Tuesday, February 18, 2014

እኔና ወላጆቼ!

አብርሃ ደስታ


ዛሬ አንድ የዉስጥ መልእክት ደረሰኝ። ቁምነገሩ "ወላጆችህ ላንተ ብለው መስዋእት ከፈሉ፣ አስተማሩህ፣ ባጭሩ ለዚህ አበቁህ። አንተ ግን እነሱን ትቃወማለህ!" የሚል ነው።

አዎ! ወላጆቼ መስዋእት ከፍለዋል። ግዜው በሚፈቅደው መንገድ አምባገነኖችን ለማስወገድ ታግለዋል። ሲታገሉ ዓላማ ነበራቸው። ዓላማቸውም ነፃነት ነበር። መስዋእት የተከፈለበት ዓላማ አንድ አምባገነን (ደርግ) በሌላ አምባገነን (ኢህአዴግ) ለመቀየር አልነበረም።

አዎ! መስዋእት ከፍለዋል። የተከፈለው መስዋእት ለስልጣን አልነበረም፣ ለዴሞክራሲ እንጂ። ለስልጣን መስዋእት መክፈል አያስፈልግም። ምክንያቱም ከተሰዋህ፣ ከሞትክ ስልጣን የት ታገኘዋለህ? ዓላማህ ስልጣን መያዝ ከሆነ እስከ ሞት የሚደርስ መስዋእት መክፈል የለብህም። ምክንያቱም ከሞት በኋላ ስልጣን አይገኝም።

ወላጆጃችን ግን መስዋእት ከፈሉ። መስዋእት የሚከፈለው ለነፃነት ነው። የመስዋእት ዓላማ ነፃነት ነው። ወላጆቻችን መስዋእት ሲከፍሉ እኛ ልጆቻቸው በነፃነት በዴሞክራሲያዊ መንገድ የፈለግነውን መደገፍ፣ ያልፈለግነውን ለመቃወም፣ ወይም በፈቃዳችን መሰረት መደገፍም መቃወምም ለመተው ነበር። በምርጫችን ስንኖር የሚደርሰንን በደል እንዳይኖር ነው። እኔ በዚሁ መሰረት ወላጆቼን በከፈልሉኝ መስዋእት መሰረት በነፃነት ለመኖር እየሞከርኩኝ ነው። 

በነፃነት ለመኖር ሲፈልግ መቃወም ሲፈልግ ደግሞ መደገፍ አለብኝ። ህወሓት ግን የኔን መቃወም ይቃወማል። ምርጫዬ ሁኖ መቃወም ሲፈልግ እንደ ጠላት ያየኛል፤ ከሃዲ ይለኛል። የትግራይ ወጣት ሙሉ በሙሉ የህወሓት አባል መሆን አለበት እያለ የፓርቲ አባል ያለመሆን ፍላጎቴንና መብቴ ይጥሳል። የህወሓት አባል ባለመሆኔ የተለያዩ ጥቅማጥቅሞች እንዳላገኝ ያደርጋል። የተከፈለው መስዋእት ግን ለዚህ አይደለም። ስለዚህ ህወሓት የሰማእታትን አደራ አፍርሷል፤ የነፃነት ዓላማው በስልጣን ቀይሮታል።

እንዲህ ከሆነ ታድያ እንዴት ህወሓትን አልቃወምም? ህወሓትን በመቃወም የወላጆቼን የነፃነት ዓላማ ከግብ አደርሳለሁ። ወላጆቼ ለኔ ነፃነት ከታገሉ ያመጥሉኝን ነፃነት ብጠቀም ችግሩ ምንድነው? የወላጆቼን ዓላማ ለሚጠመዝዝ አካል ብቃወም ችግሩ ምንድነው? ስለዚህ ህወሓት መቃወሜ ትክክል ነው። ምክንያቱም መስዋእት የተከፈለበት ዓላማ መተግበር አለበት። የህወሓት ተግባር ፀረ ሰማእታት ዓላማ ነው።

.
.
.

ወላጆቼ የታገሉት ለራሳቸው ነው። (እላይ ከፃፍኩት የሚቃረን ይመስላል፣ ግን ሌላ መንገድ ነው)። ለኔ ሊሆን አይችልም። ወላጆቼ የራሳቸው የህይወት መንገድ አላቸው። የነሱ ጀግንነት ለራሳቸው ነው። ለኔ ሊሆን አይችልም። የወላጆቼን መንገድ መከተል ካለብኝ፣ የወላጆቼን አደራ መተግበር ካለብኝ ልክ እንደነሱ ጀግና መሆን አለብኝ። በወላጆቼ ጀግንነት መዋጥ ሳይሆን የራሴ የሆነ የጀግንነት ታሪክ ሊኖረን ይገባል። ወላጆቼ ገዢውን መደብ ተቃውሞው ለነፃነታቸው ታገሉ፣ ጀግንነት ፈፀሙ። እኔስ እንደነሱ ገዢውን መደብ በመቃወም ለነፃነቴ ብታገልና ጀግና ብሆን ችግሩ ምንድነው?

አባትህ ጀግና ስለነበረ ባባትህ ጀግንነት ኑር፣ የራስ ህ የጀግንነት ታሪክ ሊኖርህ አይገባም ያለ ማነው? ባባትህ ጀግንነት የምትኮራ ከሆነ ለምን አንተ ራስህ ጀግና ለምሆን አትሞክርም?

እመኑኝ! ወላጆቼ ታግለው ደርግን ባያባርሩ ኑሮ እኔው ራሴ በደርግን እታገለው ነበር። ወላጆቻችን ደርግን ስለታገሉ እኛ ልጆቻቸው ህወሓትን መታገል የለብንም ያለ ማነው? ማንም ይሁ ማን ፀረ ነፃነት የሆነ ስርዓት ካለ መቃወም አለብን።

አዎ! በህወሓት ዘመን ነው የተማርኩት። ግን በህወሓት ግዜ ስለተወለድኩ ብቻ ነው። በሌላ ስርዓት ብወለድ ኑሮ በሌላ ስርዓት እማር ነበር። ህወሓት ዜጎችን የማስተማር ግዴታ አለበት (በስልጣን እስካለድረስ)። ያስተማረንን ስርዓት መቃወም የለብንም የሚል ሎጂክ ካለ ግን የህወሓት መሪዎችም የሃይለስላሴና የደርግ ስርዓቶች መቃወም አለነበረባቸውም ማለት ነው። ምክንያቱም የህወሓት ባለስልጣናት የተማሩት በህወሓት አይደለም፣ በሃይለስላሴና በደርግ ስርዓቶች እንጂ።

እኔ የተማርኩት ሀገርንና ህዝብን ለመለወጥ እንጂ ታማኝ የገዢው መደብ አገልጋይ ለመሆን አይደለም። የተማርኩት ሀገርን የሚጠቅም ነገር ለመስራት እንጂ የፓርቲ ካድሬ ለመሆን አይደለም። ደግሞ የተማርኩት በመንግስት ሃብት (በህዝብ ሃብት) እንጂ በህወሓት (በፓርቲ) ሃብት አይደለም። ስለዚህ በሀገር ሃብት ከተማርኩ ለሀገር እድገት መስራት አለብኝ። ይህም እያደረግኩ ነው።

No comments:

Post a Comment