አይን ያለው ይመልከት ፤ ጀሮ ያለው ይስማ ፤ እዝነ-ልቦና ያለው ራሱን ይጠይቅ !
ከስራ የሚፈናቀሉት የኮንትራት ሰራተኞች ቁጥር ከቀን
ወደ ቀን እየጨምረ መጥቷል፡፡ በሚደርስባቸው የስራ ጫና ፤ በስራ ሰአት ብዛት ፤ የጤና መታዎክን ተከትሎ ህክምና ስለማያገኙ፤ ለሃገሩ
ባዳ በመሆንና ከአካባቢውና ከስራው ጋር ራሳቸውን ባለማዋሃድ የሚያብዱ ፤ በአስገድዶ መድፈር ጉዳት የደረሰባቸውና ያረገዙ ጭምር
በሪያድ ኢንባሲ የኮሚኒቲ መጠለያና በጅዳ ቆንስል ግቢ ያለ በቂ መጠለያ ሲንገላቱ ተመልክተናል ፤ እየተመለከትንም ነው ! የሪያድ
ተጠላዮች ያበዱትን ከአራት በላይ እህቶች ጨምሮ ከ30 በላይ እህቶች ያሉበት ሁኔታ ከጅዳው የከፋና ብዙ አነጋጋሪ እየሆነ መምጣቱን
በተደጋጋሞ በቦታው ተገኝቸ ተመልክቻለሁ ፡፡ የግፉአን እህቶችን ችግር ከጓሯቸው ሄደው በመመልከት መፍትሄ በማፈላለግ እንደመፍታት
የተያዘው ምርመራ ደስ አያሰኝም፡፡ ምርመራው እህቶች የፍጥኝ ታስረው ሲጮሁ የሚያሳየውን ይህ አሳዛኝ ተንቀሳቃሽ ምስል (ቪዲዮ)
ያነሱት እነማን ናቸው ? ከሚል ጥያቄ ተጀምሮ ጥያቄና መልሱ እስከ ማስፈራራት የዘለቀ እንደሆነ ተረድቻለሁ፡፡ ቪዲዮ አነሱ የተባሉት
ሁለት ወጣቶች ሪያድ በሚገኘው ኢንባሲ ቀርበው ተንቀሳቃሽ ካሜራቸውን መቀማታቸን ሰምቻለሁ፡፡ ይገርማል ! የመንግስት ሃላፊዎቻችን
መብቱን ሳያስከብሩለትና ሳይጠብቁት ቀርቶ በወገን ላይ የሚደርሰውን ግፍ ሰሚ ይገኝ እንደሁ ያነሱት ወንድሞች ለማለት እንደተፈለገው "የሃገርን ገጽታ ለማበላሸት" የሚንቀሳቀሱ
አይመስሉኝም፡፡ ይልቁንም ለተቸገሩት ውሃና ምግብ ያቀብሉ እንደነበር በቦታው ያገኘኋቸው ገልጸውልኛል፡፡ ያም ሆኖ መብታቸውን ማስከበር
ቀርቶ ውሃ ያላቀበሉት ያልሆነ ስም እየለጠፉ ቅን አሳቢዎችን እስከማወገዝ የተንደረደሩበት እርምጃ ይስተዋላል ፡፡ ይህም ደስ አይልም
! እርምጃው " ሌባን ያዙ !" ያለን ጠቋሚ እያሳደዱ ሌባውን ከመልቀቅ ያልተናነሰ ነው ቢባል ማጋነን ይሆን ?
በጅዳ ቆንስልም እስከ ትናንትናው እለት ስድስት አዕምሯቸውን የሳቱ (ያበዱ) እህቶችን ጨምሮ ከላይ በጠቀስኳቸው በተለያዩ ችግሩች የተዳረጉ ከ38 በላይ የኮንትራት ሰራተኞች በቆንስሉ ግቢ ታዛና በጠባቧ መጠለያ ተጠልለው ሰንብተዋል፡፡ "ቆንስል መስሪያ ቤቱና ኮሚኒቲው በጥምረት በመስራት ለዘላቂው ችግር መፍትሄ ማፈላለግ ቢሳናቸውም እንዴት መጠለያ እንኳ በአግባቡ አያዘጋጁም ? " በሚል የሰላ ሂስ በነዋሪው እየተሰነዘረ ይገኛል ፡፡ በአንጻሩ ኮሚኒቲና ቆንስል መስሪያ ቤቱ ችግሩን ለመቅረፍ አማራጭ ፕሮጀክቶችን መንደፋቸውን በጓዳ በር በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች በጓዳ በር ይፋ እየሆነ መስማታችን አልቀረም፡፡ ትናንት ምሽት ደግሞ በቆንስል መስሪያ ቤቱ ተጠልለው የነበሩት የኮንትራት ሰራተኞች ወደ ሌላ መጠለያ መላካቸው አነጋጋሪ እርምጃ ሆኗል፡፡ ቆንስሉ ወደ አዘጋጀው አዲሱ መጠለያ ሂዱ ሲባሉ "አሻፈረኝ" ያሉት ግፉአን እህቶች የእንቢታቸውን ምንክያት ሲያስረዱ "ለወራት ከቆስንሉ ግቢ ውስጥ ሆነን ጉዳያችን ያልተፈጸመልን ከአይናቸው ርቀን እንረሳለን ! " የሚል ስጋት እንዳላቸው ገልጸውልኛል፡፡ ያም ሆኖ ከቀናት ውዝግብ በኋላ ትናንት ከምሽቱ ሶስት ሰአት ገደማ አምባሳደር መርዋን በድሪ በቆንስሉ ግቢ በመገኘት ጉዳያቸውን እንደሚከታተሉላቸው ቃል ተገብቶችላቸው ሳይዎዱ በግድ "መዲናተል ሃጃጂ !" ወደ ተባለው የሳውዲ መንግስት ለሃጅ ጸሎተኞች ወዳሰራው መጠለያ ተግዘዋል፡፡ ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ወገኖች ተፈናቃይ የኮንትራት ሰራተኞች ወደ ሌላ መጠለያ መሸጋገራቸው ምክንያት " እርምጃው ችግረኞችን ለመርዳት ሳይሆን ከባልስልጣናትና ለቪዛና ለተለያዩ ጉዳዮች የሚጎርፈው ሰው እንዳያያቸው ለመድረግ ነው ! " ሲጠቁሙ " ከቆንስል መስሪያ ቤቱ መራቃቸው ድሮም ትኩረት ያልሰጡት ሃላፊዎች ጉዳዩ እንዲዘነጋ ያደርገዋል ፡፡ ትኩረት በመስጠት እንዳይከታተሉት ያደርጋል !" በማለት ስጋታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡ የኮሚኒቲው ሃላፊዎችና አንዳንድ ወገኖች በበኩላቸው የቆንስል ሃላፊዎች ለወሰዱት እርምጃ ድጋፋቸውን ከመስጠት አልፈው እህቶች የቆንስል መስሪያ ቤቱን እርምጃ በአዎንታ እንዲቀበሉት ያግባቡት ፍሬ አግኝቶላቸዋል፡፡ በማህበረሰቡ ስም የተሰየመው የጅዳ ኮሚኒቲ ዛሬ እየሰራው ያለው ስራ በቅንነት ከሆነ ምስጋና የሚቸረው ቢሆንም ኮሚኒቲው አቅም እያጠረው እያደር መዝቀጡ ትናንትም ሆነ ዛሬ መነጋገሪያ ከመሆን አላለፈም፡፡ ከድክመቱ መነሻና መድረሻው ብዙ ቢሆንም ትምህርት ቤቱና ካፍቴሪያውን ማስተዳደር ተስኖት የሚንከላወሰው የጅዳ ኮሚኒቲ በዜጎች ላይ የሚደርሰው አደጋ እየከፋ ሲሄድ ለችግሩ መፍትሄ ለማፈላለግ ህዝባዊ ስብሰባ ጠርቶ ህዝቡን አለማዎያየቱ ማናችንንም ግራ እንዳጋባ ቀጥሏል፡፡ ይህው ኮሚኒዪ በያዝነው ሳምንት "የኮሚኒቲው የጡት አባት!" በአሽሟጣጮች የሚሸነቆጠውን የቀድሞውን የኮሚኒቲ ስራ አስፈጻሚ አባላት ጠርቶ ባደረገው ውይይትም ከመንግስት ጋር በመሆን ወደ መጠለያ የሚመጡትን እህቶች ለመርዳትና ለኮሚኒቲው ደጎስ ያለ ጥቅም የሚያስገኝ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን መቅረጹን ይፋ ሲያደርግ በ"ኮሚኒቲው የጡት አባት!" የሰላ ሂስ ቀርቦበታል ሲሊ ምንጮቸ ገልጸውልኛል፡፡ በማህበረሰቡ ስም የተደራጀው ኮሚኒቲ በተዘበራረቀ መንገድ እንዲህ ይጓዛል . . . ነዋሪው የሚይዝ የሚጨብጠው አጥቷል፤ የክንትራት ቪዛው ያላሰቡለትን ወረት ያዝገኘላቸው ወገኖች ከበር የሚሰራው ሁሉ ትክክል ነው ሲሉ ይሞግታሉ፤ የመንግስት ሃላፊዎች በሚጸድቀው ቪዛ ልክ ለአባይ ገቢ ማሰባሰቡ ተሳክቶላቸዋል፤ በኮንትራት ስራ የሚመጡት ዜጎች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እያደገ መጥቷል ! የሚገፉ የሚበደሉት ወገኖችም ሮሮ ከቀን ወደ ቀን እያየለ መጥቷል ! ግመሏ ትጓዛለች ፤ ውሾቹም ይጮሃሉ . . . አይን ያለው ይመልከት ፤ ጀሮ ያለው ይስማ ፤ እዝነ-ልቦና ያለው ራሱን ይጠይቅ !
No comments:
Post a Comment