Tuesday, April 24, 2012


የግልገል ጊቤ አደጋ የሙስና ውጤት መሆኑን ጥናቶች አመለከቱ

ሚያዚያ ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የግልገል ጊቤ አንድ በደለል የመሞላት ዜና ይፋ ከመደረጉ በፊት፣  አደጋ ሊፈጠር እንደሚችል በመንግስት እና መንግስታዊ ባልሆኑ ደርጅቶች የተጠኑ ጥናቶች ማመላከታቸውን መረጃዎች አሳይተዋል።
በግድቡ ዙሪያ የተጠኑ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ግድቡ ስራ ከመጀመሩ በፊት የኢትዮጵያ መብራት ሀይል በደለል ዙሪያ ያካሄደው ጥናት ግድቡ ለመጪዎቹ 50 አመታት አገልግሎት እንደሚሰጥ ይሁን እንጅ የአካባቢ እንክብካቤ ከተደረገ ለ70 አመታትም አገልግሎት እንደሚሰጥ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ መብራት ሀይል ያስጠናው ጥናት በገለልተኛ ወገን እንዲመረመር ሳይደረግ መንግስት ስራው እንዲጀመር ትእዛዝን ማስተላለፉ ታውቋል። ይህ 40 ሜትር ከፍታ ያለው እና 180 ሜጋ ዋት ሀይል የሚያመነጨው ግድብ ከአለም ባንክ ፣ ከአውሮፓ ህብረት፣ ከኦስትሪያ መንግስትና ከኢትዮጵያ መንግስት በተገኘ ገንዘብ ወጪው እንዲሸፈን ተደርጓል። ግልገል ጊቤ አንድን ለመገንባት በአጠቃላይ የወጣው ወጪ 280 የአሜሪካን ዶላር ሲሆን፣ ግድቡን ያለምንም ጫረታ የሰራው ደግሞ የጣሊያን ኩብንያ የሆነው ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ነው።
10ሺ ቤተሰቦች ያለምንም በቂ ካሳ እንዲፈናቀሉ የተደረገበት ፕሮጀክት በአፈር ደለል በመሞላት በሚቀጥሉት አመታት የሀይል ማመንጫው ሙሉ በሙሉ ሊቆም እንደሚችል በጅማ ዩኒቨርስቲ የሚሰሩ ምሁራን እና የውጭ አገር ምሁራን ጥናታዊ ወረቀቶችን አቅርበው ነበር። ይሁን እንጅ መንግስት እነዚህን ጥናቶች ከግምት ሳያስገባ ሁለተኛው የግልገል ጊቤ ፕሮጅክት እንዲጀመር አድርጓል።
26 ኪሎሜትር በሚደርስ ረጅም የውሀ ማስተላለፊያ ቦይ ተሰርቶለት የተገነባው ግልገል ጊቤ ሁለት ውሀውን የሚያገኘው ከግልገል ጊቤ አንድ በመሆኑ የግልገል ጊቤ አንድ ችግር በግልገል ጊቤ ላይም አደጋ ማስከተሉ አይቀሬ መሆኑን ጥናቶች ያመለክታሉ። ፒ ኤች ኢ ኢትዮጵያ ከጅማ ዩኒቭረስቲ ጋር በጋራ በመሆን በ2012 ባዘጋጀው ወርክሺፕ ላይ ጥናታቸውን ያቀረቡ ምሁራን በመጨረሻ ባወጡት መግለጫ ” ግልገል ጊቤ አንድ ለተደቀነበት አደጋ የማስተከከያ እርምጃ በአፋጣኝ ካልተወሰደ በስተቀር ይህ ጠቃሚ እና ታላቅ ፕሮጀክት በአጭር ጊዜ ውስጥ ከጥቅም ውጭ ይሆናል።” ሲሉ አስታውቀዋል።
የግልገል ጊቤ አንድ ፕሮጀክት በደለል የመሞላት አደጋ አንዣቦበት እያለ መንግስት 490 ሚሊዮን ዶላር በማውጣት ለምን የግልገል ጊቤ ቁጥር እንዲጀመር አደረገ ለሚለው ጥያቄ፣ የተለያዩ ጥናታዊ ወረቀቶች ችግሩን ወደ ጣሊያናዊው ኩባንያና ወደ ኢትዮጵያ መንግስት ያዞሩታል። ጣሊያን አገር በሚገኘው ” ሲአርቢኤም እና ቼክ አገር በሚገኘው ሲኢኢ ባንክ ወች ኔት ወርክ” ዘ ግልገል ጊቤ አፌር ወይም የግልገል ጊቤ ጉዳይ በሚል የተጠና ጥናት በግልገል ጊቤ ዙሪያ የጣሊያን መንግስት ከኢትዮጵአ መንግስት ጋር በመመሳጠር የፈጸመው ታላቅ ሙስና በምርመራ ላይ እያለ ተዳፍኖ መቅረቱን ይፋ አድርጓል።
በዚሁ ጥናት መሰረት የኢትዮጵያ መንግስት የግልገል ጊቤ ሁለትን ግንባታ  ያለምንም አለማቀፍ ጫረታ በድጋሜ ለሳሊኒ ኮንስትራክሽን እንዲሰጠጥ ሲያደርግ፣ አብዛኛው የግንባታ ወጪ የጣሊያን መንግስት ለኢትዮጵያ በሰጠው ብድር እንዲሸፈን ተደርጓል። የጣሊያን መንግስት ለግድቡ ግንባታ የሰጠው 220 ሚሊዮን ዶላር አገሪቱ እስከ ዛሬ ለውጭ ኢንቨስትመንት ካበደረችው ገንዘብ ሁሉ የሚበልጥ በመሆኑና የብድር ስርአቱ ግልጽነት የጎደለው በመሆኑ፣ የጣሊያን ፓርላማ አባላት የሆኑት ካሊዚዮ ላ ኢዮ እና ስፒኒ  በኖቬምበር 2005  ጥያቄ በማንሳታቸው ምክትል ዋና ጸሀፊ የሆኑት ሉጊይ ማንቲካ የተሸፋፈነ መልስ በመስጠት አልፈውታል። በ2006 ደግሞ ሌቪን፣ ማርቶኒ፣ ቶኒኒ እና ሌሎችም የፓርላማ አባላት ጉዳዩ እንዲመረመር በድጋሜ ጥያቄ አቅርበዋል። በማርች 2006 የሮም አቃቢ ህግ በግልገል ጊቤ ብድር አሰጣጥ ዙሪያ ተፈጸመ ያለው ወነጀል እንዲመረመር ፋይል ከፍቷል። ጉዳዩ በሚስጢር የተያዘ በመሆኑ እስካሁን ድረስ የምርመራ ውጤቱ ለህዝብ ይፋ አልሆነም። የጣሊያን መንግስትለግድቡ ግንባታ የሰጠው ብድር ግልጽነት የጎደለው መሆንና ብድሩ ኢትዮጵያን በእዳ አሁን ካለችበት ደረጃ ወደ ባሰ ደረጃ የሚያወርዳት ይሆናል የሚል ተቃውሞ ሲቀርብበት የ300 ሚሊዮን ዶላር የእዳ ስረዛ አድርጓል።
በግልገል ጊቤ አንድና ሁለት መካከል ያለው ውዝግብ ሳይቋጭ መንግስት አወዛጋቢውን የግልገል ጊቤ ሶስት መጀመሩ ይታወቃል። 
ሳሊኒ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በተዋዋለው ውል መሰረት በግድቡ ዙሪያ በሚፈጠር ተፈጥሮአዊ ክስተት ወይም ግድቡ በደለል ቢሞላ ምንም አይነት ካሳ እንዳይከፍል የሚያደርገው ነው። በዚህም መሰረት  በግድቡ ዙሪያ የተደቀነው አደጋ አፋጣኝ መፍትሄ ሳይሰጠው ከቀረ ኢትዮጵያ ለዘመናት ከፍላ በማትጨርሰው እዳ መዘፈቅ ብቻ ሳይሆን ግድቡ ሰው ሰራሹ ሀይቅ በአካባቢው ህዝብ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት በገንዘብ ሊተመን የማይችል ይሆናል ሲሉ ምሁራን አስጠንቅቀዋል። ይሁን እንጅ ምሁራን እንደሚሉት ግድቡን በደለል ከመሞላት ለመታደግ ስራው ቀደም ብሎ መጀመር ነበረበት ይላሉ። የአካባቢው ሰዎች ከግድቡ ክልል እርቀው ከብቶቻቸውን እንዲያረቡ፣ የእርሻ ስራም እንዲሰሩ የመፍትሄ ሀሳብ ምሁራን ያቀረቡ  ቢሆንም፣ የተፈናቀሉት የአካባቢው ነዋሪዎች ግን ከብቶቻቸውን የሚያሰማሩበት ቦታ በማጣታቸው በግድቡ አካባቢ ከብቶቻቸውን ማሰማራት እና የእርሻ ስራ መስራታቸውን ቀጥለዋል። አሁን እየተከማቸ የመጣውን ደለል ለመጥረግ ወጪው የሚቻል አለመሆኑንም ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ መንግስት ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል ያለመንም በቂ ጥናት የጀመራቸው የሀይል ፕሮጀክቶች ለአገሪቱ ትልቅ አደጋ እንደደቀኑ ይነገራል። የአባይ ግድብም ተመሳሳይ አደጋ ይዞ እንደሚመጣ ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ። “ግልገል ጊቤ አንድ በደለል ሳቢያ ቢዘጋ፣ ግልገል ጊቤ ሁለት እና ሶስትም ላይ ተመሳሳይ አደጋ ይፈጠራል፣ እነዚህን ግድቦች ለመስራት መንግስት ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ተበድሯል ፣ ይህን ገንዘብ ማን ይሆን የሚከፍለው ፣ እስከ ዛሬ ለደረሰው ጉዳትና ለሚደረስው ጉዳትስ ሃላፊነቱን የሚወስደው ማን ነው?” በማለት ምሁራን ጥያቄዎችን ያቀርባሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ እንደ አማራ እና ትግራይ ክልሎች ሁሉ አዲስ አበባ መስተዳደርም ለአባይ ግድብ ግንባታ እያንዳንዱ ነዋሪ ቦንድ እንዲገዛ  ሊያስገድድ መሆኑ ተስምቷል። ህዝቡ ለግድቡ ግንባታ ያለው ተነሳሽነት ከመቼውም ጊዜ በላይ በቀነሰበት በአሁኑ ወቅት፣ ከኑሮው ውድነት ጋር ተያይዞ ማህበራዊ ቀውሱን ያባብሰዋል ተብሎ ተስግቷል።

No comments:

Post a Comment