Wednesday, April 17, 2013

የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች ኤምባሲዎችን መጠለያ እየጠየቁ መሆኑ ተጠቆመ




-    የቀን ተማሪዎች እንዳይማሩ ኮሌጁ ተዘግቷል
-    በረሃብ አድማው ምክንያት ተማሪዎች ሆስፒታል ገብተዋል
-    ልብሳቸውን አንጥፈው መለመን ጀምረዋል

በመሀል አራት ኪሎ የሚገኘውና ለበርካታ ዘመናት መንፈሳዊ ትምህርት በማስተማር፣ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ መንፈሳዊ ምሁራንን ባፈራው የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ በቀን ተማሪዎችና በኮሌጁ ኃላፊዎች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት እየከረረ በመሄዱ፣ ተማሪዎቹ የኮሌጁን ግቢ ለቀው እንዲወጡ በመታዘዛቸው አንዳንድ ኤምባሲዎች መጠለያ እንዲሰጧቸው ደብዳቤ እየተጻጻፉ መሆኑ ተጠቆመ፡፡
7db105d1665f3ec4571b586cee2f157f_Lተማሪዎቹ በየካቲት ወር በኮሌጁ ውስጥ ይፈጸማሉ ያሏቸውን ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶች ማለትም የምግብ አቅርቦት፣ የትምህርት አሰጣጥ፣ አግባብ ያልሆነ ንብረት አያያዝና ሌሎችም ድርጊቶች እንዲስተካከሉ ለአዲሱ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ደብዳቤ በማቅረብ፣ ምላሽ እስከሚያገኙ ድረስ ትምህርት አቁመው እንደነበር ይታወሳል፡፡

ጉዳዩ በኮሚቴ እንደሚታይና እስከዚያው ድረስ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ በተላለፈላቸው ትዕዛዝ መሠረት፣ ተማሪዎቹ ያቋረጡትን ትምህርት በመከታተል ላይ እያሉ፣ የሌላ ሃይማኖት ተከታይ መምህር ተመድበዋል በማለት፣ ‹‹ከሃይማኖታችን ውጭ ሌላ ሃይማኖት ያለው ሰው ሊያስተምረን አይገባም›› ማለታቸውን ተከትሎ አለመግባባቱ መካረሩ ታውቋል፡፡

 ‹‹አንዳንድ መምህራን ሊያስተምሩን አይችሉም ስላላችሁ ከማስተርስና የማታ ተማሪዎች በስተቀር ግቢውን ለቃችሁ ውጡ፤›› መባላቸውንና ከመጋቢት 30 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ ትምህርት ሙሉ በሙሉ ማቆማቸውን አንዳንድ ያነጋገርናቸው ተማሪዎች ገልጸዋል፡፡


የረሃብ አድማ ካደረጉ አንድ ወር እንዳለፋቸውና ችግራቸውን ገልጸው በደብዳቤ ካሳወቋቸው ከቅዱስ ሲኖዶስ፣ ከፓትርያርኩ፣ ከተወካዮች ምክር ቤት፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ ከፌዴሪል ጉዳዮች ሚኒስቴር፣ ከሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ከፀረ ሙስና ኮሚሽንና ከሌሎች የሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች ምንም ምላሽ በማጣታቸው፣ አንዳንድ ኤምባሲዎች መጠለያ እንዲሰጧቸው ደብዳቤ እየተጻጻፉ መሆኑን ያነጋገርናቸው ተማሪዎች አረጋግጠዋል፡፡

ኃላፊነትን መውሰድ ፈርተው ወይም ከብዷቸው ክብ ማህተም በማድረግ ብቻ በተለጠፈ ደብዳቤ ግቢውን ጥለው እንዲወጡ መታዘዛቸውን የሚናገሩት ተማሪዎቹ፣ ላለፉት ቀናት ምዕመናኑ በሚሰጧቸው ዳቦና ሙዝ መክረማቸውን ገልጸዋል፡፡
በረሃብ አድማው የተጐዱና አቅም አንሷቸው ተዝለፍልፈው የወደቁ ሁለት ተማሪዎች ትናንትና ወደ የካቲት 12 ሆስፒታል መወሰዳቸውን የሚናገሩት ተማሪዎቹ፣ ‹‹ኮሌጁን ልቀቁና ውጡ›› የሚላቸው ግለሰብ ወይም ማን እንደጻፈው በማይታወቅ ደብዳቤ ሳይሆን ቅዱስ ሲኖዶስ በመሆኑ፣ በረሃብ ሕይወታቸው ቢያልፍም ሲኖዶሱ ‹‹ልቀቁ›› እስከሚላቸው እንደሚቆዩ አስታውቀዋል፡፡

ከማታና ከማስተርስ ተማሪዎች በስተቀር ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ዓመት ያሉ ተማሪዎች እንዲወጡ መታዘዛቸውን የገለጹት ተማሪዎቹ፣ መምህራንም እነሱን እንዳያስተምሩ መታዘዛቸውን ጠቁመዋል፡፡

ሚያዝያ 7 ቀን 2005 ዓ.ም. ተማሪዎቹ በቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ደጃፍ በመገኘት ልብሳቸውን አንጥፈው ሲለምኑ፣ በፖሊስና ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ድብደባና እንግልት እንደተፈጸመባቸውም ተናግረዋል፡፡ ተማሪዎቹ ሲለምኑ ያስተዋሉ ምዕመናን ፓትርያርኩ ወደሚያስቀድሱበት መንበረ ፓትርያርክ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው፣ ፓትርያርኩ ሊያስቀድሱ ሲመጡ እግራቸው ሥር ወድቀው ቢለምኗቸውም፣ ምንም ምላሽ ሳይሰጧቸው ማለፋቸውን ተማሪዎቹ ገልጸዋል፡፡

በመቀሌ የሚገኘው የከሳቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች፣ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጣቸው ለፓትርያርኩ ደብዳቤ መጻፋቸውን፣ የቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች ደግሞ ለምግብና ለተለያዩ ወጪዎች ዕርዳታ እያደረጉላቸው መሆኑንና ምዕመናኑም እየረዱዋቸው እንደሆነ ተማሪዎቹ ተናግረዋል፡፡

የቅድስት ሥላሴ ኮሌጅ ኃላፊ ብፁዕ አቡነ ጢሞቲዎስን፣ በተማሪዎቹ ላይ እየተወሰደ ስለሚገኘው ዕርምጃ ማብራሪያ እንዲሰጡን በሥፍራው ተገኝተን ብንጠይቅም፣ ‹‹የሉም፤ ፀሎት ላይ ናቸው፤›› በሚል ምላሽ ማግኘት አልቻልንም፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ በሚገኙበት መንበረ ፓትርያርክ ቤተ ክህነት ቅጥር ግቢ ተገኝተን ለማነጋገር ያደረግነውን ሙከራ፣ ‹‹ሰሞኑን ስብሰባ ላይ ስለሆኑ ማንም መግባት አይችልም፤›› በማለት በጥበቃ ሠራተኞች ልንመለስ ችለናል፡፡

No comments:

Post a Comment