‹‹ይቅርታ›› የኢህአዴግ ቃጭል? ወይስ…
Posted by admin on July 9, 2012 0 Commentበተመስገን ደሳለኝ
1998
አዲስ አበባ በለውጥ ፍላጐት ከአፍ እስከ ገደቧ ታጥናለች። እዚህም እዚያም የፖለቲካ ወግ ይጠሰቃል። በቡድን ሆነው፣ በስሜት ተውጠው በፖለቲካ ጉዳይ የሚከራከሩ በርክትዋል፡ ፡ ለዓመታት የፖለቲካ ጉዳይ ‹‹ፆም›› የሆነባቸው የመንግስት መስሪያ ቤቶች ሳይቀሩ ጎራ ለይተው በሚከራከሩ ሠራተኞቻቸው ተፈስገዋል፡፡ ‹‹ቅንጅቱ መንግሥት ለመመስረት የሚያስችል ድምፅ አግኝቷል›› ይላል አንዱ። ‹‹ቢሆንም ኢህአዴግ ይገግማል!›› ሲል ይመልሳል፤ ኢህአዴግ በምርጫ ስልጣን አይለቅም የሚል አቋም ያለው ተከራካሪ፡ ፡
…የጋዜጦች እትሞች ከምርጫው በፊት ከነበረው ቅጂ ከሶስት እስከ አምስት እጥፍ ድረስ ጨምረዋል። ማንበብ የሚችለውም፣ ማንበብ የማይቻለውም ቋሚ የጋዜጣ ሸማች ሆኖአል-እድሜ ለምርጫው። በኢትዮጵያ ‹‹መንግሥት…›› ሲባል የተቃወመውን በሙሉ የሚገድል እንደሆነ ከልምድ የተገነዘቡ ወላጆች ለልጆቻቸው በመስጋታቸው ጭንቀታቸው ጨምሯል፡ ፡ እነዚህ ኩነቶች የድህረ ምርጫ 1998 ዓ.ም. ዋነኛ መገለጫዎች ነበሩ፡፡
እንዲህ ውጥረት በነገሠበት አንድ ቅዳሜ ከቅንጅቱ ዋነኛ አመራሮች አንዳቸውን በአካል ልተዋወቅ ወደ ቀጠሮ ቦታ እየሄድኩ ነው-መስከረም 28 ቀን 1998 ዓ.ም.፡፡ በምርጫው ላይ የጎላ ተሳትፎ የለኝም። የየትኛውም ፓርቲ አባል አይደለሁም። ድምፄንም ለማንም አልሰጠሁም። ነገር ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ እልፍ አእላፎችን ከጎኑ ማሰለፍ ከቻለው ‹‹ቅንጅት›› መሪዎች አንዳቸውን ልተዋወቅ ነው። የሚያስተዋውቀኝ ደግሞ በእጅጉ የማከብረውና የማደንቀው የጋራ ወዳጃችን አብይ ተክለማርያም ነው። ያኔ ተወዳጇ አዲስ ነገር ጋዜጣ አልተመሰረተችም። አብይ የሚያዘጋጃት ‹‹መዝናኛ›› የተባለች በድህረ ምርጫ እየገነነች የመጣች ጋዜጣ ግን ነበረች። ቀጠሮአችንም ጋዜጣው ቢሮ ውስጥ ነው። ልተዋወቅ እየሄድኩ ያለሁት የቅንጅቱ ምክትል ሊቀመንበር ሆና ከተመረጠች 14 ቀናት ብቻ ካለፋት ከብርቱካን ሚደቅሳ ጋር ነው፡፡ (እርግጠኛ ባልሆንም ብርቱካን ቀድማኝ የደረሰች መሰለኝ) …በጥቂት ደቂቃ ልዩነት ውስጥ ዝናዋ በአጭር ጊዜ ከናኘው እንስቷ ፖለቲከኛ ብርቱካን ጋር ተገናኘን። ከዚህ ቀደም እንደሚተዋወቁ ወዳጆች የሞቀ ሰላምታ ተለዋወጥን፡፡ ዛሬ ፋይሏ በተዘጋው በመዝናኛ ጋዜጣ ቢሮም ለአንድ ሰዓት ያህል አወራን። ብዙ ነገሮችን አነሣን፣ ብዙ ነገሮችን ጣልን። ኢህአዴግ እየተፍረከረከ እንደሆነ ግምቷን ነገረችኝ። ከኢህአዴግ አመራር ውስጥም ሙሉ በሙሉ መሸነፋቸውን የተቀበሉ ሰዎች እንዳሉ ተነጋገርን፡፡ አንዳች ለውጥ እንደሚኖርም አብዝተን ተስማማን፡፡ ከቆይታችን በእጅጉ የሳበኝ ግን በውስጧ ያለው ጥንካሬ እና ብርቱ የትግል መንፈስ ነው። ‹‹ዳኛ እና ዐቃቤ ሕግ ሆኜ ሰርቻለሁ›› አለችኝ በስሜት ተውጣ። ራሴን ላይና ታች በማወዛወዝ እያዳመጥኩ መሆኑን አረጋገጥኩላት። ቀጠለች ‹‹ነገር ግን እነዚህን ቀናት (ከተመረጠችበት ጊዜ በኋላ ያሉትን ነው) እንደኖርኩት አይነት ደስተኝነት ተሰምቶኝ አያውቅም።›› ንግግሯ በደስታ ሞላኝ። ኢትዮጵያውያን ወንዶች ብቻ ሳይሆኑ፣ ኢትዮጵያውያን ሴቶችም የለውጡ ፊት መሪ ሊሆኑ እንደተዘጋጁ እርግጠኛ ሆንኩ። …ብርቱካን እየተናገረች ነው። እኔም እየሰማሁ ነው ‹‹በየደረስኩበት የሚያገኘኝ ሰው ያበረታታኛል። ጣቱን እያሳየ ድጋፉን ይገልፅልኛል። ለዚህ ሕዝብ ዛሬ ብታሰርም አይቆጨኝም›› አለች ቀልብን በሚገዛ ድምፅ።
‹‹እታሰራለሁ ብለሽ ትሰጊያለሽ?›› እንደዋዛ የጠየኳት ጥያቄ ነው። ‹‹አዎን!›› ስትል በቀላሉ መለሰች፡ ፡ ግዙፉን ቦርሳዋን እየነካካችም ‹‹መቼ እንደምታሰር ባላውቀውም ዛሬ ብታሰርም ዝግጁ ለመሆን ሻርፕና ቀላል ልብሶችን በዚህ ቦርሳ ይዤ ነው የምንቀሳቀሰው›› አለችኝ መለስተኛ ሻንጣ የሚያክለውን የእጅ ቦርሳዋን መነካካቷን ሳታቋርጥ። ደነገጥኩ። ተገረምኩም። እንዴት አይነት ቁርጠኝነት ነው? ይህ አይነቱ ድፍረትስ ‹‹ተራራን ከማንቀጥቀጥ›› በምን ያንሳል? ለራሴ ያቀረብኩት ጥያቄ ነው።…እንዴት ደስ ይላል ለሀገር ወገንተኛ መሆን፤ ለህዝብ ማድላት!
የሆነ ሆኖ ኢህአዴግ እንደቀድሞ በቀላሉ የማያንበረክካቸው እና የማያስፈራራቸው መሪዎች እየተፈጠሩ እንደሆነ ገመትኩ። ከእነዚህ ውስጥ ብርቱካን ሚደቅሳ አንዷ ለመሆኗ ደግሞ እርግጠኛ ሆኛለሁ። ማን ነበር ‹‹እንስቷ ነብር›› ያላት? ብቻ እንጃ።
ከሶስት ዓመት በኋላ
…ብርቱካን ሚደቅሳን ጨምሮ ሁሉም የቅንጅት አመራሮች ታስረው በይቅርታ ተፈተዋል። ቴዲ አፍሮም
‹‹ሆ በል ክራር፣
ሆ በል ማሲንቆ
ስታይ ሰው ታርቆ…››
የሚል ነጠላ ዜማ ለቆ በየመዝናኛ ቦታው አዋቂዎችንም፣ ወጣቶችንም… ዕቅል አሳጥቶ እያዘለለ አስጨፍሯል። ይህ ከሆነ አንድ አመት በኋላ አንድ ነገር ተከሰተ። ‹‹በሶስት ቀን ውስጥ የብርቱካን ሚደቅሳ ይቅርታ ሊነሳ ነው›› የሚል ወሬ መላ ሀገሪቱን ናጣት። ‹‹ምክንያቱ ምንድር ነው?›› የሚሉ ጠያቄዎችም እልፍ አዕላፍት ሆኑ። በስዊድን ሀገር ለደጋፊዎቿ ‹‹(የቅንጅት አመራሮች) የተፈታነው በሕዝብ ጫና ነው ስላለች ነው›› የሚሉ ድምፆች በረከቱ። ብዙዎች ግራ ተጋቡ። ‹‹ታዲያ ይህ ምን ወንጀል ነው?›› ሲሉም ጠየቁ። ‹‹ኢህአዴግን አስኮረፈ!›› አሉ እናውቃለን የሚሉ። ፖለቲካ ገብቶናል ያሉ ደግሞ ‹‹መጀመሪያውኑም ሲፈቱ ይቅርታ የተደረገላቸው በቅድመ ሁኔታ ነው›› ሲሉ ተነተኑ።
በዚህ መሀል ያ ሶስት ቀን አለፈ። ብርቱካንም ‹‹ቃሌ›› ስትል በሰጠችው መግለጫ የጣሰችው ሕግ እንደሌለ፣ ጉዳዩ በይቅርታ እንዲያልቅ ሸምጋይ በነበሩት ሽማግሌዎች ስምምነት ከተፈጠረ ‹‹የፓርቲው መሪዎች ያለ ምንም ገደብ የፓርቲውን ስራ እንደሚቀጥሉ›› ጠቅላይ ሚንስትሩ ቃል መግባታቸውን መናገራቸውን ገልፃ፣ ማስተባበልም ካስፈለገ በሚል ስሜት ይመስለኛል ‹‹…በእርግጥም በዚህ ሰነድ ላይ እኔም እንደ አንድ ታሳሪ መፈረሜን ክጄ አላውቅም፡፡ በሽማግሌዎቹም የዕርቅ ማግባቢያ መንፈስ መሰረት በፖለቲካ የተቀሰቀሰውን ክስ ፖለቲካዊ ዕልባት ለመስጠት በማሰብ ለዕርቅ ስል ከሌሎች የፓርቲው መሪዎች ጋር ተስማምቼ ሰኔ 11 ቀን 1999 ዓ.ም በተጻፈው ሰነድ በሽማግሌዎች አማካኝነት መንግስትን እና የኢትዮጵያ ህዝብን ይቅርታ ጠይቄአለሁ፡፡ ብፈልግም ልለውጠው የማልችለው ሐቅ ነው፡፡›› ስትል በይቅርታ መፈታቷን እንዳልካደች ገለፀች። መንግስት ሆዬም ‹‹ቃሌ›› የሚለው የማስተባበያ ቃል በቂ አይደለም አለና አሰራት። አንዳንድ ታዛቢዎችም ‹‹የታሰረችው ቀጣዩ አመት ምርጫ ስላለ፣ ሊቀመንበር ተደርጋ የተመረጠችበት አንድነት ፓርቲ በምርጫው ለኢህአዴግ ከባድ ተገዳዳሪ ሊሆን ይችላል›› ተብሎ ስለተሰጋ ነው ሲሉ ፃፉ፤ እድል ባገኙት ሚዲያም አፅንኦት ሰጥተው ተናገሩ።
…ጠቅላይ ሚኒስትር መለስም ብርቱካንን ካልፈታችሁ ብለው ጫና ለመፍጠር የሚፈልጉ ዕርዳታ ሰጪ ሀገራት እንዳሉ በገደምዳሜ ከነገሩን በኋላ በዚህ ምክንያት ብርቱካንን እንደማይፈቱ አስረድተው ሲያበቁ ‹‹ከጣማቸው ይቀበሉ፤ ካልጣማቸው በሊማሊሞ ያቋርጡ›› የሚል ይዘት ያለው መልስ ሰጡ። ብርቱካንም ለዕድሜ ልክ እስራት አሰቃቂው ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ገባች። ይህን ጊዜም ብዙዎች ከይቅርታው ጀርባ አንዳች ጋኔን እንዳለ ጠረጠሩ፡፡ ጠርጥረው ሲያበቁም ህዝብ የሚያውቀው ‹‹ይቅርታ›› እና መንግስት የሚጠቀምበት ‹‹ይቅርታ›› በትርጉም ለየቅል እንደሆኑ ተረዱ፡፡
2003
ብርቱካን ሚደቅሳ ለድጋሚ እስር ከተዳረገችበት እስር ቤት፣ በድጋሚ ይቅርታ የተለቀቀችበት ዓመት ሆነ። በዚህ ይቅርታ ላይም ‹‹… አሮጊት እናቴን መርዳት ልጄን ማሳደግ ሲገባኝ፤ ዘላለማዊውን ኢህአዴግ ከስልጣኑ እንዲወርድ መሞከሬ እግዜርን የመቃወም ያህል ርኩሰት ነው›› አይነት ያለው ትርጓሜ ያዘለ ይቅርታ እንድትጠይቅ መገደዷን ሰማን፡፡ ዘግየት ብሎም መንፈሰ ፅኑዋ ብርቱካን ሚደቅሳ የአዲሱ የፖለቲካ ስልት ‹‹ሰለባ›› እንደሆነች ገባን።
2004
…የአውራምባው ዳዊት ከበደ፣ በ1999 ዓ.ም መጨረሻ ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት በይቅርታ ተፈቶ ሲያበቃ ‹‹አውራምባ ታይምስ›› የሚባል ጋዜጣ መስርቶ የመንግሥትን ገመና የሚገልጡ የተለያዩ ፅሁፎችን ማተም ጀመረ። ሀገሪቱ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ታመራ ዘንድም የቻለውን ያህል አስተዋፅኦ አበረከተ። አድሎአዊ አስተዳደርን፣ የተዛቡ ፍትሆችን፣ የመብት ረገጣዎችን… ተቃወመ-በብዕሩ። ይህንን አበርክቶት ከግምት ያስገባው ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ድርጅትም (CPJ) ‹‹የ2011 ዓለም አቀፍ ተሸላሚ›› አድርጎ መረጠው። …ይህ ከሆነ ከወራት በኋላም ዳዊት ከበደ ‹‹(ያ የፈረደበት) ይቅርታ ሊነሳብኝ እንደሆነ አስተማማኝ መረጃ አገኘሁ›› ብሎ ከሀገር ተሰደደ። ሌላ ‹‹ሰለባ››ም ይሏችኋል ይህ ነው፣ ሌላ አይደለም፡፡ …እነሆም ማሰር፣ ከአሰሩ በኋላ በይቅርታ መልቀቅ፤ ከለቀቁ በኋላ ደግሞ ይቅርታን አንስቶ መልሶ ማሰር የሚባል ‹‹ፖለቲካ›› ስራ ላይ ከዋለ ድፍን አምስት አመት ሞላው። ይህ አይነቱ ፖለቲካም ውሎ አድሮ ‹‹የሚያከስር›› ወይም ‹‹የሚያተርፍ›› ተወራራጅ ሒሳብ ያለው የገዥው ፓርቲ ‹‹ተቀማጭ›› ሆነ፡፡ አንዳንዶችም ‹‹በይቅርታ ተቀባዩ አንገት ላይ ተንጠልጥሎ ቀሪ ዘመንን በሞላ ‹ኪል፣ ኪል…› የሚል ‹ቃጭል› ነው›› ሲሉ ምክንያታዊ ትንታኔ አቀረቡ፡ ፡ …እኛም በቀጣዩ አንቀጽ የይቅርታ ይህ መግላሊቷን አጀንዳ አድርገን እንያት፡፡
የፖለቲካው መንፈስ
የዚህ ትውልድ ፖለቲካ አንድምታ፣ ከያ ትውልድ የፖለቲካ አንድምታ እንደወረደ የተተገበረ ነው፡፡ በመጠፋፋት ሳጋ እና ማገር የቆመ ማለቴ ነው፡፡ ሀቅ ነው! ያ ትውልድ ከፍ ሲል በርዕዮት አለም ልዩነት እርስ በእርሱ ተጠፋፍቷል፡፡ ዝቅ ሲልም ‹‹በቃላት አጠቃቀም›› ተገዳድሏል፡፡ ለምሳሌ አንዱ ‹‹ወዛደር›› ሲል ሌላኛው ‹‹ላብአደር ነው የሚባለው›› ብሎ ጦርነት ሲያውጅበት አይተናል፡፡ ‹‹ኢህአፓ›› የተሰኘው ነውጠኛ ድርጅት ‹‹እናቸንፋለን!›› ሲል በመፈከሩ ብቻ፣ መኢሶን የተባለ ሌላ ነውጠኛ ‹‹አብዮተኛ ‹እናሸንፋለን!› እንጂ ‹እናቸንፋለን› አይልም›› ሲል በፈጠረው የሆሄያት ልዩነት ወደጎዳና ላይ መገዳደል መሸጋገራቸው የትላንት ታሪክ ነው። በነገራችን ላይ የኢህአዴግ መሪዎችም እንደ ታሪክ ተጋሪዎቻቸው በዛ ዘመን መንፈስ የተቀኙ ናቸው። መፍትሄያቸውም እንደዚያው ዘመን ነው፤ ‹‹ወይ ከኛ ጎን ቁም፤ አሊያም ጥፋ!›› ለዚህም ነው እግዜሩ ‹‹ኑ እንውረድ ሰውን በምሳሌያችን እንፍጠር›› እንዳለው በራሳቸው (በኢህአዴግ) አምሳያ የተፈጠሩ ማህበራትን እንደእንጉዳይ ያፈሉት፡፡ የኦሪቱ ቃልንም በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ቀይረው እንዲህ ያሉት ‹‹ኑ እንታገል ኢትዮጵያውያንንም፣ ኢትዮጵያንም በምሳሌያችን እንፍጠር››፤ እነሆም ቃሉን የሰሙ፣ ሰምተውም በልባቸው ያሳደሩ ‹‹የሰራተኛ ማህበር፣ የመምህራን ማህበር፣ የሀኪሞች ማህበር፣ የጋዜጠኞች ማህበር፣ የነጋዴዎች ማህበር፣ የአርቲስቶች ማህበር፣ የሸማቾች ማህበር…›› ተፈጠሩ፡፡ ለዚህም መሰለኝ የዛሬ ሃምሳ አመት የነበረው ‹‹የዲሞክራሲ›› እና ‹‹የሰብአዊ መብት›› ጥያቄ ዛሬም ዋነኛ አጀንዳ ሆኖ ሀገሬን ያሉ እየታገሉለት ያለው። በጥያቄው ላይ ያለው ልዩነት ‹‹የአፄ ኃይለ ሥላሴ የብዝበዛ አገዛዝ…›› የሚለው ‹‹የአቶ መለስ ዜናዊ አምባገነናዊ አስተዳደር…›› በሚል መተካቱ ብቻ ነው። ከዚህ ባሻገር የማይካደው ልዩነት ይህ ትውልድ እንደ ‹‹ያ ትውልድ›› በፖለቲካ ልዩነት አውሮፕላን አይጠልፍም፤ ለሃሳብ ተቃርኖም ነፍጥ አያነሳም። ይህ ማለት ግን ስርዓቱ ተቀናቃኙን በትውልዱ የትግል ስልት እየገጠመው ነው ማለት አይደለም። እንዲህማ ልንል አንችልም። ምክንያቱም ከ‹‹ቀይ ሽብር›› ማፋፋም አንስቶ ‹‹አሸባሪ›› ብሎ በፍርድ ቤት ወንጅሎ ቃሊቲ እስከ ማውረድ የሚደርሱ መንግሥታዊ ምላሾችን እያየን ነውና።
እዚህ ጋ መነሳት ያለበት ቁም ነገር አለ፡፡ ይኸውም ተቀናቃኝ ወይም ተቃዋሚ ላይ የአፄው መንግሥት የተሻለ ርህራሄ እንደነበረው ነው፡፡ አፄው ግዙፍ ተቃውሞዎችን ሳይቀር ለረጅም ጊዜ ታግሰው አልፈዋል፡፡ አንዳንዴም በ‹‹አስለቃሽ ጢስ››፤ አልፎ አልፎም ‹‹ዱላ›› ብቻ በያዘ ፖሊስ ችግሩን ለመፍታት ይሞክሩ ነበር። በአፄው ላይ ተማሪዎችን እና ሠራተኞችን ካነሳሱት ውስጥ አንዱ የሆነው የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን) መስራች እና ዋና ፀሀፊ የነበሩት አንዳርጋቸው አሰግድ ‹‹በአጭር የተቀጨ ረጅም ጉዞ›› በሚል ርዕስ በፃፉት መጻሕፍ ላይ፡-
‹‹በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ‹ምኅረት፣ ግዞት፣ የቁም እስር፣ አምባሳደርነት ሾሞ መላክ፣ ከሹመት አግልሎ ማቆየት…› የፖለቲካ ተቃዋሚዎች አያያዝ መንገዶች ነበሩ። እርሳቸውን የተኩት ሁለቱ መንግሥቶች ወሬውንም የሰሙ አይመስሉም፡ ፡ ብቻ ደግሞ ‹ምኅረት…ወዘተ› የመንግሥት ጥንካሬ ምልክት ተደርጎ መታየት የለበትም፡፡ የሚያመላክተው ተቃራኒውን ነው። ሆኖም ግን እንደዚያ ያለው መንግሥት ከገዳይና በእስር ከሚያበሰብስ መንግሥት ይሻላል›› ሲሉ የሰጡት ምስክርነት አንድ ማሳያ ሊሆን ይችላል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ፕሮፌሰር አንድሪያስ እሸቴም ባለፈው ቅዳሜ ከሸገር ራዲዮ ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ ላይ ‹‹አፄ ኃይለሥላሴ ተቃዋሚዎቻቸውን ልጆቼ ናቸው ብለው ያስቡ ነበር›› ያሉት ሌላ ማረጋገጫ ሊሆን ይችላል። በእርግጥ አንዳርጋቸው አሰግድ ‹‹ሁለቱ መንግስታቶች ወሬውንም የሰሙ አይመስሉም›› ሲሉን፤ ወሬውን የሚያውቁት አንድሪያስ እሸቴ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ሆነው እያለ ‹‹ተቃዋሚዎችን እንደ ልጆችህ ተመልከት›› ብለው አለመምከራቸው በፕሮፌሰሩ ላይ ያለውን ምፀት ይበልጥ ያጎላዋል። የኩነናው ባለድርሻም ያደርጋቸዋል፡፡
ይቅርታ ወይስ…
በ1996 ዓ.ም ወርሃ ሚያዚያ የወጣው ‹‹ነጋሪት ጋዜጣ›› የይቅርታን አዋጅ የሚመለከት እንደሆነ ይገልፃል፡፡ ነገር ግን አዋጁ በክፍል 3፣ አንቀጽ 16 ላይ ‹‹የይቅርታ ዓላማ የህዝብን ደህንነትና ጥቅም ማስከበር ነው›› ከማለቱ ውጭ ስለይቅርታ ምንም አይነት ማብራሪያ የለውም፡፡ የሚያተኩረውም በይቅርታ አቀራረብ ሥርዓት ላይ ነው፡፡
ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ በሚወጡ አዋጆች ላይ ካሉ መሠረታዊ ችግሮች አንዱ ይህ ነው። ያልተብራሩ ወይም ግልፅ ያልሆኑ ሀሳቦችን አጭቆ ማቅረብ፡፡ ይህ ደግሞ ለትርጉም አሻሚ ይሆንና ብዙ ክፍተት ይፈጥራል። በይቅርታ አዋጁ ላይም ‹‹ይቅርታ›› ማለት ምን ማለት እንደሆነ አልተገለፀም፡ ፡ ወይም ይቅርታ የተደረገለት ሰው ሊነፈግ ስለሚችለው መብት አልተዘረዘረም። ለዚህም ነው በኢትዮጵያ በተለይም ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ ታስረው በይቅርታ የሚፈቱ ዜጐች፣ የተሰጣቸው ይቅርታ ሙሉ ነፃነትን የሚያጎናፅፍ ሳይሆን፣ በተንቀሳቀሱ ቁጥር ‹‹ኪል፣ ኪል…›› እያለ ‹‹ቀይ መስመር›› መኖሩን የሚያስታውስ ባንገት የሚጠለቅ አስደንባሪ ‹‹ቃጭል›› እንዲሆን ያደረገው። ልክ በምርጫ 2002 ዕለት ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው ‹‹ምርጫው እየተጭበረበረ›› ለመሆኑ ማስረጃ እንደደረሳቸው ተናግረው ሳይጨርሱ፣ በምርጫ 97 ማግስት የተጠለቀላቸው ‹‹ቃጭል›› መደወሉን ተከትሎ በኢቲቪ ያስተባበሉት አይነት ማለት ነው፡፡ አዲሱ ምህዳር ማጥበቢያ- የይቅርታ ፖለቲካ ማለትም ይህ ነው፣ ሌላ አይደለም፡፡
ይቅርታ ማለት ምንድር ነው?
የ‹‹ከሳቴ ብርሃን ተሠማ የአማርኛ መዝገበ ቃላት›› ይቅርታ ለሚለው ቃል አቻ ትርጉም ‹‹አንድ ነገር ሲሳት ወይም በንግግር ማኻል አንድ ነገርን ጣልቃ ከተደረገ በኋላ ለማድረግ ይቅርታ ማለት ነው›› ይላል።›› መቼም ለዕድሜ ልክ ፍርደኞች የተሰጠው ይቅርታ በዚህ የሚገለፅ ነው ባንልም ‹‹ይቅርታ›› የምትለዋን ቃል ግን ትንሽ ሰፋ ያደርጋታል። ምክንያቱም በሀገራችን ይቅርታ በገዥዎችም፣ በተገዥዎችም መካከል የነበረ እና ሀገሪቷን ከመፈራረስ አግዶ ያቆየ ባህል ነው፡፡
እናም ‹‹ይቅርታ›› እንዲህ በአዳዲስ ብልቶች ተከፋፍሎ ትርጉሙ ከመየቀሩ በፊት የቆየ ባህል ነበር። ይህ አንድ እውነት ነው፡፡ ኢህአዴግን መደገፍ መብት የሆነውን ያህል፣ አምባገነንነቱንና ሙሰኛነቱን መቃወም መብት መሆኑ ደግሞ ሌላ እውነት ነው፡ ፡ ስለዚህም ገና ለገና ‹‹የአይናቸው ቀለም አላማረኝም›› እየተባለ አንዱን ‹‹ሽብርተኛ›› ሌላውን ‹‹ተላላኪ›› እያሉ ወንጅለውና ፈርደው ሲያበቁ ‹‹ይቅርታ›› በሚባል እጥን አጥኖ ማንነትንም ሆነ ሞራልን ማምከን፤ ቀን ከሌሊት እንቅልፍ አሳጥቶ የሚያሳድረውን ያንን ‹‹የቁጣ ቀን›› መምጫ ዕድሜ ከማሳጠር ባለፈ ጠቀሜታ የለውም። በይቅርታ የሚለቀቅ እስረኛም በገደብ እንደተለቀቀ ተደርጎ ‹‹ይቅርታህ ሊነሳ ነው›› የሚለው ጨዋታም አትራፊ አይደለም፡ ፡ ምንአልባት አገሪቱም ፖለቲካውም የኢህአዴግ ነው ወደሚል ግልፅ አምባገነንት ካልተሄደ ማለቴ ነው።
የሆነ ሆኖ በኢትዮጵያ አብዮታዊ ዴሞክራሲን ‹‹እንደግል አዳኝ›› አድርጎ ለመቀበል አይነተኛ መፍትሄ ሆኖ እየወጣ ያለው ተቃዋሚዎችን እና ነፃ ጋዜጠኞችን ማሰር፤ ከአሰሩ በኋላ ደግሞ ፍርድ ቤት ማመላለስ፣ ማመላለስ፣ ማመላለስ… ዳኛ መሣይ፣ ዐቃቤ ሕግ መሣይ፣ ምስክር መሳይ፣ ማስረጃ መሳይ… ብዙ መሣይ ነገሮችን ማዘጋጀት። በመጨረሻም እድሜ ልክ ወይም አስራአምስት እና ሃያ ዓመት እስር መፍረድ፡፡ ከፍርዱ በኋላም ‹‹የይቅርታ ጠይቅ›› ግፊትን እንደደራሽ ውሃ በር ተቆልፎበት በተዳከመ እስረኛ ላይ መልቀቅ፡፡ አስከትሎም በግፊቱ ለወደቀው አዲሱን ማህተም (ቃጭል) በአንገት አስጠልቆ ቀሪ ዘመንን ለሀገሩ እንግዳ፣ ለሰዉ ባዳ ማድረግና ከሁለት አማራጭ ጋር ፊት ለፊት ማላተም። የመጀመሪያውም አማራጭ ሀገር ለቆ መሠደድ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ኢህአዴግ ሲዘፍን እስክስታ እያስወረዱ አጃቢ አድርጎ ማስቀመጥ ይሆናል ማለት ነው።
በአናቱም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል በፅንፈኝነት የሚናወዝ፣ አቻቻይ ለሆነ አማካይ መንገድ ትዕግስት የሌለው እንደሆነ ይታወቃል። ፖለቲካዊው ስነ-ልቦና ስርዓቱን የሚቃወሙ ዜጐች በታላቅ መከራ ውስጥ ቢያልፍም በገዢው ቡድን ተገደው እንኳን የሚስማሙባቸውን ጭብጦች ለመረዳት ዕድል አይሰጥም። የተቃወሙትን ይቅርታ መጠየቅ የተንበርካኪነት ተመሳስሎ ተደርጎ ይወሰዳል። ኢህአዴግ ይህን በሚገባ የተረዳ የሚያስመስለው፣ በግፍ ያሰራቸውን ዜጐች በተለያዩ መንገዶች አንገታቸውን እንዲሰብሩ ካደረገ በኋላ በይቅርታ እንዲፈቱ ማስገደዱ ነው። በይቅርታው የሚወጡት ፖለቲከኞችም የደጋፊዎቻቸው መሰረት እንደሚላላ ኢህአዴግ በሚገባ የተረዳው ይመስላል። ፓርቲው ራሱ በብክለቱ ውስጥ የተሳተፈበትን የፖለቲካ ተለምዶት በዚህ መልክ ሊያተርፍበት እንደሞከረ ከላይ የቀረቡት ትርክቶች በበቂ የሚያሳዩም ይመስለኛል፡፡
መቼም ኢህአዴግ በዚህ አያያዙ እስር ቤት ባሉ ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኞች፣ እንዲሁም እንደ ሰሞኑ ወሬ ከሆነ ደግሞ የ‹‹ቃጭል›› ማህተም የሚያስሩ ወይም እንዲያስሩ አስገዳጅ አማራጭ የሚቀርብላቸው ዜጐች ቁጥር ከኢኮኖሚ ‹‹እድገቱ›› በላይ መናሩ አይቀሬ ነው። ሁኔታውን አንዳንዴ ሳስበው፣ ሳስበው አቶ መለስ ፓርቲያቸው ለ40 እና 50 ዓመት በስልጣን ላይ እንዲቆይ እየሰሩ ያሉት ሠርክ እንደሚነግሩን ‹‹ልማታዊ መንግሥት›› ሆነው ሳይሆን ‹‹ተቺዎቻቸው››ን እና ‹‹ተቀናቃኞቻቸው››ን በሙሉ እያሰሩ፣ በይቅርታ እየፈቱ ቃጭል አንጠልጥለውባቸው በማሸማቀቅ ይመስለኛል።
የሆነ ሆኖ ከዚህ በኋላ የሚኖረው ትግል ‹‹ቃጭል›› በማሰር እና ‹‹ቃጭል›› አላስርም በሚሉ የነፃነት ፍናወጊዎች መካከል መሆኑ አይቀሬ ነው። ጎበዟ ርዕዮት አለሙ ከቃጭሉ ይልቅ ‹‹ይግባኙን›› መርጣለች። ምንአልባት ‹‹እምቢይ ባይነት›› እየመጣ ለመሆኑ ይሄ አንድ ምልክት ሊሆን ይችላል። ሌሎችም አሉ ‹‹ኪል፣ ኪል፣ ኪል…›› የሚል የቃጭል ድምፅን መስማት የማይፈልጉ፡ ፡ …ብርቱዎቹ እየመጡ ይሆን? ማን ነበር ‹‹ቆንጆዎቹ ገና አልተወለዱም›› ያለው?
ከእንዲህ አይነቱም ‹‹ብቅል›› እና ‹‹ጌሾ›› የሚዘጋጅ ፅዋ ‹‹አውዳሚነት›› በሚጎነጨው ብቻ የሚገደብ ነው ማለቱ ከታሪክ አለመማር ነው፡፡ አፄውን የበላው የወጣቶች ጎርፍ ነው፡፡ ደርጉንም ያንኮታኮተው ‹‹ወታደራዊ ሳይንስ የማያውቁ›› ተብለው ሲተቹ የነበሩ ተማሪዎች እና አርሶ አደሮች ናቸው፡፡ መቼም ከዚህ በላይ ይግባኝ የሌለው የታሪክ ብያኔ የትም የለም፡፡ ለዚህም ነው ጋዜጠኞቻችን ‹‹ዜና መዋዕል›› ከመፃፍ ወይም ከማይታይና ከማይዳሰሰው ‹‹ልማት›› የተጣባ ዜናቸው ባለፈ ሀገራዊ ጥቅምን ያቀነቅኑ ዘንድ ግድ የሚላቸው።
መቼም ለሀገራዊ ጥቅም እቆማለሁ ተብሎም፣ መስዋዕትነትም ተሸሽቶ የሚሆን ነገር አይደለም። በተቀረ ከይቅርታው ደብዳቤ ጀርባ በደን እንደተዋጠ ተራራ የተደበቀ አንዳች እንቆቅልሽ ለመኖሩ ግልፅ ነው። ሆኖም ዛሬ ይህ እንቆቅልሽ እንዲፈታልን አንጠይቅም። ነገ ግን ሌላ ቀን ነው። ምናልባትም ነገሩ ሁሉ ‹‹የነጋበት ጅብ ታሪክ››ን መልሶ ሊያመጣ ይችልም ይሆናል፡ ፡ ማን ያውቃል? ድሮ ድሮ በያ ትውልድ የትግል ዘመን፣ ትግላችን በሚባለው መጽሔት ላይ እንዲህ የሚል ግጥም ሠፍሮ ነበር።
‹‹ጐበዝ ዝም አትበሉ
ዝምታ ለበግም አልበጃት
አስራ ሁለት ሆና አንድ ነብር ፈጃት።››
ይህም እምቢይ ባዮች እልፍ እየሆኑ መሄዳቸው አይቀሬ ለመሆኑ ምሳሌ ነው፡፡ እውነትም ነው፡፡ መኢሶኖች ‹‹የየካቲቱ ገጣሚ›› እያሉ የሚንቆለጳጰሱት ያ ምርጡ ገጣሚ ዮሐንስ አድማሱ ያለውም፡-
‹‹አሉ ቁጢጥ ቁጢጥ፣
በሰማይ ደመና
ከእንግዲህ ቀረች
እንቅልፍና ጤና
መንግስት ብረት እንጂ አይገዛም ልቦና››ም እንዲሁ እውነት ነው፡፡ …ቀጣዩን የከርሞ ሰው ካለን የምናየው ይሆናል።
No comments:
Post a Comment