ቁጥር አንድነት/645/2ዐዐ5
ቀን 29/05/2ዐዐ5 ዓም
ቀን 29/05/2ዐዐ5 ዓም
በ‹‹ጀሃዳዊ ሃረካት›› ትረካ የሙስሊሙን ማህበረሰብ ጥያቄ ማዳፈን አይቻልም!
ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) የተሰጠ መግለጫ
ይሄንን መግለጫ ስናወጣ ሀገራዊ ራዕይ እንዳለው ፓርቲ በገዥው ፓርቲ እያፈርንና እያዘንን ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ ዜጎች በማንኛውም መንገድ የሚያነሱትን ጥያቄ በግልጽና በውይይት መፍታት ያለመፈለጉ ግልጽ ሀገራዊ አደጋ እየሆነ መምጣቱን እያየን ነው፡፡
በኢትዮጵያ ሕዝብ ግብር የሚተዳደረው ነገር ግን የገዥው ፓርቲ መሳሪያ በመሆን የሕዝብ ጥያቄዎችን ለማፈን ተባባሪ መሳሪያ በመሆን እያለገለ ያለው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ‹‹ጀሃዳዊ ሃረካት›› በሚል የተሰናዳና እንደተለመደው የሙስሊሙን ህዝብ ጥያቄን ለማዳፈን የተዘጋጀ አይነት ትረካ (ዶክመንተሪ) ሲያቀርብ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ ከዚህ በፊትም ከፍርድ ቤት ፍርድ በፊት ፍርድ የሚሰጡ ‹‹አኬልዳማ››ን የመሳሰሉ ዶክመንተሪዎች በማቅረብ የተጠርጣሪዎችን ሰብዓዊ ክብር በሚጥስ ሁኔታና ከህግ በላይ በሆነ አካሄድ እየወነጀሉ አቅርበዋል፡፡ ዶክመንተሪዎች የሚሰጣቸው ርዕስ ግዝፈትና የአጽመ ታሪካቸው ትረካ ልልነት ከተራ ድራማም ያነሰ ነው፡፡ ስለዚህ ነው ኢትዮጵያን የምታክል ትልቅ ሀገር እያስተዳደረ ባለ መንግሥት አዝነናል የምንለው፡፡
በ28/05/05 ምሽት ላይ ‹‹ጀሃዳዊ ሃረካት›› በሚል የቀረበው ትረካም የቀረበበት አብይ ምክንያት፡-
1. የሙስሊሙን አንድ ዓመት የዘለቀ ግልፅ ጥያቄ ፊት ለፊት ተወያይቶ በመመለስ ፋንታ በእጅ አዙር ለማድበስበስ የተሰራ መሆኑ፤
2. በዜጎች ላይ የስነ-ልቡና ጫና በመፍጠር በፍርሓት ውስጥ አድርጎ ለመግዛት በማለም እና
3. መንግሥት በኃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አልገባም ቢልም እጁን አስረዝሞ በኃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ በመግባት የሚያደርገውን የአድራጊ ፈጣሪነት ስራ ‹‹ሕግ የማስከበር›› የሚል ሽፋን በመስጠትና ትንሹን ጉዳይ በማግዘፍ የማደናገር ስራ ለመስራት ያለመ ነው፡፡ እንደ ፓርቲም ይህንን መቃወም ብቻ ሳይሆን ኃላፊነት የጎደለውና፣ አርቆ አስተዋይነት ያጣ ተግባር ስለሆነ በአስቸአኩዋይ እንዲገታ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
ሌላው አሳፋሪ ጉዳይም እንደተለመደው የፍርድ ቤቶች ገለልተኛ ውሳኔ ‹‹ማን አለብኝ›› በሚሉ አምባገነን ግለሰቦች እየተጣሰ እንደሆነ ‹‹ጀሃዳዊ ሃረካት›› አሳይቶናል፡፡ የደረሰን መረጃ እንደሚያመለክተው ይህ ዶክመንተሪ በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት አራተኛ ወንጀል ችሎት የዕግድ ትእዛዝ ቢተላለፍበትም በማናለብኝነትና ሥልጣንን ካለአግባብ በመጠቀም ያለምንም ይግባኝ በከፍተኛው ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት ተሽሮ ለኢትዮጵያ ህዝብ እንዲተላለፍ ተደርጓል፡፡ የመንግሥትን ህግ ጣሽነት በግልጽ ያሳያል፡፡ ራሱ ህግ የሚጥስ ገዢ ፓርቲስ እንዴት የሌሎችን ህግ ሊያስከብር ይችላል?
ፓርቲያችን አሁንም ስጋት አለው፤ አሁንም የገዥውን ፓርቲ አፋኝ አካሄድን እንቃወማለን፣ አሁንም የመንግሥትን በኃይማኖት ጣልቃ ገብነት እናወግዛለን፣ ጥሪያችንም የዜጎች ጥያቄ በግልጽና በአደባባይ ይመለስ የሚል ነው፡፡ የህዝብ ጥያቄ ይከበር ነው፡፡ ስለዚህ ‹‹ጀሃዳዊ ሃረካት›› የሚል ትረካ በማቅረብ የሙስሊሙን ጥያቄ ማዳፈን አይቻልም፡፡ ዶክመንተሪው የሙስሊሙ ማህበረሰብ ጥያቄ መልስ ሊሆንም አይችልም፡፡
ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) የተሰጠ መግለጫ
ጥር 29 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም
አዲስ አበባ
No comments:
Post a Comment