June 3, 2013 by
(ዘ-ሐበሻ) ዛሬ ማለዳ በአዲስ አበባ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በመወጣት ድምጻቸውን ካሰሙ በኋላ የኢሕአዴግ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ሬድዋን ሁሴን ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ “ፓርቲው ህገ መንግስቱን በመጣስ በሃይማኖት እጁን መክተቱና በህግ የበላይነት አምናለሁ እያለ በፍርድ ቤት ጉዳያቸው የተያዘባቸው ሰዎች በሁካታ ይፈቱልን ማሰኘቱ ተጠያቂ ያደርገዋል” አሉ።
አቶ ሬድዋን በፍርድ ቤት ሽብርተኛ የተባሉ ሰዎችን ሰማያዊ ፓርቲ እንዲፈቱለት መጠየቁ አግባብ አይደለም ካሉ በኋላ “የሃይማኖት አክራሪነትን አጀንዳው አድርጎ ሲንቀሳቀስ የነበረው ሰማያዊ የፖለቲካ ፓርቲ ጸረ ህገ መንግስታዊ እንቅስቃሴው ዛሬ በጠራው ሰልፍ ተጋልጧል ብሎ ኢህአዴግ ያምናል።” በማለት የፓርቲው ሰዎችን ለማሰር ያለውን እቅድ ፍንጭ ሰጥቷል።
የኢሕአዴግ መንግስት በተለያዩ ጊዜያት በልምድ እንደታየው ግለሰቦችን ማሰር ሲፈልግ “ሕገመንግስቱን” እንደሚጠቅስ የሚያስታውሱት የፖለቲካ ተንታኞች ኢሕአዴግ ይህን “ሰማያዊ ያዘጋጀውን ሰላማዊ ሰልፍ ላልተፈለገ አላማ አውሎታል” ሲል መግለጹ እንደተለመደው ሰበብ ፈልጎ ለማሰር ያለውን እቅድ ያሳየ ነው ብለውታል።
አቶ ሬድዋን በመግለጫቸው “በሰልፉ በአብዛኛው የተንጸባረቀው የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ይፈቱ እየተባለ መስተጋባቱ፤ ፓርቲው ህገ መንግስቱን በመጣስ በሃይማኖት እጁን መክተቱና በህግ የበላይነት አምናለሁ እያለ በፍርድ ቤት ጉዳያቸው የተያዘባቸው ሰዎች በሁካታ ይፈቱልን ማሰኘቱ ተጠያቂ ያደርገዋል” ሲሉ በግልጽ መናገራቸውን የተመለከቱ የፖለቲካ ተንታኞች ስርዓቱ ይህን አይነት መግለጫ የሚሰጠው ከፍራቻ እንደሆነ ተናግረዋል።
የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት በበኩላቸው ለመንግስታዊ ሚዲያዎች ሰጡት በተባለው አስተያየት በሃይማኖት ውስጥ ችግር አለ እስከተባለ ድረስ እና የታሰሩ ሰዎች እስኪፈቱ ድረስ ፓርቲው ትግሉን ይቀጥላል ብለዋል። በዛሬው በሰልፉ በቅርቡ በቤንሻንጉል ክልል እንግልት የደረሰባቸው የአማራ ክልል አርሶ አደሮች አደሮች ጉዳይ ፣ በአሸባሪነት ተጠርጥረው የታሰሩ የፖለቲካ መሪዎችና የህዝበ ሙስሊሙ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት እንዲሁም የጋዜጠኝነት ሙያቸውን በአግባቡ በመወጣታቸው የተወነጀሉ ጋዜጠኞች ከእስር ይፈቱ የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡
በየትኛውም አካባቢ ተዘዋውረን የመኖር መብታችን ይከበርልን ፣ ህገ መንግስቱን የሚቃወሙ አፋኝ አዋጆች ይሰረዙልን ብለዋል ሰልፈኞቹ ሲሉ የመንግስት መገናኛ ብዙሃንም ዛሬ ጠዋትም ዘ-ሐበሻ መዘገቧ ይታወሳል።
No comments:
Post a Comment