Thursday, July 5, 2012

ፓርላማው በአቶ መለስ ዜናዊ ህመም ምክንያት የመዝጊያ ፕሮግራሙን አራዘመ

የኢሳት አማርኛ ዜና » ፓርላማው በአቶ መለስ ዜናዊ ህመም ምክንያት የመዝጊያ ፕሮግራሙን አራዘመ

ፓርላማው በአቶ መለስ ዜናዊ ህመም ምክንያት የመዝጊያ ፕሮግራሙን አራዘመ

ሰኔ ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-99 በመቶ የአንድ ፓርቲ አባላት የተሰባሰቡበትና በምሁራን ዘንድ ” እጅ አውጭ”  እየተባለ የሚጠራው ፓርላማ በሕገመንግስቱ ከተደነገገው ውጪ የስብሰባ ጊዜውን በአንድ ሳምንት ማራዘሙን ምንጮቻችን ገለጹ፡፡
ፓርላማው በሕገመንግስቱ አንቀጽ 58 ንዑስ አንቀጽ 2 ላይ በተደነገገው መሰረት የዓመቱ ሥራው ተጠቃሎ የሚዘጋው ሰኔ 30 ቀን መሆኑን ደንግጓል፡፡ በየዓመቱ ለቀጣዩ ዓመት የሚቀርበው በጀት በም/ቤቱ አባላት ቀናት የወሰደ ጥልቅ ውይይት ከተካሄደበት በኃላ ጠ/ሚኒስትሩ በተገኙበት የማጠቃለያ ውይይት ተደርጎበት የሚጸድቅበት አሰራር እንደነበር ነገርግን ዘንድሮ ፓርላማውም ጊዜ ሰጥቶ በበጀቱ ላይ ካለመነጋገሩም በላይ ባልታወቀ ምክንያት በሕገመንግስት ጭምር የተደነገገ ቀን ተሸሮ ስብሰባዎች ከሰኔ 30 በኃላ መተላለፋቸውን ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡

እንደምንጮቻችን ገለጻ ከሆነ ፓርላማው ቀሪ ሥራዎቹን በቀጣይ ሳምንት ውስጥ አጠናቆ ለዕረፍት ይበተናል ተብሎ ተገምቷል፡፡ ይህም ሆኖ ግን ጠ/ሚኒስትሩ በፓርላማው መዝጊያ ሥነሥርዓት ላይ ይገኙ፣አይገኙ አሁንም የታወቀ ነገር የለም፡፡ ፓርላማው የስብሰባ ጊዜውን ለማራዘም የተገደደው ከአቶ መለስ ጤና ጋር ጋር በተያያዘ መሆኑን የገለጡት ምንጮች፣ የአቶ መለስ የጤና ሁኔታ ከፓርላማ ውጭ ያሉ ሌሎች የስራ አስፈጻሚ ስብሰባዎችም እንዲተላለፉ እየተደረገ መሆኑን ገልጠዋል።
አቶ መለስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያለው የጤናቸው ሁኔታ የህዝብ መነጋጋሪያ አጀንዳ ሆኗል። በርካታ ኢትዮጵያውያን አቶ መለስ በዚህ ሁኔታቸው ምናልባትም ለረጅም ጊዜ በስልጣን ላይ ላይቆዩ ይችላሉ ብለው ያስባሉ። የአቶ መለስ በሽታ መንስኤ በውል እይታወቅም። ደጋፊዎቻቸው በምግብ መመረዝ ታመዋል የሚሉ መልእክቶችን እየላኩ ሲሆን፣ ሌሎች ወገኖች ግን አቶ መለእ በጭንቅላት ህመም እየተሰቃዩ ነው ይላሉ። ኢሳት አቶ መለስ ወደ ሚታከሙበት ሆስፒታል በመደወል ለማጣራት ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም፣ አቶ መለስ የሚታከሙበትን ሆስፒታል ከማረጋጋጥ በስተቀር የሆስፒታሉ ሰራተኞች መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። የሆስፒታሉ ሰራተኞች ለኢሳት እንደተናገሩት አቶ መለስ በሆስፒታሉ የተመዘገቡት የኢትዮጵያ ጠቅላሚኒስተር ተብለው ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ አምባሳደር ተብለው ነው።
በሌላ የፓርላማ ዜና ደግሞ  አቶ መለስ ዜናዊ ለምርጫ ቦርድ አባልነት አሁን በሥራ ላይ ያሉት የቦርድ አባላት እንዲቀጥሉ ያቀረቡትን
የሹመት ጥያቄ የአትዮጽያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ብቸኛ የፓርላማ ተመራጭ ውድቅ አደርገውታል፡፡
በዛሬው ዕለት ለፓርላማው የሾሙአቸውን ሰዎች እንዲያጸድቁላቸው ጥያቄያቸውን  በጹሑፍ   ያቀረቡት አቶ መለስ ተሿሚዎቹ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻና ገለልተኛ መሆናቸውን ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በዚሁ መሰረት የምርጫ ቦርድ አባል እንዲሆኑ በጠ/ሚኒስትሩ የተሾሙት ፕሮፌሰር መርጋ በቃና- የቦርዱ ሰብሳቢ፣ዶ/ር አዲሱ ገ/እግዚአብሔር- ምክትል ሰብሳቢ፣ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ተገኔ ጌታነህ- አባል ፣ዶ/ር ማህሙድ አብዱላሂ-አባል፣ አቶ ፍቅረማርያም በረደድ- አባል፣ ወ/ሮ ሙሉ አባተ-አባል፣አቶ ዝናሬ ማሞ-አባል፣ አቶ አንለይ ኃይሌ-አባል፣ አቶ አላምረው ከበደ-አባል ናቸው፡፡
አቶ ግርማ ሠይፉ የመድረክ ብቸኛ የፓርላማ አባል ሰዎቹ በሥልጣን ዘመናቸው ብቃት እንደሌላቸው የተረጋገጠ በመሆኑ ፓርቲያቸው ሹመቱን እንደማይቀበለው ይፋ አድርገዋል፡፡
አቶ አስመላሸ ወ/ስላሴ የተባሉ አባል በሰጡት ምላሸ ተሿሚዎቹ ባለፉት አምስት ዓመታት ቦርዱን ነጻና ገለልተኛ፣ ለሕገመንግስቱ ታማኝ በመሆን ማገልገላቸውን በመጥቀስ የአቶ ግርማን ነቀፋ መሰረት የለውም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የጥርስ ሐኪሙና በፓርላማ ብቸኛ የግል ተመራጭ የሆኑት ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ የቦርዱ አባላት ነጻና ገለልተኛ ናቸው ሲሉ ለገዥው ፓርቲ ድጋፋቸውን ገልጸዋል፡፡ ሹመቱ በአንድ ተቃውሞ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል፡፡
ተቃዋሚዎች ምርጫ ቦርድ እንደገና እንዲዋቀር በተደጋጋሚ ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል።
______________________________________________________________

No comments:

Post a Comment