Tuesday, January 21, 2014

የደህንነት ሰራተኞች ሃላፊነታችን ለአገር ወይስ ለፖለቲካ ስርአቱ ነው የሚል ጥያቄ አነሱ


ጥር ፱ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-መንግስት በመረጃዎች አያያዝ ዝርክርክነት ፣ በሳይበር በሚደረጉ ስለላዎች እና ከውስጥ ባሉ የመንግስት አካላት እየሾለኩ በሚወጡ መረጃዎች ህልውናየ አደጋ ላይ ወድቋል በማለት ግመገማ ማድረጉን ተከትሎ ”የደህንነት ሰራተኞች ሃላፊነታችን ለማን ነው?” የሚል ጥያቄ ማንሳታቸውን ከደህንነት መስሪያ ቤት ለኢሳት የደረሰው በድምጽ የተደገፈ መረጃ አመለከተ። በስብሰባው ላይ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እና የመንግስት ሹሞችም ተገኝተው ነበር።

ጥያቄውን ያነሱት በፌደራል ስር የሚገኙ የደህንነት ስራተኞች እና ቀደም ብሎ በአቶ መለስ ዜናዊ ዘመን በትግራይ ውስጥ በመቀሌ ዩኒቨርስቲ ሽፋን የተቋቋመው ኤም አይ ቲ እየተባለ በሚጠራው ከመቀሌ ከተማ 9 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በተገነባው ተቋም ውስጥ ተመርቀው የወጡት የደህንነት ሰራተኞች ናቸው።

የደህንነት ሰራተኞቹ “የእኛ ሃለፊነት የአገር ደህንነትን ማስጠበቅ ነው የፖለቲካ ስርአቱን ?” በሚል ጥያቄ ያነሱ ሲሆን፣ አንድ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣን ” የፖለቲካ ስራ የማይሰራ ደህንነት የለም፣ የደህንነት ስራ ሲጀመር ስርአት የማቆየት ስራ ነው፤ ስርአቱን የምናቆይበት ደግሞ ፕሮፌሽናል ነው፣ በስርአቱ ላይ እምነት ማሳደር የሚጠይቅ ተግባር ነው፣ የግንቦት7ትን አስተሳሰብ የሚያቀነቅንና ስርአቱ በጉልበት መፍረስ አለበት ብሎ የሚያስብ ሰው፣ የተስፋየ ወልደ ስላሴ አይነት የደህንነት ብቃት አለው ቢባል፣ ሞሳድ 20 አመታት አሰልጥኖታል ቢባል ስርአቱን ከማፍረስ ውጭ ደህንነቱን ሊያስጠብቅ አይችልም” ፣ ስለዚህ የደህንነት ስራ ለሚሰሩ ወገኖች የፖለቲካ ወገንተኝነታቸው ወሳኝ ነው የሚል መልስ ሰጥተዋል ።

“የደህንነት ተቋሙ ፣ ሰራዊቱና ሚዲያው በተቃዋሚዎች ዘንድ መቼውንም ቢሆን ገለልተኛ ተደርጎ አይቆጠርም” ያሉት እኝህ ከፍተኛ ባለስልጣን ፣ ገለልተኛ ማድረግ የሚባል አስተሳሰብ ያለው ካለ እንደዛ ሊሆን አይችልም፣ ሊሆን የሚችለው የተቃዋሚዎችን ሰዎች ደህንነት ውስጥ ማስገባት ነው ብለዋል። ” በተለይም በተቋም ደረጃ ፤በምህጻረ ቃል ኢንሳ እየተባለ የሚጠራው የመረጃ ደህንነት መስሪያ ቤት፤ የዜግነት እና ኤምግሬሺን ፤የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤በጀኔራል ሳሞራ የኑስ የሚመራው የመከላከያ ደህንነት ፤የአስተዳደር እና ፀጥታ ፤ የፌደራል ፖሊስ ፤ የፀረ ሽብር ግብረ ሃይል በእዝ ሰንሰለት በሚፈጠር ልዩነት እርስ በርስ እየተወዛገቡ ሲሆን፣ ተቋሞቹን በትክክል የሚመሩትን አካላት ለመለየት አስቸጋሪ ሆኖ መገኘቱና እርስ በርስ በሚፈጥሩት እሰጥ አገባ አንዱ አንዱ የሚሰራውን የማጠፋፋት እርምጃ እየወሰዱ መሆኑ በግምገማው ላይ ተነስቷል፡፡

የመንግስት ሚስጥሮች ለሶስተኛ ወገኖች ተላልፈው እየተሰጡ በመሆኑ ሚስጢሮችን መደበቅ የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል ሲሉ አንዳንድ ባለስልጣኖች አስተያየቶችን ሰጥተዋል።

ለተነሱት አስተያየቶች መልስ የሰጡት ባለስልጣኑ፣ ኢንሳ የተቋቋመውም ይህን ለመስራት መሆኑን ገልጸው፣ “አገሮች ሙሉ በሙሉ ከሳይበር ስለላ ነጻ ባለመሆናቸው አቶ ሃይለማርያምም ነጻ ናቸው ብየ አላስብም” ብለዋል። “አሜሪካኖች የምንናገረውን ሁሉ ከፈለጉ ይሰሙታል” የሚሉት እኝሁ ባለስልጣን፣ “እኛም የአቅማችንን ያክል አሜሪካኖች የሚናገሩትን ለማዳመጥ እንሞክራለን” ብለዋል። የሳይበር ስለላ ለማካሄድ ጥሩ ጅምሮች ቢኖሩም፣ ያን ያክል የምንኩራራበት ግን አይደለም በማለት ኢነሳ ያለበትን ደረጃ አመላክተዋል ከኦሮሚያና ከደቡብ የመጡ የደህንነት ሹሞች ደግሞ “በመከላከያ የደህንነት ተቋሞች ውስጥ የአንድ ብሄር የበላይነት ጎልቶ ይታያል” በሚል ቅሬታ ያነሱ ሲሆን ፣ ባለስልጣኑም “የሰራዊት ማመጣጠን ስራ በረጅም ጊዜ የሚሰራ ስራ ነው ” በማለት ለመመለስ ሞክረዋል።

” ትግሉን መርተው እዚህ ድረስ የመጡ ሰዎችና በመከላከያ ውስጥ ያለውን የመኮንኖች ቦታ የያዙት ከአንድ አካባቢ የመጡ መሆናቸው ግልጽ ነው የሚሉት ባለስልጣኑ፣ ያም ሆኖ ከትግራይ የመጡ በርካታ ጄኔራሎች ጡረታ እንዲወጡ ቢደረግም ሂደቱ ግን ረጅም ጊዜ የሚወሰድ ነው ሲሉ አክለዋል።

“የብሄር ተዋጽኦ ብቻ የአንድን ሰራዊት ጠንካራና ደካማ ጎን መገለጫ ተደርጎ መወሰድ ካለበት አደጋ አለው ” ያሉት ባለስልጣኑ፣ የአንድ ብሄር የበላይነት አለ ተብሎ በአጭር ጊዜ ለማመጣጠን ብቻ በአንድ አዳር ሁሉንም ነገር መቀየር እንደማይቻል መንግስት ያምናል ሲሉ ተናግረዋል አቶ መለስ ዜናዊ በውጭ ሃይሎች ተገድለዋል ይባላልና በምን እንደሞቱ በትክክል ይነገረን በሚል ባለስልጣናት ላነሱት ጥያቄም የደህንነት ባለስልጣኑ፣ “አቶ መለስ በውጭ ሃይሎች ተገድለዋል የሚል ትክክለኛ ማስረጃ የለም በማለት መመለስ የጀመሩት ባለስልጣኑ፣ እርሳቸው የሞቱት በስራ ብዛት ተዳክመው እና ህክምናውን መቋቋም ባለመቻላቸው ነው ሲሉ ደምድመዋል።

በተያያዘ ዜናም የሃገሪቱን ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል ከኢሳት ጋር በመሆን እየሰራችሁ ነው፣ ለኢሳትም መረጃ ታቀብላላችሁ ተብለው የተጠረጠሩ 5 የደህንነት አባላት በቁጥጥር ስር ውለዋል። ወጣት መብራቴ ታምራት ፤ወጣት ጀማል አወል ፤ወጣት ደጀኔ አድማስ ፤ ወጣት ሃይሉ ጨርቆስ ፤መቶ አለቃ አሰፋ አብርሃ ሰሞኑን በደህንነቶች ቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኢሳት የደህንነት ምንጮች ገልጸዋል።

በተመሳሳይ ዜናም በሃገሪቱ በ28ቱ ዩኒቨርስቲዎች የሚገኙ የህወሃት አባላት ተማሪዎች እና የደህንነቶች ሃለፊዎች ግምገማ መጀመራቸውን ለማወቅ ተችሎአል።

በግምገማው ወቅት የኦህዴድ እና የብአዴን መሪዎች የተማሪዎችን እንቅስቃሴ በመከታተል ባሰዩት ውጤት የተገመገሙ ሲሆን፣ ባለፉት ስድስት ወራት የአክሱም ፤ ደብረ ታቦር እና ደብረ ብርሃን የኒቨርስቲዎች ከፍተኛ የአመጽ እንቅስቃሴ የታየባቸው በመሆኑ ልዩ የደህንነት ክትትል እንደሚያስፈልጋቸው ተወስቷል።

Monday, December 30, 2013

በጀግኖች አባቶቻችን ደም የተቦካው ሉአላዊ ግዛታችን ላይ የሚደረገውን ስውር ሴራ ያለማወላወል በፅናት እንታገለዋለን፡፡ ከሰማያዊ ፓርቲ (ሰማያዊ) የተሰጠ መግለጫ

 
ታኅሣሥ 20 ቀን 2006 ዓ.ም. (December 30, 2013) 
የኢትዮጵያንና የሱዳንን ድንበር የማካለሉ ሥራ ከመስከረም 29 ቀን 2002 ዓ.ም. (October 9, 2009) ጀምሮ እየተከናወነ እንደሆነ፣ በእንግሊዘኛ ቋንቋ የሚታተመው ዕለታዊ የሱዳን ጋዜጣ ሱዳን ትሪቢውን (Sudan Tribune) በመስከረም 8 ቀን 2002 ዓ.ም. (September 18, 2009) መዘገቡ ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያና የሱዳን የድንበር ጉዳይ ያንገበገባቸው ኢትዮጵያውያን በሀገር ውስጥና በውጪ የሚኖሩት ዜጎቻችንም ራሳቸውን በተለያዩ “ኮሚቴዎች” እና “ግብረ ሃይሎች” በማደራጀት ለጉዳዩ ክፈተኛ ትኩረት እንዲሰጠው ሲጥሩ ቆይተዋል፡፡ ፓርቲያችን (ሰማያዊ)፣ ለነዚህ ሀገር ወዳድ ዜጎች ያለውን ከፍተኛ አክብሮት ለመግለጽ ይወዳል፡፡ 

ሆኖም፣ የነዚህን ሀገር ወዳድ ዜጎችና አፍቃሪ-ኢትዮጵያውያን ጥሪና መግለጫዎች ከቁብም ካለመቁጠር፣ በሥልጣን ላይ ያለው የወያኔ-ኢህአዲግ መንግሥት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጀርባ ሥውር የሥልጣን ማራዘሚያ ደባዎችን እየሸረበ እንደሚገኝ አጋልጠዋል። ወያኔ ራሱ ያቋቋመው “የኢትዮጵያና የሱዳን ድንበር ኮሚቴ” አባላት ራሳቸው በተለያዩ ቃለ-ምልልሶች እንዳጋለጡት፣ ወያኔ በአባቶቻችን ደም ተላቁጦ ለተቦካውና የበርካታ ሰማዕታትን ህይወት ላስከፈለው የኢትዮጵያ ድንበርና የግዛት ሉዓላዊነት ግዴለሽነቱን በተግባር አሳይቷል፡፡ የኢትዮጵያንም ሉዓላዊ ግዛትና ድንበር “በጫካ ውሎችና ስምምነቶች” እያመካኘ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ታሪካዊ ጠላቶች አሳልፎ መስጠቱን አጠናክሮ ቀጥሎበታል፡፡ 

ይህንንም ከፍተኛ የሆነ የሃገር ክህደትና ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ለማስተባበል በመገንዘብ፣ የወያኔ-ኢህአዲግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በድረ-ገጹ ላይ በመስከረም 2002 ዓ.ም መጨረሻ ላይ አንድ የማደናገሪያ መግለጫ አውጥቶ ነበር። ከዚህም የማደናገሪያ መግለጫ ውስጥ የሚከተሉትን ሦስት(3) አበይት ጉዳዮች መገንዘብ ይቻላል። እነርሱም፦ 

1ኛ. የኢትዮጵያና ሱዳን የፖለቲካ ኮሚቴ (Ethio-Sudan Political Committee) ተብሎ የሚጠራ ከፍተኛ አካል መኖሩንና የኢትዮጵያና የሱዳን የጋራ ድንበር ኮሚቴም (Ethio-Sudan Joint Boundary Committee) በፖለቲካው ኮሚቴ ሥር እንደሚሠራ አረጋግጧል፤ የዚህ የኮሚቴ መዋቀርና የአሰራር ሂደቱም ለረጅም ዓመታት ከኢትዮጵያ ሕዝብ አይንና ተደብቆ የቆየ እንደሆነና፣ ወያኔ-ኢህአዲግም በሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ክትትል መጋለጡን ሲያውቅ ተጨንቆ ያወጣው ምስጢር ነበር። 

2ኛ. የኢትዮጵያና የሱዳን የጋራ የድንበር ኮሚቴም (Ethio-Sudan Joint Boundary Committee) ከጥቅምት 5 ቀን 2002 ዓ.ም. (October 15, 2009) እስከ ግንቦት 2002 ዓ.ም.(May 2010) ድረስ የኢትዮጵያና ሱዳን ድንበርንና አካባቢውን ሙሉ በሙሉ እንደሚቀይስና ቅኝት እንደሚያደርግም ገልጾ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ወያኔ ሲጋለጥ ያወጣው ሌላው ምስጢር ሲሆን፣ (ሱዳን ትሪቢውን ያወጣውን ዜና የሚያጎለምስ) እና የሱዳን ሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ድንበሩን ለማካለል የሚያደርገውን ዝግጅት የሚያስተጋባ ነው። 

3ኛ. የድንበር ክለላው ከግንቦት 2002 ዓ.ም. ( May 2010) በኋላ እንደሚደረግና ከዚህም ጋር አያይዞ ወያኔ-ኢህአዲግ ያለፉት የኢትዮጵያ መንግሥታት አምነው የተቀበሉት የድንበር ክልል እንዳለ አስምስሎ ለማቅረብም ጥረት አድርጎ ነበር፡፡ በመሆኑም፣ ወያኔ-ኢህአዲግ አሁን የሚያካሂደው “የድንበር-ክለላ ሂደት” ዳግም ድንበርን የመከለል ተግባር ( re-demarcation ) እንደሆነ መግለጹ ለመግለጽ ሞክረዋል፡፡ ይህ ማደናገሪያና ተራ ልፈፋ፤ የኢትዮጵያን ህዝብ ለማወናበድና ግዛቱን በጫካ ውሎችና ስምምነቶች አማካይነት አሳልፎ ከመስጠት የዘለለ ኢምንት እውነታ የለውም፡፡ ይሄንን በተመለከተም ያጠኑት ሊቃውንትንና በግዛቱ ላይ የሚኖሩትን ዜጎች ምስክርነት ሊያገኝ አልቻለም፤ አይችልምም፡፡

የወያኔ-ኢህአዲግ መንግሥት “ያለፉት የኢትዮጵያ መንግሥታት የተቀበሉት የድንበር ክልል” የሚለው ሀተታ፤ ሜጀር (ሻለቃ) ጉዊን የተባለው የእንግሊዝ ጦር መኮንን በ1902 ዓ.ም. (እ.አ.አ.) “አስምሬአለሁ” የሚለውን የወሰን ክልል ነው። ይሁንና አንድ በእንግሊዝ የቅኝ-ገዥነት አባዜ የሰከረ ሻለቃ ያሰመረውን መስመር መሠረት አድርጎ ፀረ-ኢትዮጵያና ፀረ-ሉዓላዊነትን የወያኔ-ኢህአዲግ ገዢ ቡድን “ለሱዳን ይገባታል” ብሎ መሟገቱ የፖለቲካ ቅጥፈት እንጂ ታሪካዊ ማስረጃ የለውም፡፡ የሚከተሉትም ታሪካዊ ዳራዎች የወያኔን ሙግት ውድቅ ያደርጉታል፦

1ኛ.ሻለቃ ጉዊን መሬቱን አካልያለሁ ሲልና በወረቀት ሲያሰምር፤ በኢትዮጵያ በኩል አንድም ተወካይ ስለአልነበረ የጉዊን የድንበር ማካለል ተግባር ከቅኝ ገዢዎች ማንአለብኝነት ተለይቶ የማይታይና የውል አፈጻጸም ሥርዓት የማይከተል በመሆኑ የተነሳ ተቀባይነት የለውም፡፡

2ኛ. የ1896 ዓ.ም.(እ.አ.አ.) የአድዋ ጦርነት ድል በቅኝ ገዥዎች ላይ በፈጠረው ከፍተኛ መደናገጥ ምክንያት 1902 ዓ.ም. (እ.አ.አ.) አካባቢ እንግሊዝና ጣሊያን በጋራ በመመሳጠር የሰሜንና የምዕራብ ኢትዮጵያን ድንበር ለመግፋት የፈፀሙት ሴራ ስለሆነ፣ የሻለቃ ጉዊን ተልዕኮም ከዚያ ሴራ ተነጥሎ ሊታይ አይችልም፡፡ ስለሆነም ተቀባይነት የለውም፡፡

3ኛ. ከአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት በፊትም ይሁን ከዚያ በኋላ፣ ይህ ሻለቃ ጉዊን ከለለው የሚባለው መሬት ምን ጊዜም ቢሆን ከኢትዮጵያ ይዞታ ውጭ ሆኖ አያውቅም፡፡ ይባስ ብሎም፣ በአፄ ቴዎድሮስና በአፄ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት የኢትዮጵያ ግዛት አሁን ሱዳን ተብሎ ከሚጠራው ሃገር በጣም ወደ ውስጥ የገባ ነበር፡፡ ስለሆነም፣ የግዛት ጥያቄ ሲነሳ የይገባኛል ታሪካዊ መሠረት ያላት ኢትዮጵያ መሆኗን ለማስተባበል አዳጋች ነው፡፡ 

4.አሁን የወያኔ-ኢህአዲግ መንግሥት በመጋቢት 22/2006 ዓ.ም ገደማ March 30, 2014 ለሱዳን ለመስጠት ቅድመ-ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡ ለኢትዮጵያ ህዝብ ከፍተኛ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ምንም አይነት ግልጽነትና ተጠያቂነትን መርሆው ያላደረገው የወያኔ-ኢህአዲግ መንግሥት ግን አንዳችም መረጃ የኢትዮጵያ ህዝብ እንዳያገኝ የተለመደ አፈናውን ገፍቶበታል፡፡ በመሆኑም፣ በእልፍ-አዕላፍ ድንበር ጠባቂ ኢትዮጵያዊያን ደምና አጥንት ተጠብቆ የኖረውን ዳር ድንበር፣ ወያኔ በተለመደ “የደጃዝማቾች ፈረስ መጠጫና ጉግዝ መጫወቻ ነው” በሚል ንፍገት አሳልፎ ለሱዳን ሊሰጠው ተዘጋጅቷል፡፡ ይህ የምዕራብና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሰፊ ውሃ-ገብና ለም ሉዓላዊ መሬት፣ የታሪክ ማስረጃዎችንና የኢትዮጵያውያንን መስዋዕትነት በማናናቅ ለባዕዳን ሊሠጥ አይችልም፡፡ 

ስለዚህ ከላይ በተጠቀሱት ማስረጃዎችና በዓለም-አቀፍ የአሠራር ደንብ መሠረት፤ ወያኔ-ኢህአዲግ ከሱዳን ጋር የሚያደርገው የድንበር ክለላ ስምምነት ህገ-ወጥ ነው። ከዚህም ባሻገር፤ ከዋናው ባለጉዳይ የኢትዮጵያ ሕዝብ በስተጀርባ የሚደረግ ማንኛውም ዓይነት ስምምነት ይሁን የድንበር ክለላ ተግባር ምንም ዓይነት ተቀባይነት አይኖረውም። 

ከዚህም ሌላ፣ ወያኔ-ኢህአዲግ የተወሰኑ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ መሬት ቆርሶ በመስጠት ሥልጣኑን በጎረቤት አገር ሱዳን ለማስባረክ ብሎ የሚያደርገው ሽር-ጉድ በየትኛውም መስፈርት ተቀባይነት የለውም፡፡ ውጤቱም “ታግዬላቸዋለሁ የሚላቸውን ብሄሮችና ብሔረሰቦች” ከማዳከምና ብሎም ለማፈራረስ የተጠቀመበተ ዘዴ የቅኝ ገዢዎች ለራሳቸው ጥቅም ማስጠበቂያ ያሰመሩትን የድንበር መስመር በመቀበልና የቅኝ ገዢ ጠበብትን እንደ ምስክር በመጠቀም ነው። ይህም ተግባሩ፣ቀድሞውንም በቋፍ የነበረውን የወያኔ-ኢህአዲግን መንግሥት የፖለቲካ ቅቡልነት የሚያሳጣው መሆኑን ለማስታወስ እንፈልጋለን፡፡ አልፎ-ተርፎም በዚህ ተግባሩም ዛሬም የቅጥረኛ ሥራ እያከናወነ እንደሆነ ህዝቡ እንዲያውቀው እንፈልጋለን፡፡

ይህ የወያኔ-ኢህአዲግ ገዢ ቡድን ተግባር የሃገራችን ኢትዮጵያን ዓለም-አቀፍአዊ ክብር የሚጎዳ ስለሆነ ከተግባሩ እንዲታቀብ እናሳስባለን፡፡ በተጨማሪም፣ ለጉዳዩ ባለቤት ለሆነው ለኢትዮጵያ ህዝብ፣ ዝርዝር መረጃና ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ የማሳወቅ ግዴታ እንዳለበትም ልንገልጽ እንወዳለን፡፡ ይህን ሳያደርግ ቢቀር ግን፣ ፓርቲያችን የተጣለበትን የአባቶቻችንን ክብርና የሀገራችንን ሉዓላዊነት የማስጠበቅ ታሪካዊ ኃላፊነት መቼም ቢሆን ያለምንም ማወላወል የምንወጣ መሆናችንን ለጉዳዩ ባለቤት ለኢትዮጵያ ኅዝብ በድጋሚ እናረጋግጣለን፡፡

ሰላም፣ ተስፋ፣ ፍትህና እኩልነት በዲሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች በተከበሩባት ኢትዮጵያ ዕውን ይሆናል!!!

Saturday, December 28, 2013

ፍትህ የተጠማች ብላቴና



በአንድነት ጠቅላላ ጉባኤ ወቅት ታዳጊዋ ፍትህን ጠየቀች (ከፍኖተ ነጻነት የተወሰደ)

«ይህች ህጻን አማራም፣ኦሮሞም፣ጉራጌም፣ትግሬም ፣ሙስሊም፣ክርስቲያን ፣የኢህአዴግ ተቃዋሚ ወይም ደጋፊ ፣ሽፍታ አይደለችም፡፡ለሁሉም ያልደረሰች ህጻን ብቻ ናት፡፡ሁላችንንም የምትጠይቀን ፍትህ ብቻ ነው፡፡አባቷን ገድለው እጇን በጥይት ቆርጠዋል፡፡ምናልባት ሳድግ መምህር የመሆን ህልም አለኝ ብላኛለች፡፡ማን ነው ለዚህ ህልሟ የሚያደርሳት ?ወዳጄ ነገ ከነገ ወዲያ በአዲስ አበባ በአንድ ቦታ ሳንቲም ትሎት ወይም ትለን ይሆናል፡፡እውን ህመሟ ይሰማናል?ይሰማቸዋል?» ሲል ነበር የአንድነት ጥቅላላ ጉባኤ ተካፋይ አባቷን እንዲሁም እጆቿን ያጣችዉን ታዳጊ ወጣት ሲያስተዋወቅ የተነገሩት።

አባቷን በጥይት የተነጠቀችውና እጇን የተቆረጠችው ታዳጊ በጠቅላላ ጉባኤው በቀረበበችበት ወቅትም ፣ አባላቱ በእንባ ታጥበዋል፣ቁጭት ውስጣቸውን አንገብግቦት ‹‹ፍትህ፣ፍትህ፣ፍትህ» በማለት ጩኅታቸውን አሰምተዋል።

አባቷ ለበርካታ አመታት የኢሕአዴግ /ብሃዴን አባል የነበሩ፣ መዋጮ የሚያዋጡ ሰው ነበሩ።ሰባት ልጆች የነበሯቸው ሲሆን በዚህ ሁኔታ ሕይወታቸው ማለፉ የአገዛዙን ምንነት ብዉ አደርጎ ያጎላ ነዉ።

ቪዲዮዉን ይመልከቱና ይፍረዱ !





Esat special Public meeting in Bergen Norway part 1 and 2 Dec14 2013

በኖርዌ በርገን ከተማ በዲሞክራሲያዌ ለውጥ ድጋፍ ድርጅት በኖርዌ አዘጋጅነት  የተደረገ ህዝባዊ  ስብሰባ




Wednesday, December 18, 2013

የግንቦት7 ህዝባዊ ሀይል “መጪው አመት ህዝብን የመታደግ እርምጃ የሚወሰድበት አመት ይሆናል” አለ

 (ስምንት)ቀን ፳፻፮ /  ኢሳት ዜና :-ህዝባዊ ሀይሉ የተመሰረተበትን አንደኛ አመት በማስመልከት ባወጣው መግለጫ ” ያለፈው አንድ አመት የመሰባሰብ ድርጅት መሰረታዊ የሆኑ የፖለቲካና የወታደራዊ ስልጠና የተሰጠበት፣ የድርጅት ማጠናከሪያና የማጥራት ሂደት የተካሄደበት ” ነበር ብሎአል። መጪውን አመት የተለየ የሚያደርገው ህዝባዊ ሀይሉ በህዝብ ላይ በሚደርሰው ግፍና ውርደት ከሚሰማው ከፍተኛ ብስጭትና ቁጭት አልፎ ባለፈው አመት ሊደርስላቸው ያልቻለውን የአገራችንን ግፉአን ህዝቦች መታደግ የሚችልበትን እርምጃዎች መውሰድ የሚችልበት መሆኑ ነው” የሚለው ህዝባዊ ሀይሉ፣ በዚህ የህዝባዊ ሀይሉ የአንደኛ አመት ምስረታ ክብረ በአል ወቅት ለወገንም ለጠላትም በግልጽ እንዲያውቀው የምንፈልገው ይህን ሃቅ ነው ብሎአል።
ህዝባዊ ሀይሉ ” ለተራ የፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ስንል በቂ ዝግጅት ያልተደረገበት የሃገሪቱን ውድ ልጆች በከንቱ የሚማግድ ጀብደኛ እንቅስቃሴ  አናደርግም። በውሸት ተስፋ  ህዝብን አንመግብም።  አይናችንን ከዋናው የኢትዮጵያና  የህዝቧ  ጠላት ከሆነው ከወያኔ ላይ አንስተን በሌሎች  ወያኔን እቃወማለሁ በሚሉ ሃይሎች ላይ አንተክልም። ከወያኔ ሌላ ወደ ጎን የምንዋጋው፣ የምንጨቃጨው አታካራ የምንገጥመው ምንም ሃይል አይኖርም። ወያኔን ለመምታት ህዝባዊ ሃይሉ የጨበጠው  ቡጢ ወገኖቻችን በፍቅር ለመጨበጥ የሚዘረጉ ጣቶች  እንዳሉት በጸረ ወያኔ ዴሞክራሲያዊ ትግሉ  ከልባቸው ለመተባበር ለሚፈልጉ ሃይሎች ሁሉ ግልጽ እናደርጋለን።” ሲል አትቷል።
በግንቦት7 ህዝባዊ ሀይል አመራሮች ላይ መንግስት የመግደል ሙከራ ማድረጉና መክሸፉ ይታወሳል።  በቅርቡ ደግሞ ከአመራሩ ጋር ለመደራደር ጥያቄ ማቅረቡና ንቅናቄው ውድቅ ማድረጉ ይታወቃል።

Tuesday, December 17, 2013

የግንቦት 7 ህዝባዊ ሃይል የተመሰረተበትን አንደኛ አመት አስመልክቶ የተሰጠ ድርጅታዊ መግለጫ


ቀን ታህሳስ 7 2006
ታህሳስ 7 2006 ዓም የግንቦት 7 ህዝባዊ ሃይል ከተመሰረተ አንድ አመት ሞላው። አንድ አመት በጭንቅና በአሳር ለተያዘች የዛሬይቱ ኢትዮጵያና ህዝቧ እጅግ ረጅም ግዜ እንደሆነ ህዝባዊ ሃይሉ በሚገባ ይገነዘባል። ባላፈው አንድ አመት ውስጥ የኢትዮጵያን ህዝብ የመከራ፣ የአሳርና የውርደት ህይወት ይበልጥ እየሰፋ፣ የሚፈጸምበት ግፍ ይበልጥ እየገዘፈ መሄዱን አይተነዋል። በሃገርና በህዝብ ላይ እየወረደ ያለውን ወያኔ ወለድ የስቃይና የፍዳ ናዳ በቅጡ ላጤነው ሃገሪቱና ህዝቧ የአዳዲስ የስቆቃና የመከራ አይነቶች መፈተኛ ቤተ ሙከራዎች እየተደረጉ ለመሆኑ ጥርጥር አይኖረውም። ለሚራበው፣ ለሚረገጠው፣ በግፍ ለታጎረው፣ በኑሮ ውድነት ለሚጠበሰው፣ ለተሰደደው ለተፈናቀለው ኢትዮጵያዊ እንድ አመት በሲኦል የቀናትና የወራት መቁጠሪያ እንደሚለካ ዘመን እጅግ የረዘመ የስቃይ ግዜ ነው።
የዋልድባ መነኩሳት ገዳማችን አትድፈሩ አታፍረሱ በማለታቸው እየተገረፉ ለዘመናት ፈጣሪያቸውን ከሚማጸኑበት ለሃገርና ለህዝብ ምልጃ ከቆሙበት ገዳም በዘር መመዘኛ እየተለዩ እንደቆ ሻሻ ተጠርገው የተባረሩበት፣ እምነታችን አትንኩ ያሉ የእስልምና እምነት ተከታዮችና መሪዎቻቸው በሃሰት ክስ ተመስርቶባቸው ወህኒ መውረዳቸው አንሶ ወንድሞቻችን ይፈቱ በማለት ሰላማዊ ጥያቄ ያቀረቡ ወገኖቻቸን በወያኔ ነፍሰ ገዳዮች በአረመኔያዊ ጭካኔ የተጨፈጨፉት በዚሁ አመት ነው። ወያኔ በህዝብ መሃከል በዘራው የዘር መርዝ የተነሳ በሽዎች የሚቆጠሩ አማሮች ከጉራ ፈርዳና ከቤንሻንጉል፣ ኦሮሞዎች ለዘመናት ከኖሩበት ምስራቅ ሃረርጌ አካባቢ እንዲፈናቀሉና በገዛ ሃገራቸው መድረሻ ቢሶች እንዲሆኑ የተደረገው በዚህ አንድ አመት ውስጥ ነው። ጋምቤላዎች ሙርሲዎች አፋሮችና ሌሎችም ብሄረሰቦችና ማህበረሰቦች የተጨፈጨፉበት፣ በልማት ስም ለመጡ የውጭ ወራሪዎችና ወያኔ ለፈጠራቸው ቱጃሮች ቦታ እንዲለቁ ተደርጎ ቀደምቶቻቸው ለዘመናት ከኖሩባቸው ቀየዎች እንዲነቀሉ ተደርገው እንደ አልባሌ ነገር የትም እንዲበተኑ የማድረጉ ሂደት ከመቼውም በላይ ተጠናክሮ የቀጠለው በዚሁ አመት ነው። በዚሁ አንድ አመት በወያኔ የሃገሪቱ ገዥዎች በህዝብ ላይ የተፈጸመው ጭካኔና ወንጀል ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም።
ይህ ወያኔ ሰራሽ ሃገር በቀል የውርደትና የስቃይ ህይወት አልበቃ ብሎ ወያኔ ከሳውዲ የጨለማ ዘመን ገዥዎች ጋር በመተባበር ወንድሞቻችን በሳውዲ አውራ ጎዳናዎች ላይ እንዲታረዱ እህቶቻችን በቡድን በተደራጁ የሳውዲ ጎረምሳዎች እንዲደፈሩ ሁኔታዎችን አመቻችቶ ለኢትዮጵያውያን ያለውን እጅግ የከረረ ጥላቻ በአደባባይ ያሳየበት አመት ነው። እንዲህ አይነቱ የጅምላ ግፍና ውርደት ከመከሰቱ በፊት ህዝባዊ ሃይሉ በአረብ ሃገር በባርነትና በስደት የሚገኙ እህትቶቻችንን ወንድሞችችን ስቃይ ስቃዩ አድርጎ በመውሰድ “ላንቺ ነው” በሚለው ድርጅታዊ መዝሙሩ “በባለጌ አረቦች መዳፍ ውድ ክብራቸው ለጎደፈው እህቶቻችን፣ በአረቦች የባርነት ቀንበር ጀርባቸው ለጎበጠው ወገኖቻችን እንደርስላችኋለን፣ የተሰባሰብነው ደማችን የሚፈሰው የመከራ ቀናችሁን ለማሳጠር ነው” የሚል ቃል ኪዳኑ ሰጥቶ ነበር። የድርጅታችንን ምስረታ አንደኛ አመት ስናከብር ልባችንን ደስታ ሳይሆን ሃዘን እንዲሞላ የሚያደርገው ይህ ቃል ኪዳናችን ለማክበር የጀመርነው ጉዞ ከድርጅት ምስረታና ከድርጅታዊ ዝግጅት አልፎ በኢትዮጵያ ህዝብ ጥላቻና ንቀት የተነፋውን የወያኔን እብሪት በማስተንፈስ የወሰዳቸው ተጨባጭ የአለኝታነት እርምጃዎች ባለመኖራቸው ነው።
ምንም እንኳን ግንቦት7 ህዝባዊ ሃይል እራሱን እንደ ድርጅት አቁሞ ኢትዮጵያውያንን አሰባስቦ መራራው ትግል የሚጠይቀውን የፖለቲካ የወታደራዊ ስልጠናና ትጥቅ አስታጥቆ በወያኔ ላይ ለመዝመት የጀመረውን ጉዞ የሚያስቆመው ምድራዊ ሃይል እንደሌለ ብናውቅም የህዝብ ስቃይ ለግዜው መቀጠሉ የህባዊ ሃይሉን አባላት ማሰቃየቱ አልቀረም። በወያኔ ግፈኛ አገዛዝ የተንገፈገፈው ወገናችን ህዝባዊ ሃይሉ የወያኔን አገዛዝ እድሜ የሚያሳጥሩ ፈጣን እርምጃዎችን እንዲወስድ በከፍተኛ ጉጉት እየተጠባበቀ እንደሆነ እናውቃለን። ህዝባዊ ሃይሉን ለመቀላቀል በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ የሃገሪቱ ዜጎች በተጠንቀቅ እንደቆሙ እናውቃለን። እነዚህ ዜጎች ከሁሉም የእምነት የቋንቋ የጾታ የእድሜ የኑሮና የማህበረሰብ ስብጥር የሚያካተቱ እንደሆኑ እናውቃለን። በሃገሪቱ ታሪክ ተሰምቶና ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ የወታደር ልብሱን እየጣፈ እንዲለብስ፣ የወታደር ጫማውን መቀየሪያ አጥቶ ሸበጥ እንዲያደርግ የተገደደውን፣ የወያኔ ጀነራሎች በስልጣንና በዘረፋ ሲያብጡ በድህነት እንዲሟሽሽ የተፈረደበት የሃገሪቱ ሰራዊት በዘር በእምነት ሳይለያይ ከህዝባዊ ሃይሉ ጎን ለመቆም አሰፍስፎ የቆመ እንደሆነ እናውቃለን። ይህ ሃገራዊ እውነታ ለህዝብ የገባነውን ቃልኪዳን የለምንም ጥርጣሬ ማስከበር እንደምንችል በሙሉ ድፍረት እንድናውጅ የሚያስችለን ሃቅ ነው።
የወያኔ ጀንበር እየጠለቀች የኢትዮጵያ ህዝብ ጀንበር እየፈካች የመሄዱ ጉዳይ እንደማይታጠፈው የመንጋትና የመምሸት የተፈጥሮ ህግ ነቅነቅ የማይል እንደሆነ ግንቦት7 ጠንቅቆ ያውቃል። እውቀታችን ልዩ ጥበብ የሚጠይቅ ኣይደለም። ግፍ ፍትህን አሸንፎ፣ እውነት በሃሰት ተደፍቃ፣ ጥላቻ ፍቅርን፣ አድሎ እኩልነትን፣ ሃገራዊ ክህደት ሃገር መውደድን፣ ባንዳነት አርበኛናትን ለዘላላሙ ቀብረው የሄዱበት የሃገራችንና የሰው ልጆች ታሪክ የለምና የወያኔን አይቀሬ ሞት ለመተንበይ ልዩ ጥበብ አያሻንም። ይህን እኛ ብቻ ሳንሆን በዘረፋና በጥላቻ የደነዘዘ ህሊና ያዳበሩት የወያኔ ባለስልጣናትም ያውቁታል። ያለእኔ ጀግና የለም፣ ያለእኔ አልሞ ተኳሽ የለም በሚል እብሪት በመጻደቅ የሚታወቁት ወያኔዎች በመቶ ሽዎች በሚቆጠሩ ወታደሮች ተከበው፣ በታንክ በአይሮፕላን በሚሳይል ታጅበው ከሚኖሩበት ቤተመንግስትና ቪላዎች ውስጥ ብርክ እንዲይዛቸው ያደረገው ለመሆኑ፣ ሳር ቅጠሉ ግንቦት ሰባት እየመሰላቸው ሲበረግጉ እንደሚያመሹ፣ የግንቦት ሰባት አባላት እያሉ ከድርጅታችን ጋር አንዳችም ግንኙነት የሌላቸውን ዜጎች እያሰሩ ሲያሰቃዩ፣ ከምላሳቸው ላይ ግንቦት 7 የሚል ስም ተፈናጦባቸው እንደሚውሉ በራሳቸው ሚድያ ወያኔዎች ራሳቸው እያሳዩን እያስደመጡን ነው። ከዚህም አልፎ በዚህ አንድ አመት ውስጥ የህዝባዊ ሃይሉን መሪዎች በመግደል ድርጅቱን ለማኮላሸት ይቻላል በሚል ወያኔ የላካቸው ነፍሰ ገዳዮችና ድርጅቱን ከውስጥ ለመቦርቦር ያሰማራቸው ሰርጎገቦች ተራ በተራ ተልእኳቸው እየከሸፈ በህዝባዊ ሃይሉ እጅ እየወደቁ ወይም ተልእኳቸው እንደማይሳካ ሲረዱ እየፈረጠጡ ወደ ወያኔ ሲመለሱ አይተናል።
ያለፈው አንድ አመት ተመክሯችን ስለወያኔ ብቻ ሳይሆን ስለራሳችንም ጥንካሬና ድክመት ብዙ ነገሮች ያስተማረን ኣመት ነው። የቀደምቶቻችን የጀግንነት የአርበኛነት ቅርስ በመላ ህዋሳቸው የተሸከሙ ለኢትዮጵያ እና ለህዝቧ ሲሉ ደማቸው ለማፍሰስ ውድ ህይወታቸውን ለመሰዋት ወደኋላ የማይሉ ቆራጥ ብቻ ሳይሆኑ አርቀው የሚያዩ በርካታ ልጆች ሃጋሪቷ ያሏት መሆኑን ያረጋገጥንበት አመት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ድርጅታችን የኢትዮጵያን ህዝብ ብቸኛው የመንግስት ስልጣን ባላቤት የማድረጉን ታሪካዊ ራእዩን ለመሳካት የሚያደረገው ትግል ከወያኔ ጋር ብቻ ሳይሆን ከራሳችንም ጋር የሚደረግ እንደሆነ በሚገባ የተረዳነው በዚሁ የአንድ አመት የድርጅታችን እድሜ ነው። ከራሳችን ጋር የሚደረግ ትግል ወያኔ በማህበረሰባችን ውስጥ ከዘራቸውና የሃገሪቱን ዜጎች እንዲበክሉ ካደረጋቸው የዘረኛነት የአድሎ ከህዝብና ከሃገር ጥቅም በፊት የራስን ጥቅም ማስቀደም፣ የሱሰኛነትና የሙስናና ሌሎችም አደገኛ ባህሎች ጋር ነው።
ህዝባዊ ሃይሉ ደግሞ ደጋግሞ እንደገለጸው ትግላችን አንድ መንግስታዊ ስርአት ወድቆ ሌላው የመንግስት ስርአት በመጣ ቁጥር የህዝብ ተስፋ እየጨለመ “አዲስ ከመጣው ስርአት ያላፈው ያረጀ ስርአት በግፈኛነቱ በዘራፊነቱ ያነሰ ነበር” የሚል የግፈኛና የዘራፊ ስርአቶች ንጽጽር ላይ የቆመ አሳዛኝ የህዝብ ህይወት እንዲያበቃ ነው። ደርግን ያየ የአጼውን ስርአት እንከኖች ረስቶ ንጉሱ ይሻሉን ነበር ያለበት፣ ወያኔን ያየ የደርግን አስከፊ ዘመን ረስቶ መንጌ በስንት ጣሙ ያለበት አሳዛኝ ሁኔታ ከወያኔ መውደቅ በኋላ በሃገራችን እንዳይደገም ነው ትግላችን። የኢትዮጵያ ህዝብ የውድ ልጆቹን ህይወት ገብሮ ወያኔን በማስወገድ የሚያመጣው ስርአት ከወያኔ ብሶ ህዝብ ወያኔ ማረኝ የሚልበትን ቅስም ሰባሪና አዋራጅ የታሪክ ቅጥልጥሎሽ እንዳይቀጥል ማድረግ ህዝባዊ ሃይሉ የተመሰረተበት፣ አባላቱ መከራ ለመቀበልና መስዋእትነት ለመክፈል በረሃ የገቡበት ዋናውና ብቸናው ምክንያት ነው። ትግላችንን መራራ የሚያደርገው ከበሰበሰውና የአንድ ጀምበር የህዝብ ቁጣ ከታሪክ ቆሻሻ የመጠያ ስፍራ ከሚከምረው የወያኔ ስርአት ጋር ብቻ ሳይሆን በወያኔ ቦታ የሚተካውን ስርአት ከአድሎና ከዘረኛነት ከዘረፋና ሃገራዊ ክህደት የጸዳ፣ ዳግም ለኢትዮጵያውያን ውርደትና እንግልት ምክንያት እንዳይሆን ለማድረግ ከራሳችን ጋር ሳይቀር የማያቋርጥ ትግልን ማድረግ የግድ ስለሚል ነው። ህዝባዊ ሃይሉ የአመጽ ትግል የሚያደርግ፣ የመሳሪያው ብዛትና የሰራዊቱ ቁጥር እያደገ የሚሄድ ሃይል መሆኑን ስለምንረዳ ይህን ሃይል ገና ከጅምሩ ከብዙ እንከኖች እያጸዱ ማደራጀት ካልተቻለ በሃገርና በህዝብ ላይ የሚመጣውን አደጋ የህዝባዊ ሃይሉ አባላት ጠንቅቀው የተረዱት ሃቅ ነው። ይህ ግንዛቤ የሰራዊቱን አባላት በጥንቃቄ መመልመልን፣ ማሰልጠንንና መገንባትን የግድ የሚል ነው።
ይህ ከራሳችን ጋር የሚደረግ ትግል እጅግ መራራ ነው። ታሪካዊ ስህተቶችን ላለመድገም የሚደረግ ትግል ነው። ይህ ትግል የአካልና የመንፈስ ጽናትን፣ ሃቀኛነትን፣ ታማኝነትን፣ ጀግንነትን የሚጠይቅ ትግል ነው። የወያኔ ስርአት ከሃገር ግድያው በተጨማሪ ትውልድን ለመግደል ሆን ብሎ ያስፋፋቸው እኩይና ጎጂ ባህሎችና ልምዶች ምን ያህል ማህበረሰባችንን እንደጎዱት ህዝባዊ ሃይሉ ባላፈው አንድ አመት እድሜው በሚገባ የተረዳው ጉዳይ ሆኗል። ህዝባዊ ሃይሉ የሚመኘውን የኢትዮጵያ ትንሳኤና ተሃድሶ እውን ለማድረግ እነኝህ ወያኔ ሆን ብሎ ያስፋፋቸውን የባህልና የሞራል ብክለት ማጽዳት የግድ እንደሆነ የተረዳ አካል ሆኗል።
ትግላችን መደፍረስን መጥራትን፣ መንተክተክን መስከንን የትግሉ ሂደት አካል አድርጎ የሚጓዝ ነው። ትግሉ የሚልመጠመጠውን እንደቀስት ቀጥ ብሎ ከሚራመደው፣ በካፊያው የሚንቀጠ ቀጠውን ለዶፉ ደንታ ከሌለው፣ ዝናር በቅፌን ከምሩ ተኳሽ የሚለይ መራራ ትግል ነው። ያለፈው አንድ አመት ይህን አስተምሮናል። ህዝባዊ ሃይሉ ትግሉ ቀላል ነው የሚል ከእውነታ ጋር ያልተያያዘ ቃል ለህዝብም ሆነ ህዝባዊ ሃይሉን ሊቀላቀሉት ለተዘጋጁት ወገኖቹ አይናገርም። ህዝባዊ ሃይሉን ለመቀላቀል ለተሰለፉ በሽዎች ለሚቆጠሩ ወገኖቻችን ትግሉ የሚጠየቅውን የሞራል የስብእና ጥብቅነት፣ከፍተኛ የሃገርና የወገን ፍቅር፣ ጥልቅ የሆነ የመስዋእትነት ፈቃደኛነት የሚጠይቅ መሆኑን ከማስረዳት አንቦዝንም። ህዝባዊ ሃይሉ ለህዝብ ቃል እንደገባው ከወያኔ ጋር የምናደርገው ትግል በጥበብ በእውቀት በጥናት በጥንቃቄ የምናደርገደው ነው። ነጻነት ያለመስዋእትነት እንደማይሳካ ብናውቅም ለተራ የፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ስንል በቂ ዝግጅት ያልተደረገበት የሃገሪቱን ውድ ልጆች በከንቱ የሚማግድ ጀብደኛ እንቅስቃሴ አናደርግም። የውሸት ተስፋ ህዝብን አንመግብም። አይናችንን ከዋናው የኢትዮጵያና የህዝቧ ጠላት ከሆነው ከወያኔ ላይ አንስተን በሌሎች ወያኔን እቃወማለሁ በሚሉ ሃይሎች ላይ አንተክልም። ከወያኔ ሌላ ወደ ጎን የምንዋጋው፣ የምንጨቃጨው አታካራ የምንገጥመው ምንም ሃይል አይኖርም። ወያኔን ለመምታት ህዝባዊ ሃይሉ የጨበጠው ቡጢ ወገኖቻችን በፍቅር ለመጨበጥ የሚዘረጉ ጣቶች እንዳሉት በጸረ ወያኔ ዴሞክራሲያዊ ትግሉ ከልባቸው ለመተባበር ለሚፈልጉ ሃይሎች ሁሉ ግልጽ እናደርጋለን።
ያለፈው አንድ አመት የመሰባሰብ የድርጅት ምስረታ መሰረታዊ የሆኑ የፖለቲካና የወታደራዊ ስልጠና የተሰጠበት፣ የድርጅት ማጠናከሪያና የማጥራት ሂደት የተካሄደበት ነው። በዚህ ረገድ የተሰራው ስራ አጥጋቢ ውጤት አስገኝቷል። ስልጠናው፣ ድርጅት ማጠናከሩና ማጥራቱ ወደፊትም የሚቀጥል ነው። መጪውን አመት የተለየ የሚያደርገው ህዝባዊ ሃይሉ በህዝብ ላይ በሚደርሰው ግፍና ውርደት ከሚሰማው ከፍተኛ ብስጭትና ቁጭት አልፎ ባላፈው አመት ሊደርስላቸው ያልቻለውን የሃገራችንን ግፉአን ህዝቦች መታደግ የሚችልበትን እርምጃዎች መውሰድ የሚችልበት አመት መሆኑ ነው። በዚህ የህዝባዊ ሃይላችን የአንደኛ አመት ምስረታ ክብረ በአል ወቅት ወገንም ጠላትም በግልጽ እንዲያውቀው የምንፈልገው ይህን ሃቅ ብቻ ነው።
ውድመት ለዋናውና ለብቸኛው የኢትዮጵያ ህዝብና የኢትዮጵያችን ጠላት ለሆነው የወያኔ ገዥ ጉጅሌ!!!!
ድል በወያኔ ግፈኛ ስርአት አበሳውን ለሚያየው የመላው የኢትዮጵያ ህዝብ!!!!!!
የግንቦት 7 ህዝባዊ ሃይል የተመሰረተበትን አንደኛ አመት አስመልክቶ የተሰጠ ድርጅታዊ መግለጫ, Audio  (mp3)

ምንጭ: www.ginbot7pf.org