ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል የባለቤቷን ሽልማት ልትቀበል ነው
ሚያዚያ ፳ (ሃያ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ምኢሳት ዜና:-የ2012 የፔን ባርባራ ጎልድ ስሚዝ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት አሸናፊ በሆነው በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ሽልማት ሥነ-ስርዓት ላይ ባለቤቱ ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል እንደምትገኝ ምንጮቹን በመጥቀስ የዘገበው አዲስ ቪው ነው።
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ሀሳቡን በነፃነት በመግለጹ ሳቢያ በፈጠራ የሽብርተኝነት ተከሶ ጉዳዩን በፍርድ ቤት እየተከታተለ ባለበት በአሁኑ ወቅት “ፔን ፍሪደም አዋርድ” የተባለውንና ለጀግና ጋዜጠኞች የሚሰጠውን ዓለም አቀፍ ሽልማት አግኝቷል።
ፔን አሜሪካን ሴንተር የተባለው ዓለማቀፍ ድርጅት ጋዜጠኛ እስክንድር ለሰራቸው ስራዎች እውቅና በመስጠት ፤26ኛው የድርጅቱ ሽልማት ለጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እንዲሆን ከቀናት በፊት መወሰኑ ይታወሳል።
ይኸው “ፔን አሜሪካን ሴንተር”የተሰኘው ድርጅት በሚያዘጋጀው እና እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር የፊታችን ሜይ 1 ቀን 2012 በኒውዮርክ ሲቲ በሚገኘው በ “አሜሪካን ሙዚየም ኦፍ ናቹራል ሂስትሪ’ በሚካሄደው የሽልማት ፕሮግራም ላይ፤ ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል በተጋባዥነት በመገኘት የባለቤቷን ሽልማት ትቀበላለች ተብሎ ይጠበቃል።
ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል የዓለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተንከባካቢ ድርጅት በምህፃረ-ቃሉ የሲ.ፒ.ጄ የ 2007 ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ዓለማቀፍ ሽልማት አሸናፊ መሆኗ ይታወቃል።
የእስክንድር እና የሰርካለም ብቸኛ ልጃቸው ህፃን ናፍቆት እስክንድር፤ አባቱ እና እናቱ የ1997ቱን ምርጫ ተከትሎ ከቅንጅት አመራሮችና ከሌሎች ጋዜጠኞች ጋር ለሁለት ዓመታት በታሰሩበት ወቅት በቃሊቲ እስር ቤት መወለዱ ይታወቃል።
የዛሬ ዓመት አካባቢ ፖሊሶች ጋዜጠኛ እስክንድርን ዳግም እያዋከቡ ወስደው ያሠሩት፤ መንገድ ላይ ሲያጫውተው ከነበረው ከህፃን ልጁ ከናፍቆት ነጥለው እንደነበር ይታወቃል።
ህፃን ናፍቆት ፖሊሶች አባቱን እያዋከቡ ሲወስዱበት ፦”አባባ!አባባ!>>” እያለ ስቅስቅ ብሎ እንዳለቀሰ መዘገቡ አይዘነጋም።
No comments:
Post a Comment