Friday, April 20, 2012

ሙስሊሞች ዛሬ በአወልያ መስጊድ ተገኝተው ተቃውሞአቸውን አሰሙ

ሚያዚያ ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በብዙ መቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሙስሊሞች ዛሬ በአወልያ መስጊድ ተገኝተው ተቃውሞአቸውን አሰሙ::
 በዛሬው የጁመዓ ጸሎት እጅግ በርካታ ቁጥር ያለው ሙስሊም ተገኝቶ በተለይ አቶ መለስ በቅርቡ ያደረጉትን ንግግር  መቃወሙን የደረሰን ዜና ያመለክታል። ወጣቱ፣ ጎልማሳው አዛውንቱ የአቶ መለስ ንግግር ክርስቲያኑን ከሙስሊሙ ለማጋጨት ሆን ተብሎ የቀ ረበ መሆኑን በመረዳት በተለያዩ መንገዶች ተቃውሞውን ሲገልጽ ተሰምቷል።
ከአራት ቀን በፊት አቶ መለስ ዜናዊ በፓርላማ ቀርበው ባደረጉት ንግግር ላይ ህዝበ ሙስሊሙ ቅሬታ የተሰማው መሆኑን የገለጹልን አንድ ታዋቂ ሙስሊም፣  ሰውየው ሆን ብለው ህዝቡን የሌለ ሥጋት በመፍጠር በሃይማኖት ለመከፋፈል የሚያመቻቸውን ንግግር ብለዋል። ታዋቂው ሙስሊም ከእንግዲህ በየመስኪዶች በምናደርገው የተቃውሞ ስብሰባ ላይ ፈቃደኛ የሆኑ ክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ተገኝተው ፣ መንግሥት በሀሰት የሚጭንብን ክስ መሠረት የሌለው እና በሠላማዊ መንገድ ሃይማኖቴን በመንግሥት ሰዎች ምርጫ ሳይሆን ራሳችን በመረጥናቸው ዑላማዎችና የአህባሽን ሳይሆን እስልምና የሚለንን ዶክትሪን እናምልክ፣  የሚል መሆኑን እንዲያረጋግጡ እንጠይቃለን “ብለዋል፡፡
በየመስኪዱ አቅራቢያ የሚገኙ የአጥቢያ ቤተክርስቲያን ክርስቲያኖችም ጥሪ ተላልፎላቸዋል ሲሉ ለኢሳት ዘጋቢ ገልጠዋል።
በአስኮ አቅራቢያ የምትኖረው ኢክራም ሞሀመድ በበኩሏ “እኔ መምህርት እና ሙስሊም ነኝ፣ ጠ/ሚንስትሩ በፓርላማ ቀርበው ንግግር ያደርጋሉ ሲባል ስለመምህራንና ስለሙስሊሙ ማህበረሰብ ያላቸውን ግንዛቤና አዎንታዊ የመፍትሄ ምላሻቸውን አደምጣለሁ ብዬ ጓጉቼ ነበር ፤ ሆኑም ተራ ቅጥፈት፣ ዛቻ፣ ማስፈራራያ፣ ንቀት እና እውነታውን በማድበስበስ ጥያቄዎቹን የጥቂቶች የማስመሰልና የማደፋፈን ንግግር ነው ያደረጉት፣ እንዲያውም እኛን በዘወርዋራ መንገድ የክርስቲያኖች ስጋት ሁሉ አስመስለው አቀረቡን ስለዚህ ይህ ሀሰት መሆኑን ለማሳየት ስብስባችን ላይ ክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንዲገኙ እየጠየቅን” ነው ብላለች፡፡
ሌላ ወጣት ደግሞ ተቃውሞው ከእንግዲህ በመላ አገሪቱ በሚደረጉት መስኪዶች ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን፣ መንግስት የፈለገውን የሀይል እርምጃ ቢወስድ ወደ ሁዋላ እንደማይመለሱ ገልጦ፣ መንግስት ጥያቄውን በሀይል ለመጨፍለቅ የሚያደርገው ሙከራ ህዝቡን ይበልጥ እያስቆጣ የሚሄድ እንጅ የሚያረጋጋው አይሆንም ብሎአል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፈው ዓርብ ቃሊቲ ቻራሊያ አቅራቢያ በሚገኘው መስኪድ ውስጥ መጅሊስ አይወክለንም የሚል ቲሸርት የለበሱ ሙስሊሞችን የፌዴራል ፖሊስ ከመስኪድ እያስወጣ በቁጥጥር ሥር እንዳዋላቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡
____________________________________________________________________________________________________________________________________

No comments:

Post a Comment