Thursday, July 19, 2012

ከኢትዮጵያ ወጣቶች ብሔራዊ ንቅናቄ የተሰጠ የአስቸኳይ ሃገራዊ ጥሪ

ከኢትዮጵያ ወጣቶች ብሔራዊ ንቅናቄ የተሰጠ የአስቸኳይ ሃገራዊ ጥሪ

by Eyouthm Abiyot on Thursday, 19 July 2012 at 10:25 ·
ከኢትዮጵያ ወጣቶች ብሔራዊ ንቅናቄ የተሰጠ የአስቸኳይ ገራዊ ጥሪ  

መላው የኢትዮጵያ ህዝብና የዓለም ማህበረሰብ እንደሚገነዘበው ሁሉ የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሔራዊ ንቅናቄም የአምባገነኑ የመለስ ዜናዊ ስርዓት እያከተመ እንደሚገኝ ይገነዘባል፡፡
የዓለማችን ተመሳሳይ ታሪኮች እንደሚዘክሩት ሁሌም በአምባገነኖች መዳፍ ስር የወደቁ ሃገራትና ህዝቦች ጨቋኞቻቸው ባልታሰበ ሁኔታ በሞት ሲሸኙ ቀጣዩ ሂደት በአብዛኛው ጊዜ እጅግ አሳዛኝና ወደባሰ አዘቅት ሲወስድ ታይቷል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ አልፎ አልፎ በአንዳንድ ሃገራት በህዝቦች በሳል ትግልና መስዋዕትነት እንዲህ አይነቱን ፈታኝ አጋጣሚዎችን በአግባቡ በመጠቀም ወደ ህዝባዊ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት በመቀየር መልካም የታሪክ ትሩፋቶች ሆነው አልፈዋል፡፡
ከዚህም ታሪካዊ እውነታ በመነሳት የአምባገነኑ መለስ ዜናዊ ስርዓት ውድቀትን ተከትሎ የሚፈጠረውን የስልጣን ሽኩቻ  ምን ያህል አሳሳቢ ሊሆን እንደሚችል በቀላሉ መገመት ይቻላል፡፡ አበው “ሌባ ሲሰርቅ ይስማማል፣ ሲካፈል ደግም ይጣላል” እንዲሉ ፤ በተለይም ሽኩቻው ላለፉት 21 ዓመታት በዙሪያው ባሰባሰባቸው ፈርጀ ብዙ ዘራፊ ቡድኖች መካከል ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ ይገመታል፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ይህ ዘረኛና እኩይ ሰው በማን አለብኝነትና በእብሪት በጎረቤት ሃገራት ላይ በወሰዳቸው አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነቶችና ወረራዎች ምክንያት ሃገራችንና ህዝባችን ሁሌም ለአደጋ እንዲጋለጡ አድርጓል፡፡ በዚህ ፈታኝ ወቅት የሚፈጠረውን ባለቤት አልባነት በንቃት የሚከታተሉና ለበቀል ያቆበቆቡ ጎረቤት ሃገራት የሁኔታውን አመቺነት በመጠቀም አሳፋሪ የታሪክ ጠባሳ ሊያሸክሙን ይችሉ ይሆናል፡፡
ከላይ ከተቀመጡት ግልፅ አደጋዎች በተጨማሪ እጅግ ብዙ አሳሳቢ ሁኔታዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሔራዊ ንቅናቄ ዋና አላማ አደጋዎችን ማመላከት ብቻ ሳይሆን በይበልጥ ይህንን የታሪክ አጋጣሚ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ በመጠቀም  በኢትዮጵያ ህዝባዊ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት በዘላቂነት  እንዲገነባ ማስቻል ነው፡፡
ይህንን እውነታ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድና በማስተዋል ከተጠቀምንበት ለእኛ ለኢትዮጵያውያንና ለምንወዳት ሃገራችን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ይከፍትልናል ብለን በፅኑ እናምናለን፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሔራዊ ንቅናቄ በዚህ ፈታኝ ወቅት ለምንመኘው ታሪካዊ ድል በጎ አስተዋፅኦ ሊያደርጉ ይገባል የሚላቸውን የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በአንድነት የሚያቀናጅ ሃገራዊ ጥሪ ከዚህ እንደሚከተለው  ያቀርባል፡፡


1ኛ. ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ
መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ፆታ፣ እድሜ፣ ሃይማኖት፣ ጎሳና፣ ዘር ሳይለይ ለአለፉት ዘመናት በተለይም በአምባገነኖቹና በጨካኞቹ የመንግስቱ ኃ/ማርያምና የመለስ ዜናዊ ስርአቶች እንደ ባእድ ወራሪ በገዛ ልጆቹና ሃገሩ የግፍ ግፍ ሲፈፀምበት፣ ምድሪቱም በደም ጎርፍ ስትታጠብና፣ ሁሉም በሚችለውና በአቅሙ እነዚህን የሰው አውሬዎች ከላዩላይ ለማስወገድ ሲኳትንና በመራራ ትግሉና በውድ ልጆቹ መስዋዕትነት የመጀመሪያውን ጭራቅ አስወግዶ ሁለተኛውን እኩይ ሲተካ ሃዘኑ ያልጠናበትና ፈጣሪውን ያላማረረ ኢትዮጵያዊ የለም፡፡
ይሁንና ሁልግዜም ታሪክ እንደሚዘክረውና ድርሳናት እንደሚነግሩን “በጨለማ የነበረ ህዝብ ብርሃን አየ” ነውና በጭቆና ውስጥ ያለን እኛ ኢትዮጵያውያን ይዋል ይደር እንጂ ነፃነታችንን መቀዳጀታችን ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ እነሆ ዛሬ የአምባገነኑ መለስ ዜናዊ ጨቋኝ ስርዓት የጀመረውን የግፍና የጥፋት መንገድ ሳያጋምስ በሃያሉ የኢትዮጵያ አምላክ እጅ ለፍርድ ተይዟል፡፡
ይሁን እንጂ ይህ እኩይ ስርዓት በህዝባችን መካከል የዘራቸው የጥላቻ፣ የበቀል፣ የክህደትና፣ የመለያየት መርዞች ስራቸውን እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ በተለይም የብሔርተኝነት፣ የጎሰኝነት፣ የጎጠኝነትና፣ ብሎም የመንደርተኝነት መርዙ ምን ያህል የከፋና የከረፋ መሆኑን በአለፉት 21 የሰቀቀንና የጭንቅ ዓመታት እሬት እሬት እያሉን አጣጥመናቸዋል፡፡ ይበልጡንም ወንድማችንና ጋሻችን የሆነውን ጨዋውን  “የትግራይ” ህዝብ በስሙ በመነገድ ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለመነጠልና ሌሎች ብሄረሰቦች በጠላትነት እንዲነሳሱበት ለማድረግ ያልተቆፈረ ጉድጓድና ያልተሸረበ ምድራዊ ሴራ አልነበረም፡፡ ነገር ግን የህዝባችን አንድነትና ፍቅር የተሸረበበት ድር የአለፉት እልፍ አእላፋት ትውልዶች ለአንድነትና ለነፃነት በተሰዋ ንፁህ ኢትዮጵያዊ ደም በመሆኑ የከፋፋዮቹ ህልም እስከ አሁኗ ሰአት ድረስ ሊሳካ አልቻለም፡፡ የተመኙትንም ኢትዮጵያን የማፍረስና ህዝቧን የማጫረስ ፋሽስታዊ ተልእኮና ህልም ሳያሳኩ ወደ ጥልቁ “በአቦሸማኔ” ፍጥነት እየተምዘገዘጉ ይገኛሉ፡፡
በአሁኑ ሰአት በሃገራችን የተፈጠረውን ታሪካዊ ክስተት የአምባገነኖች ቡድን እንዳይቀለብሰውና ወደ ህዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ሊደረግ የሚገባውን ታሪካዊ ጉዞ እንደለመዱት ለእኩይ አላማቸው መጠቀሚያነት እንዳያውሉት ህዝባችን ነቅቶ ሊጠብቅ ይገባል፡፡ ሁላችንም ልክ እንደ አባቶቻችን ሃገራችንና ህዝባችንን ከሁሉም ነገር በላይ በማስቀደም፤ በአንድነትና በፍቅር ፀንተን በመቆምና፤ በማስተዋል እኩዩ የመለስ ዜናዊ አገዛዝ የዘራውን የመጠፋፋት መርዝ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ከስር መሰረቱ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማፅዳት ታሪክ የጣለብን አደራና ፈተና ነው ብሎ የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሔራዊ ንቅናቄ በፅኑ ያምናል፡፡      
ስለዚህም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላቶቹ ያቀበሉትን የመለያየት አጀንዳ በማጥፍት፤ ለነፃነቱ መከበር በአንድነት በመቆም ለህዝባዊ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ምስረታ በፅኑ እንዲታገልና ከእጁ የገባውን ይህን ታሪካዊ አጋጣሚ ዳግም ለአምባገነናዊ ስርዓት አሳልፎ እንዳይሰጥ የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሔራዊ ንቅናቄ ወገናዊ ጥሪውን ከታላቅ አክብሮት ጋር ያቀርባል፡፡

2ኛ. ለሃይማኖት ተቋማት
“ኢትዮጵያ የሃይማኖት ደሴት ናት!” የዓለም ታሪክና ታላላቆቹ የየዕምነቱ መሪዎች ከተናገሩልን፤ የሃይማኖት ድርሳናትም በትልቁና በደማቁ ከከተቡልንና ዛሬም የዓለም ህዝቦች በአድናቆትና በግርምት ከሚመለከቱት ማንነታችን መካከል ዋነኛው  መገለጫችን ነው፡፡ እኛም ኢትዮጵያውያን በሁሉም ሃይማኖቶቻችን በመከባበርና በመቻቻል በአንድነት የኖርንባትና የምንኖርባት የቅድስት ሃገር ኢትዮጵያ ባለቤቶችና ጨዋ ህዝቦች መሆናችንን በኩራት የምንናገረው ሃቅ ነው፡፡ እንዲሁም ይህን ማንነታችንን በተለያየ ጊዜና ዘመናት ለአደጋ የሚያጋልጡ ክስተቶች እንደነበሩና አባቶቻችን በድል አድራጊነት እንደተወጡት እናውቃለን፡፡ እነሆም ዛሬ በእኛ ዘመን በተለያዩ አጋጣሚዎች ይህን ኩራታችንን ለመናድ የተለያዩ ትንኮሳዎችን አስተናግደናል፡፡ ይህም አልበቃ ብሎ የሃገሪቱን የመንግስት ስልጣን የያዘው የአምባገነኑ የመለስ ዜናዊ አስተዳደደር በሃይማኖት ተቋሞቻችንና ይዞታዎቻችን ቀጥተኛ ትንኮሳ፣ ወረራና፣ ግድያ ሲፈፅምብን ኖሯል፡፡እየፈፀመም ይገኛል፡፡ ይህንንም በእውነተኛና ታማኝ የሃይማኖት አባቶች፣ ምዕመናንና፣ ተቋማት ላይ ሲፈፀም የነበረውን ግፍና መከራ እስከ አሁን ድረስ በፅናት እየታገልን እንገኛለን፡፡ በዚህም ህዝባችን ድል እንደሚቀዳጅ እርግጠኞች ነን፡፡
ወገኖቻችን ! ዛሬ ሃገራችን ኢትዮጵያ እጅግ አሳሳቢ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች፡፡ ስለሆነም እንደ አንድ ኩሩና ጀግና ህዝብ በዚህ ሰአት ለገጠመን ሃገራዊ ፈተና ቅድሚያ በመስጠት እስከዛሬ በፅናት የታገላችሁላቸውን ሃይማኖታዊ ክብርና መብቶቻችሁን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በጋራ ያለምንምና ማንም ተፅዕኖ የምንጎናፀፈው በሃገራችን ሰላም፣ዲሞክራሲና፣ ፍትህ ሲረጋገጥ ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም ለዚህ ህዝባዊ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ቅድሚያ በመስጠት ትኩረታችሁን፣ ፀሎታችሁንና፣ ድጋፋችሁን በሃገራችን ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲመሰረት ለምንፈልገው ሁሉንም ወገኖች በእኩልነት የሚያሳትፍ ስርዓት ምስረታ ታደርጉ ዘንድ የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሔራዊ ንቅናቄ ወገናዊ ጥሪውን ከታላቅ አክብሮት ጋር ያቀርባል፡፡

3ኛ. ለፖለቲካ፣ ለሲቪክና፣ ለግብረ-ሰናይ ድርጅቶች በሙሉ
ለአለፉት ዘመናት ደከመንና ሰለቸን ሳትሉ ለሃገራችሁ እድገት፣ ለህዝባችሁ አንድነትና ነፃነት፣ እንዲሁም ለዲሞክራሲያዊ ህዝባዊ መንግስት ምስረታ ሌት ከቀን የባዘናችሁና በዱር በገደሉ የተንከራተታችሁ ውድ ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሲቪክ ተቋማት፣ ግብረ-ሰናይ ድርጅቶችና፣ የሙያ ማህበራት በሙሉ እነሆ የታገላችሁለትን አላማ አጨናግፎና እናንተንም ለእስር፣ ለአካል ጉዳተኝነት፣ ለስደትና፣ ለሞት ይዳርጋችሁ የነበረው የእኩዩ የመለስ ዜናዊ ስርዓት ህልውና እያከተመ ይገኛል፡፡
ምንም እንኳ ይህ የአምባገነኖች ስርዓት የመጨረሻው ስንብት ላይ ቢሆንም “ሌባ ሲሰርቅ…..” እንደሚባለው ሁሉ እየተፈጠረ ያለው የሃይል ሚዛን መዛባት የዘራፊውን ቡድን እርስ በእርስ እንደሚያባላቸውና አሸናፊው የአውሬው ክንፍ ዝርፊያውን ለማስቀጠል መንበሩን ለመያዝና መሪውን ወደ ፈለገው ለመጠምዘዝ እንደሚሞክር እሙን ነው፡፡
ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሔራዊ ንቅናቄ ከህዝቡ ጋር ካለው ቀጥተኛ ግንኙትና ተጨባጭ መረጃ በመነሳት የመለስ ዜናዊ የግፍ አገዛዝ ያንገሸገሸው ህዝባችን በሁሉም የሃገሪቱ ክፍሎች ህዘባዊው ቁጣ ሊፈነዳ ጫፍ ላይ የደረሰ መሆኑን  ያስገነዝባል፡፡ ስለሆነም እስከ ዛሬ ደንቃራ ሆኖ አንድነታችሁንና ህብረታችሁን የተፈታተነውን የንድፈ ሃሳብ ልዩነት ወደጎን በመተው ለማይቀረው ህዝባዊ ቁጣና ለህዝባዊ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ አፋጣኝ የጋራ አስተዋፅኦና ድጋፋችሁን ታበረክቱ ዘንድ የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሔራዊ ንቅናቄ ወገናዊ ጥሪውን ከታላቅ አክብሮት ጋር ያቀርባል፡፡

4ኛ. ለመምህራን፣ ለተማሪዎች፣ ለአርሶ አደሩ፣ ለሲቪል ሰራተኛውና፣ ለነጋዴው የህብረተሰባችን ክፍሎች በሙሉ
የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሔራዊ ንቅናቄ እስከዛሬ ድረስ የህልውናችን መሰረት በመሆን፤ ከትውልድ ትውልድ ታሪካዊ ሃላፊነታችሁን እየተወጣችሁ በተቻላችሁ መንገድና አቅም ሁሉ አምባገነኖችን በመታገል ላሳያችሁት ፅናትና ተጋድሎ ታላቅ አክብሮቱን ይገልፃል፡፡ በተመሳሳይ እንደ ቀደሙት ታሪካዊ ክስተቶች ሁሉ ዛሬም በጨካኙና በአምባገነኑ የመለስ ዜናዊ አገዛዝ መወገድ ተከትሎ ሊፈጠር የሚችለውን አለመረጋጋትና ህገወጥነትን በመገንዘብ አካባቢያችሁን፣ ሃገራችሁንና፣ ማህበረሰባችሁን ከማንኛውም ጥቃትና ምዝበራ ነቅታችሁ ትጠብቁ ዘንድ፤ እንዲሁም ለሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ በሚደረገው የህዝብ ትግል ፍፁም ሰላማዊ በመሆ መንገድ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የተለመደውን ታሪካዊ ግዴታችሁንና ሃላፊነታችሁን ትወጡ ዘንድ የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሔራዊ ንቅናቄ ወገናዊ ጥሪውን ከታላቅ አክብሮት ጋር ያቀርባል፡፡

5ኛ. ለሃገር መከላከያና ለፖሊስ ሰራዊቱ  አባላት
ለአለፉት 21 ዓመታት አምባገነኑ የመለስ ዜናዊ መንግስት ያደርስባችሁ በነበረው ከፍተኛ ተፅዕኖ ምክንያት በህዝባችን ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍና መከራ ስታስፈፅሙ እንደነበራችሁ ይታወቃል፡፡ ይሁንና ዛሬ የአምባገነኑ የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚወገድበት ወቅት መድረሱ እውን ሆኗል፡፡ ስለሆነም ይህ ታሪካዊ ክስተት ከማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል ይልቅ ለእናንተ ኢትዮጵያዊ ወገናችሁን ለመካስ የሚያስችል ልዩና መልካም አጋጣሚ ይዞላችሁ እንደመጣ እናምናለን፡፡
ይኃውም የሃገራችሁን ዳርድንበርና የህዝባችሁን ደህንነት በቅንነትና በታማኝነት የመጠበቅና የማገልገል ታላቅ ሃገራዊ ኃላፊነት በአግባቡ ትወጡ ዘንድ ያስችላችኃል ብለን እናምናለን፡፡ በተለይም በዚህ ወቅት ህዝባችሁንና ሀገራችሁን ከማንኛውም ጥቃትና አደጋ እንድትታደጉና ወደ ህዝባዊ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የሚደረገውን ፍፁም ሰላማዊ የህዝብ ትግል ከማንኛውም የአምባገነኖች ጥቃት ነቅታችሁ በመጠበቅና በመከላከል  አኩሪ ታሪክ ትሰሩ ዘንድ የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሔራዊ ንቅናቄ ወገናዊ ጥሪውን ከታላቅ አክብሮት ጋር ያቀርባል፡፡

6ኛ. ለብሔራዊ መረጃና ደህንነት አባላት
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የመረጃና የደህንነት አባላት ህዝብ የጣለባችሁን ወሳኝ ሃገራዊ አደራ በአግባቡ እንዳትወጡና አምባገነኑን መለስ ዜናዊንና ስርአቱን ለመጠበቅ ሲባል ብቻ በግዴታ የኢትዮጵያን ህዝብ በማሳደድ አስነዋሪ ተግባር ውስጥ እንድትዘፈቁ መደረጉን በአለፉት 21 ዓመታት በህዝባችን ላይ የተፈፀሙት ግፎች ያረጋግጣሉ፡፡ ነገርግን ዛሬ ያ የጨቋኙ የመለስ ዜናዊ አገዛዝ እንደሚወገድና በምትኩም ህዝባዊ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት የሚመሰረትበት አዲስ የታሪክ አጋጣሚ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ለእናንተም እኩል እየመጣላችሁ መሆኑን  እናምናለን፡፡
ስለሆነም እናንተም ይህን ታሪካዊ አጋጣሚ በአግባቡ በመጠቀም መላው ህዝባችሁንና ኢትዮጵያ ሃገራችሁን ከማንኛውም የውስጥና የውጭ ጥቃት በንቃት በመጠበቅ፣ እንዲሁም አሁን በጨቋኙ የመለስ ዜናዊ ስርዓት ውስጥ የተፈጠረውን የሃይል ክፍተት በመጠቀም በሃገራችን ውስጥ ሊከሰት የሚችለውን የስርዓት አልበኝነት ትከላከሉ ዘንድ ከወዲሁ ልናሳስብ እንወዳለን፡፡ በአጠቃላይ ህዝባችን ለሚያደርገው ፍፁም ሰላማዊ የሆነ የህዝባዊ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ መንግስት ምስረታ ሂደት የበኩላችሁን አስተዋፅኦ በማበርከት ታሪካችሁን በክብር መዝገብ ላይ ታሰፍሩ ዘንድ የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሔራዊ ንቅናቄ ወገናዊ ጥሪውን ከታላቅ አክብሮት ጋር ያቀርባል፡፡

  7ኛ. ለጋዜጠኞችና ለሚዲያው ማህበረሰብ በሙሉ
ከአምባገነኑ የመለስ ዜናዊ አውሪያዊ አገዛዝ ጋር ፊት ለፊት በመጋፈጥ ለእውነት፣ ለዲሞክራሲ፣ ለፍትህና፣ ለነፃነት አኩሪ ተጋድሎ እያደረጋችሁ ለምትገኙት ክቡራንና ክቡራት የኢትዮጵያ ነፃ ሚዲያ አባላት፤ እንዲሁም አቅማችሁ በፈቀደው ሁሉ መረጃ በመስጠትና በማስተለላለፍ ለተሳተፋችሁ “የእውነት ብርሃኖች” ሁሉ ዛሬ በሃገራችን እየተፈጠረ የሚገኘውን አዲስ የታሪክ ክስተት በንቃት እየተከታተላችሁ እንደምትገኙ እናምናለን፡፡
እንደሚታወቀው ምንም እንኳ የአምባገነኑ የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ፍፃሜ የተቃረበ ቢሆንም ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ሃገራችንን ወደ አዲስ የነፃነት፣ የዲሞክራሲና፣ የፍትህ ምዕራፍ ለማሸጋገር ይቻል ዘንድ በሁሉም አቅጣጫ ብልህነት የተሞላበት አካሔድ እንደሚያስፈልገው  አያጠራጥርም፡፡
ስለሆነም ይህንን ታሪካዊ ክስተት ተከትሎ የሚከሰተውን ውጥንቅጥ በማጋለጥና በማጥራት፤ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ህዝብና ለዓለምዓቀፉ ማህበረሰብ ትክክለኛና ሚዛናዊ መረጃ በወቅቱ በማድረስ ህዝባችን ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለሚያደርገው የህዝባዊ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ትግል የበኩላችሁን አስተዋፅኦ በማድረግ የዜግነት ግዴታችሁን ትወጡ ዘንድ የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሔራዊ ንቅናቄ ወገናዊ ጥሪውን ከታላቅ አክብሮት ጋር ያቀርባል፡፡

8ኛ. ለመላው ኢትዮጵያ ወጣቶች ብሔራዊ ንቅናቄ አባላትና ደጋፊዎች፤ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ወጣቶች በሙሉ
ለአለፉት 21 ዓመታት ሲያሰቃየን የኖረው እኩዩ የመለስ ዜናዊ አገዛዝ እያከተመለት እንደሚገኝ እርግጥ ነው፡፡ በመሆንም ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወጣት ከፊት ለፊታችን ተሰቅሎ የሚታየንን የአምባገነኖችን ዘላለማዊ የጨለማና የውርደት መቃብር በጉጉትና በተስፍ እየተመለከትን፤ ከውልደታችን ጀምሮ የምንናፍቀውንና የምንጓጓለትን ነገር ግን ልናየውና ልንኖርበት የተከለከልነውን ህዝባዊ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት የመገንባት መልካም አጋጣሚ በእጃችን እንደገባ የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሔራዊ ንቅናቄ ይረዳል፡፡ እንዲሁም ከሁሉም በላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ያለምንም ገደብና ቅደመ ሁኔታ በእኩልነት፣ በነፃነትና፣ በፍትሃዊነት የምንኖርባትን ታላቋን ኢትዮጵያ ማየት የወጣቱ ትውልድ ታለቅ ራዕይ መሆኑንና  የመገንባቱም ዕጣ-ፋንታ ዛሬ በትክሻው ላይ እንደወደቀ እናምናለን፡፡
ነገርግን እስከ አሁን ድረስ እግር በእግር እየተከተለ የነፃነት፣የፍትህ፣የእኩልነትና፣ የዲሞክራሲ ፍላጎትና ተስፋችንን እያመከ የሚገኘው የአምባገነኖች ርዝራዥ ሃይል ተጠቃሎ ከእነ እኩይ ምግባሩና ሴራው ከሃገራችንና ከህዝባችን ጫንቃ እስኪወገድ ድረስ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ የትግል መስክ እንደ አቅማችንና ችሎታችን ተሰልፈን በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ መስዋዕትነት እየከፈልን የምንገኝ ወጣቶች ሁሉ ወደ ዲሞክራሲያዊ ህዝባዊ ስርዓት ግንባታ የሚደረገው ጉዞ ግቡን እስኪመታ ድረስ በፅናትና በቁርጠኝነት ትግላችንን ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ እስከመጨረሻው እንድንቀጥል የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሔራዊ ንቅናቄ ለማሳሰብ ይወዳል፡፡ ስለሆነም በዚህ የታሪክ አጋጣሚ በአምባገነኖች መንደር ሊፈጠር የሚችለውን ትርምስ ተገንዝበን ለውጡ “የጉልቻ መለዋወጥ” ብቻ ላይ ተገድቦ ሂደቱ ዳግም የትውልድ ተስፋችንን  እንዳያጨልምብንና ዳግመኛ ሃገራችን በሌላ አምባገነናዊ ስርዓት እንዳትጠለፍ ሂደቱን በንቃት በመከታተልና ባሉት ፍፁም ሰላማዊ እንቅስቃሴዎች በሙሉ ግንባር ቀደም ተሳታፊዎች በመሆን ሃገራችንን ወደ ምንመኘው ህዝባዊ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ  ስርዓት ለማሸጋገር በአንድነት እንድንቆም የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሔራዊ ንቅናቄ ወገናዊ ጥሪውን ከታላቅ አክብሮት ጋር ያቀርባል፡፡
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!
የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሔራዊ ንቅናቄ!

No comments:

Post a Comment