አንዳንድ
ተጋባዦች ህጻናት ልጆች ስላሏቸው አራት ሳይበሉ ወደቤታቸው የተመለሱ መሆኑን ይህ ጽሃፌ ዋቢ ምስክርነት መስጠት ይችላል::
በሌላ ወቅት የኢትዮጵያ ማህበረሰብ የአድዋን 116 ኛ መታሰቢያ ክብረ በአል ምክንያት በማድረግ ህብረተሰቡን ከቀኑ ሁለት ስአት
እንዲገኙለት በአክብሮት ጠርቶ አብዛኛው ተጋባዥ የደረሰው በአራት ስአት ለይ ነው:: የሚገርመው አንዳንዶቹ ፕሮግራሙ ሊፈጸም
ግማሽ ስአት ሲቀረው ደርሰዋል:: በዚህም ምክንያት ማህበረሰቡ ተጨማሪ ያዳራሽና ሌሎች ክፍያወች አክሎ የፕሮግራሙን ግዜ
ለማራዘም ተገዿል:: ማህበረሰቡ ለእለቱ ያወጣቸው መርሃግብሮች በጊዜ እጥረት ምክንያት ማስተናገድ ባለመቻሉ አንዳንድ
መርሃግብሮች እንዲሰረዙ መደረጉን ካስተናጋጆች ተረዳን::
ኧረ ዲያስፖራን ምን ነካው ሲባል አይ ሰው በስአቱ ስለማይመጣ እኔ አስቀድሜ ወይም በስአት ደርሸ ለምን ልንቃቃ ሲል
ይደመጣል:: የሚገርመው ይህ መጥፎ ባህሪና ልምድ ኢትዮጵያኖች ተሰደው በሚገኙባቸው አምስቱም አሃጉራት ተመሳሳይ መሆኑ
3
ከማስገረምም በላይ አሳዛኝ ሆኖ እናገኘዋለን:: ድንቄም ስልጣኔ:: ሁሉም እንዲህ ካለ ማነው ስአት አክባሪ የሚሆነው:: ቀጠሮ
የማያከብር ዳያስፖራ ለራሱ ያልበጀ አገርም አያኮራ ለማለት እንገደዳለን:: በቅርቡ ወደ ኢትይዮጵያ ሄጀ የወገኖቻችንን ስአት
አክባሪነት ሳይ በጅጉ ደሳለኝ:: ተሟጦ አልቆ የነበረው ተስፋዬ እንደገና ለመለመ::
ለሗላቀሩ ዲያስፖራ ግን በጅጉ አዘንሁለት:: የሚአሳዝነው ግን በውጪ ሃገር ተወልደው የሚአድጉት ልጆቻችው ከዚህ ሗለቀር
ዲያስፖራ ወላጅና ህብረተሰብ ምን ይማሩ ይሆን በማለት ተከዝሁ::
እስኪ እንጠያየቅ ዲያስፖራ:: ስአትን ማክበር ያልቻለ ዲያስፖራ በምን ታምር ነው ስለሃገሩ ፖለቲካዊ፥ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ
ሁኔታ የሚዶልተው? ይህነው ለሃገሩ አለኝታነኘ እያለ የሚመጻደቀው:: ከሆነ እሰየው:: ይህ ታዛቢ ግን ለማመን ይቸገራል:: እንደእኔ
ግምትና አስተሳሰብ የቀጠሮን ስአት የማያከብር ዲያስፖራ ለራሱ ሳይበጅ እንዴት ሃገር ያኩራ:: ተው ጎበዝ እራሳችሁን አታስገምቱ::
አገራችሁንና ወገናችሁንም አታዋርዱ፥ አታሳፍሩ::
ብዙ ነገር ባህያ አይጫንም ይላል ያገራችን ሰው:: ደሮ እንኳ በደመነፍስ ስአቷን ሳታዛንፍ ትቀሰቅሰናለች ወይም ንጋትን ታበስራለች::
እንስሣት በተወሰነ ስአት ባለቤታቸው ምግብ ካስለመዳቸው በዛችው ቦታና ስአት ይገኛሉ:: መጋቢያቸው ከዘገየ በመጮህ እሮሮ
ያሰማሉ:: ህጻናት በተወሰነ ስአት መተኛት ከለመዱ ስአትዋ ስትደርስ ያዛጋሉ ወይም ያለቅሳሉ:: ሰልሆነም በለመዱአት ስአት ይተኛሉ
ይነሳሉ:: ይህን የሚአዛቡት ካመማቸው ወይም ከራባቸው ብቻ ይሆናል:: ከእንስሳት የተሻለ የማሰብ ዐአምሮ ያለን፥ የጊዜና ስአትን
ጥቅምና ጉዳቱን ጠንቅቀን እያወቅን ብሎም ገንዘብ በሆነበት ሃገር እየኖርን፥ ይብዛም ይነስም ዘመናዊ ፊደል ዘመናዊ ለመሆን
ቆጠርን እያልን የምናወራ እንዼት ይህን መገንዘብና ማሻሻል ያቅተናል:: ማሻሻል ይቻላልና እንዝመትበት::
ምናልባት በዚች ጽሁፊ አስቀይሚአችሁ ከሆነ ከወዲሁ ይቅርታ እጠይቃልሁ:: ለሁላችንም የሚበጅ ስለመሰለኝና በዚህ ጉዳይ ላይ
ብዙ ሰው ሲብከነከን ወይም ከንፈሩን ሲመጥ ስለማይና ስለምታዘብ ነው ወደ አደባባይ ያወጣሁት እንጅ አዲስ ግኝት ወይም
ሮኪት ሳይንስ ሆኖም አይደለም:: በመጨረሻም በዚህ ጉዳይ ላይ ማንም ጲላጦስ ሆኖ ያለ የለም:: ሑላችንም የችግሩ አካሎች ስለሆን
የመፍትሄውም አካል መሆን ይገባናል:: ስለሆነም ኢትዮጵያዊ ዲያስፖራ ራሱን ፈትሾ ከተስተካከል ለራሱ ክብርን ፥ ለሃገሩ
ኩራትንና አለኝታነትን ያጎናጽፋል::
ቸር ይግጠመን::
የናንትው አቢቹ ነጋነኝ (aneganega@hotmail.com)
4

No comments:

Post a Comment