ዋግሹም ጎበዜና አፄ ዮሐንስ ከአፄ ቴዎድሮስ
ህልፈት በኋላ እኔ ልንገስ እኔ ልንገስ በሚል ለጦርነት ሲዘጋጁ ዋግሹም ጎበዜ ስልቻ ሙሉ ጤፍ ለአፄዉ ይልኩላቸዋል። መልዕክቱ .
. . ዋ! ብዙ ሠራዊት አለኝ የሚል ነበር
አፄ ዮሐንስም የዋዛ ሰዉ አልነበሩም፤ ስልቻ ሙሉ ጤፍ
እንዳለ ቆልተዉ ይመልሱላቸዋል። እሳቸዉ የላኩትን ስልቻ ሙሉ ጤፍ አንጂ ተቆልቶ የተመለሰላቸዉን ጤፍ ጉዳይ ከመጤፍ ያልቆጠሩት
ዋግሹም ጎበዜ ከአፄ ዮሐንስ ጋር ሁለቴ ጦርነት ገጠሙና ተሸንፈዉ እጃቸዉ ተያዘ። እጃቸዉ ከተያዘ በኋላ ያለዉ ታሪክ አያምርምና
ልተወዉ።
ወገን . . . የዛሬዉ ጉዳዬ ከነዚህ የቀድሞ ነገስታቶቻችን ጋር አይደለም። አንድ ሳልጠቅሰዉ ማለፍ የማልፈልገዉ ጉዳይ
ቢኖር ግን አፄ ዮሐንስ በጠመንጃ ኃይል ሥልጣን ከያዙ ከአንድ መቶ አርባ አመታት በኋላ ዛሬም ኢትዮጵያ ዉስጥ የስልጣን ሽግግር
መልኩን አልቀየረም።
ትልቁ ችግር ከቀብር መልስ ነዉ። እዎ! ከቀበር መልስ። ያ’ ሁሉ ስድብ፤ ንቀት፤ ዛቻ፤ እብሪት፤ አገር መበተንና ማን አለብኝ ብሎ መፎከር እንዲህ “ሃምሳ ስምንትን” ፈርቶ በግማሽ ሜትር ጨርቅ ተጠቅልሎ ለመሰናበት ነዉ። አቤት እግዚኦ! ከወያኔ ጋር ተቀላቅለን ባናዉቅም እነሱ እየገደሉ እኛ እየቀበርን ጎን ለጎን ስንኖር ሃያ አንድ አመት አለፈን።
ከአሁን በኋላ . . . በቃ! ተራዉ የህዝብ ነዉ። በነጋ በጠባ እየቀበሩ መኖር በአንድ ሰዉ ቀብር አከተመ። ወያኔዎች የሚማሩ ከሆነ ከላይ ከፍ ሲል ከቋጠርኩት ስንኝ ወይም ከዋግሹም ጎበዜ ታሪክ ይማሩ። አንማርም ካሉ ግን የነሱ ግዜ ላይመለስ አክትሟል። ከቀብር መልስ ግዜዉ የኛ ነዉ።
ሃያ አንድ አመት ሙሉ ሲከፋፍለን፤ ሲያስረንና ሲገድለን ለኖረ ሰዉ ማቅ ለብሳችሁ አፈር ነስንሳችሁ አልቅሱ ተባልን፤ መቼስ ምን ይደረጋል ብለን እምባ ባይወጣንም አለቀስንላቸዉ። አይበቃም ብለዉ ገፉን፤ ገፈተሩን ገንዘብ ብጤም ሰጡንና አገሩን ሁሉ አርሆ አደረጉት። ችግሩ ሁሉም ማዉጣት እንጂ የሚቀበል ጠፍቶ ልቅሶዉ ዘፈን መሰለ። ለሁሉም ሰዉየዉ ገድሎን ስለሞተ ሳይሆን ሞቶም ስለገደለን አለቀስን፤ እነሱ ለሱ ያለቀስን መሰላቸዉ። እኛ ግን ያለቀስነዉ ለራሳችን ነዉ።
ስዩም መስፍንንና በረከት ስምኦንን ለሚያዉቅ ሰዉ ሁለት ሳምንት ሙሉ ድፍን አገር ስራ አቁሞ (ያዉም በልማታዊ መንግስት አገር) ለሚጠላዉ ሰዉ እንዲያለቅስ መገደዱ ብዙም ላይደንቅ ይችላል። እኔን የገረመኝና እግዚኦ ያሰኘኝ የአገራችን የክርስትና እምነት መሠረት ከሆነችዉ ከትግራይ መሬት የበቀሉ ሰዎች እንደ ናቡከደነፆር ህዝብ ለምስል እንዲሰግድ ማስገደዳቸዉ ነዉ።
ለዚያዉም በኃጢያት ተጨማልቆ ለሞተ ክፉ ሰዉ ምስል። መቼም አባ ጳዉሎስ ስራ እንዳይበዛባቸዉ ቀድመዉ ሄዱ እንጂ እንዲህ አይነቱ ኃጢአት በበርሜል ጠበልም የሚነፃ አይመስለኝም። ለሰዉ ቢሰገድ ኖሮ ስንት የሚሰገድለት አበሻ ነበር።ግን ምን ይደረግ ጋኖች አለቁና ሆነ ነገሩ። ለሁሉም አይዞን አባቶቻችን “ሊነጋጋ ሲል ይጨልማል” ያሉት ነገር እዉነት ነዉ።
የፌዴራል ስርአት ገንብተን አገር አረጋግተናል መሪ ቢሞት መሪ ይተካል እያሉ በየመገናኛ አዉታሩ ሲጨፍሩ ያየናቸዉ የወያኔ መሪዎች እንኳን አገር ማረጋጋት ታምሞ የሞተ ሰዉ እንኳን መተካት አቅቷቸዉ አገራችንን መሳቂያና መሳለቂያ አድርገዋታል። በእኛዉ ድጋፍ ነፃነቷን የተጎናፀፈችዉ አገር ጋና ፕሬዚዳንቷን ባጣች በሃያ አራት ሰዐት ዉስጥ ሌላ ፕሬዚዳንት አግኝታለች።
ይህ የሆነዉ አስተዋይ የሆኑ የጋና መሪዎች ህገ መንግስቱን ከራሳቸዉ አንጻር ሳይሆን ከአገራቸዉ ጥቅም ጋር አያይዘዉ ስለ ጻፉት ነዉ። የኛዎቹ ስስታሞችና ጭፍኖች ግን ህግ አዉጭዉም ሆነ ህግ አስፈጻሚዉ እነሱ እራሳቸዉ ስለሆኑ እነሆ አገራችን ካለ መሪ ሩብ አመት እየሞላት ነዉ።
እፍረት የሚባል ነገር በማያዉቀዉ አፋቸዉ መለስ በ80 ሚሊዮን ሰዉ ተተክቷል እያሉ በተግባር ግን ከደቡብ ክልል የመጣዉን የኃ/ማሪያም ደሳለኝን ጠ/ሚኒስትርነት መቀበል አቅቷቸዉ የሱን ሹመት ለማጽደቅ የተጠራዉን ፓርላማ አዘግይተዉታል።
ሰለ ወያኔ ብዙ ሰምተናል ብዙም አይተናል። የሚበቃን ይመስለኛል። አነዚህ ጉደኞች ወይ እነሱ አይጠፉ ወይ እኛ አላጠፋናቸዉ መለስ-ወያኔ ወያኔ መለስ ስንል እነሱ ሲገቡ የተወለደ ልጅ እሱ እራሱ ወልዶ አባት ሆኗል።
ደግነቱ መለስ ሃያ አመት ቀጥቅጦ ቢገዛን የፀደቀ መስሎት ቸኮለ መሰለኝ ላይመለስ ወደ ፈጠሪዉ ሄዷል። አሁን የቀረን ወያኔ ብቻ ነዉ። ያ’ መለስ ቁጭ ቁጭ አድርጎ የፈጠረዉ ጥርቅምቅም ነገር . . . ኢህአዴግ ነዉ “ስድ አደግ” አሁንስ ስሙም ጠፋኝ።
ለሁሉም እሱን ተዉት ታምሞ ብራስልስ ባይሄድም ከመለስ ጋር ሞቷል። ቀድሞዉኑስ ቢሆን አንዱ ታቦት ሌላዉ ጣዖት ሆነዉ ኖሩ እንጂ ኢህአዴግና መለስ መች ተማምነዉ ያዉቃሉ።
አገራችን ኢትዮጵያ ቢዘረዝሩት መቋጫ ቢቆጥሩት ማለቂያ የሌለዉ ብዙ ችግሮች አሏት። የችግራችን ሁሉ ቁልፍ ግን አንድ ነዉ። አሱም የአገራችን ሁለቱ ዋና ዋና መዋቅሮች (ፖለቲካዉና ኤኮኖሚዉ) እኛ ብቻ እንብላ በሚሉ ስግብግቦች ተተብትቦ መያዙ ነዉ።
ወያኔ እነዚህን ሁለት መዋቅሮች እስከተቆጣጠረ ድረስ የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ የወያኔን ኪስ መሙላት በሚችልበት መልኩ የቁጥር እድገት ሊያሳይ ይችላል፤ ደሃዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ግን “ሺ ግዜ ቢታለብ ለኔ በገሌ” እንዳለችዉ እንስሳ ለሱ ጠብ የሚል ነገር አይኖርም።
ስለዚህ ከዛሬ በኋላ እኔ “ድያስፖራ” ነኝ እኔ “የአገር ቤት” ነኝ የሚባል ነገር የለም፤ ለመጣዉ ነገር ሁሉ እንደ ብረት እየጋሉ መብረድም የለም። ትግላችን ከሰላማዊ ሠልፍ፤ ከአዳራሽ ዉስጥ ፉከራና ከፓልቶክ ጩከት እልፍ ማለት አለበት። እነዚህ ሁሉ አስፈላጊ ናቸዉ ግን ሺ አመት ብንሰበሰብ ወይም ኦቫል (Oval Office) ዉስጥ ገብተን ሰላማዊ ሰልፍ ብናደርግም እጃችንና እግራችን ተንቀሳቅሶ ስራ ካልሰራ ወያኔን ማሸነፍ ቀርቶ ማስደንገጥም አንችልም።
ወያኔን አስወግደን (በትጥቅ ትግል) ወይም አስገድደን (በህዝባዊ አመጽ) ኢትዮጵያን ማዳን ብንወድም ባንወድም ታሪክ የጣለብን ሀላፊነት ነዉ። ይህንን ለማድረግ ደግሞ በመካከላችን መደጋገፍ እንጂ መወዳደር አያስፈልግም። ትግሉ በወያኔና በእኛ መኃል ነዉ እንጂ በአስወጋጆችና በአስገዳጆች መካከል አይደለም።
ወያኔ ሀያ አመት ሙሉ ሲከፋፍለን፤ሲያስረን፤ ሲገድለንና አገራችንን ለባዕዳን ሲሸጥ ያደርግነዉ ነገር ቢኖር አንድ ሰሞን ቁጣ፤ አንድ ሰሞን ጩኸት አንድ ሰሞን ዉግዘት ብቻ ነበር። እንደዚህ አይነቱ የአንድ ሰሞን ትግል ዬትም አላደረሰንም። መለስ የሞተዉ በፈጣሪ ቁጣ ነዉ እንጂ በእኛ ጩኸት አይደለም።
ዛሬ አድገናል ጥርስም አዉጥተናል ስለዚህ መንከስ መጀመር አለብን። ወያኔን መንከስ ያለባቸዉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ አይደሉም፤ የፓሪቲ መሪዎች ወይም የሲቪል ማህበራት ብቻም አይደሉም። ወያኔን መንከስ ያለበት ጥርስ ያለዉና አገሩ የተነከሰችበት ኢትዮጵያዊ ሁሉ ነዉ። እኛ ኢትዮጵያዉያን በመታደል ስማችን ካለመደፈርና ከጀግንነት ጋር የተቆራኘ ነዉ።
አለመደፈራችንና በነጭ አለመገዛታችን ደግሞ የኩራታችን ሁሉ ምንጭ ነዉ። በኔ ግምት የዚህ ኩራት ምንጭ አባቶቻችን ናቸዉ እንጂ እኛ አይደለንም። እየተገዙ ኩራት የለምና እኛም እንዳባቶቻችን የኩራት ምንጭ የምንሆነዉ በነጭ ብቻ ሳይሆን በጥቁርም መገዛት ስናቆም ነዉ።
በ1966 ዓም አንድ ብለን ጀምረን ሁለትና ሦስትን ጠርተን መደምደም አቃተንና ደርግ አስራ ሰባት አመት ጨፈረብን። በ1983 ዓም ሁለት ብለን ሦስትን ፈራናትና ወያኔ አሁን ድረስ እየጨፈረብን ነዉ። ይህ ስህተት ዘንድሮ መቆም አለበት። “ሠራገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ” ትግል ማክተም አለበት።
የዘንድሮዉ ትግላችን ወያኔን ለማስወገድ ብቻ ሳይሆን ወያኔ አገራችን ዉስጥ የመጨረሻዉ አምባገንን ስርአት እንዲሆን ጭምር ነዉ። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ለእኛ፤ ለወያኔም ሆነ በ”መረጋጋት “ ስም ለበደለን የአለም አቀፉ ህብረተሰብ ከአሁን የተሻለ ግዜ የለም።
የአሜሪካ መንግስት በመረጋጋት ስም የኢትዮጵያ ህዝብ መብት ሲረገጥ ዝም ብሎ መመልከቱን ማቆም አለበት። ጭንቅላቱን ያጣዉ የወያኔ አገዛዝም ካለ እኛ ለኢትዮጵያ የሚበጃት የለም የሚለዉን የጅል አባባሉን አቁሞ የአገሪቱን የፖለቲካ በር ከፍቶ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚበጀዉን እራሱ እንዲመርጥ መፍቀድ አለበት።
ከሁሉም በላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች የተሻለ ነዉ የሚሉትን አማራጭ ይዘዉ መቅረብ አለባቸዉ። ምድረ ተቃዋሚ ሁሉም በየፊናዉ አማራጭ የሚባል ነገር ሳይይዝ ባዶ እጁን ዉጭ ጉዳይና ኮንግረስ ሎጥ ሎጥ ማለቱን ቢያቆም ደስታዉን አንችለዉም። እቺ የብቻ ሎጥ ሎጥ አንዳችን ሌላችንን አማንባት እንጂ (ያዉም ለነጮች) ትግላችንን አንድ ስንዝር እንኳን ወደፊት ገፍታዉ አታዉቅም።
ከወር በፊት ሞቶ ከሁለት ሳምንት ፍትሀት በኋለ ትናንት የተቀበረዉ መለስ ዜናዊ ነዉ አንጂ ወያኔ አሁንም አልሞተም። በእርግጥ ወያኔ በመለስ ሞት ጭንቅላቱ ተቆርጦ የቀረዉ ግማሽ አካሉ ነዉ፤ ሆኖም ወያኔ የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊት፤የፖለቲካ ሥልጣንና የኤኮኖሚ አዉታሮች እስከተቆጣጠረ ድረስ ሌላ ጭንቅላት አብቅሎ ልግዛችሁ ማለቱ አይቀርም።
የኢትዮጵያ የፖለተካ ኃይሎች ወያኔ መለስን ተክቶና እራሱን አደላድሎ እንደለመደዉ “አገር አማን ነዉ” ማለት እስኪችል ድረስ ግዜ ከሰጡት እነሱ እንኳን ኢትዮጵያን ሊታደጉ እራሳቸዉንም ማዳን አይችሉም። እራሱን ማዳን ያልቻለ ደግሞ ሌላዉን ማዳን አይችልም።
ስለዚህ የሚሰማ ጆሮ ያለዉ ሁሉ ይስማ – ኢትዮጵያን ማዳን በኋላ አይደለም አሁን ነዉ፤ ነገም አይደለም ዛሬ ነዉ። ኢትዮጵያን ማዳን ደግሞ ለእኔ፤ ለእሷና ለእሱ የሚተዉ ስራ አይደለም። ኢትዮጵያን ማዳን የእኛ ስራ ነዉ። ትግሉ አንዳንዶቻችንን ኢትዮጵያን ሂዱ ብሎ ሊጠራን ይችላል፤ ከኢትዮጵያም ወደ ዉጭ ሊያስወጣን ይችላል ወይም የሳሎን ዉስጥ ፎቴ የሚቆረቁረን ቅምጥሎች በረሃ ገብተን ከላይ የፀሐይ ሀሩር ከታች ያልተጠረበ ድንጋይ ምነዉ ባልተፈጠርኩ ሊያሰኘን ይችላል።
እንቻለዉ! ነፃነት ከዚህም በላይ ያስከፍላል። አለማችን ህይወቱን ለነፃነት የሚሰዋ ጀግና መድረክ እንጂ እየበላ የሚሞት ቦቅቧቃ ጓዳ አይደለችም. . . ሆናም አታዉቅም። ሃያ አመት ሙሉ ደደቢት እያልን ተሳልቀናል፤ ጽፈናል ተናግረናል። ማዉራት በጣም ቀላል ነዉ። እሾክን በእሾክ ነዉና እስኪ እኛም ደደቢት እንግባ።
ምነዉ ዛሬስ ተንጣጣ ትሉኝ ይሆናል። ምን ላድርግ ወድጄማ አይደለም። እሳቱ እንደገና ዳቦ ከላይም ከታችም ቢለበልበኝ ነዉ እንጂ። ወይ ጉድ! ምነዉ ተንጣጥቼም ቢሆን በወጣልኝ። እሱ ኖሮልኝ እኔ ያልኖርኩለት የኢትዮጵያ ህዝብ፤ ሳይማር ያስተማረኝ ተርቦ ያጠገበኝ የኢትዮጵያ ገበሬ፤ ከመዶሻ ጋር ተጋፍጦ ብረት ቀጥቅጦ ያሳመረኝ የኢትዮጵያ ሰራተኛ ዕዳ ከበደኝ፤ የእምነት ቃል አደራዉ ጨነቀኝ።
ጩኸቱ ባህር አቋርጦ ተከተለኝ፤ አልሰማሁም ብዬ ብሸሸዉ መደበቅ አቃተኝ። ኡኡታዉ ጆሮዬ ዉስጥ አቃጨለ የጣረሞት ድምጹ ሆዴ ዉስጥ ዘለለ። እንግዲህ ለምን አልንጣጣ። አንተስ ወንድምዬ አንቺስ እህቴ ምን እያሰባችሁ ነዉ? ከቀብር መልስ ጉዞህ ወዴት ነዉ? አንቺስ ጉዞሽ ወዴት ነዉ? ወንድሜ ቁርጥህን እወቀዉ . . . መይሳዉ ድረስልኝ እንዳትል እሱ ሽሽት አያዉቅም።
እህት አንቺም “በጣይቱ ሞት” እንዳትይ ጣይቱ ጠላትን ማመስ እንጂ ለፈሪ መድረስ አታዉቅበትም። እቺ የምንወዳት ኢትዮጵያ የኛ የሆነችዉ መይሳዉ ሽጉጡን ስለጠጣላትና ጣይቱም ያንን ሶላቶ ወግድ ስላለችዉ ነዉ። ከእኛም የሚጠበቀዉ ይህ ብቻ ነዉ። አባቶቻችን ጥለዉልን ያለፉት ጠላትን ማስጮህ እንጂ ጠላት ላይ መጮህን አይደለም።
አንድ እዉነት ወለል ብሎ ይታየኛል። እኛ ፈለግን አልፈለግን፤ ወያኔም ወደደ አልወደደ ወይም ምዕራባዉያን ተስማሙ አልተስማሙ ከቀብር መልስ ኢትዮጵያ እንደትናንቱ አትቀጥልም። የኢትዮጵያን የወደፊት አቅጣጫ ወያኔ ብቻዉን ወይም እንደ 1983ቱ ምዕራባዉያንና ወያኔ ብቻ እንዲወስኑ መፍቀድ የለብንም።
የአሜሪካና የእንግሊዝ ህዝብ እራሱን በእራሱ እንደሚመራ ሁሉ የኢትዮጵያም ህዝብ እራሱን በእራሱ እንዲመራ ዕድል ሊሰጠዉ ይገባል። ከዚህ ዉጭ በእነሱ ቋንቋ “መረጋጋት” በሚሉት የሻገተ ቃል አምባገነንነትን ለማራዘም የሚያደርጉትን ሩጫ እንኳን ኖረን ሞተንም መቀበል የለብንም።
የአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት ከማንም በላይ የሚጠቅመዉ የኢትዮጵያን ህዝብ መሆኑን አፍቃሬ ወያኔ የሆኑ ምዕራባዉያን መንግስታት ሁሉ ሊገነዘቡት ይገባል። የኢትዮጵያን ህዝብ ጥቅምና ፍላጎት የማይጠብቅ በምዕራባዉያን ፍልጎትና በወያኔ የ “እከከኝ ልከክህ” ተንኮል ላይ የተመሰረተ የአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት ዬት እንዳደረሰን አይተናልና ለኢትዮጵያ ከኢትዮጵያዉያን በላይ እናስባለን የሚሉን ከሆነ 1928 (ጄኔቫን)፤ 1968 (ጂሚ ካርተርን) 1983 (ሄርማን ኮህንን) ልናስታዉሳቸዉ ይገባል።
ከአሁን በኋላ ኢትዮጵያን የሚያዋጣትና የሚበጃት መንገድ ለሁላችንም ግልጽ የሆነ ይመስለኛል። የኢትዮጵያ ህዝብ በዲሞክራሲ ተሳስሮ በክልልም ሆነ በማዕከል እራሱን በእራሱ ማስተዳደር መጀመር አለበት።
አዲስቷ ኢትዮጵያ ቤተመንግስት ዉስጥ ሆኖ የሚመራትን መሪዋንና “ስለ ማሪያም” እያለ ለምኖ የሚያድረዉ ዬኔ ብጤ ደሃ ልጅዋን እኩል የሚዳኝ የፍትህ ስርአት መገንባት አለባት። የአገራችንን ወጣቶች የወደፊት እድል የሚወስነዉ የተወለዱበት ዘር ሳይሆን ችሎታቸዉና ባህሪያቸዉ ብቻ መሆን አለበት።
እነዚህ ህዝባዊ እሴቶች በሌሉባት ኢትዮጵያ ዉስጥ አወቅን፤አደግን ተማርን ብንልም ተጠቃሚዉ እንደተለመደዉ ጠመንጃ የያዘዉ አካል ብቻ ይሆናል። ይህ የማያወላዉል የኢትዮጵያ ህዝብ አቋም ነዉ፤ ይህንን ቁርጠኛ አቋማችንን ደግሞ የዉጭ ሸረኞችም ሆኑ የኛዉ አገር መሬት ያበቀላቸዉ ዳተኞች አጥብቀዉ ሊገነዘቡት ይገባል።
በህዝብ ስም እየመጡ ህዝብን መበደል፤ ነፃ አወጣንህ እያሉ በባርነት መግዛትና እኩልነትን እየሰበኩ በዘር ተመራርጦ መሿሿም ከወያኔ ስርአት ጋር ሞቶ መቀበር አለበት። ትግሉን እኛ ብቻ ካልመራነዉ ለምትሉን ሁሉ ወይ ትግሉን ተቀላቀሉ አለዚያም መንገድ ልቀቁ። የሚገባችሁ ከሆነ ትግል መሪ ይፈጥራል እንጂ መሪ ትግሉን አይፈጥርም።
አገራችሁ ኢትዮጵያም የልጆቿን ፍላጎት እንጂ የእናንተን ስስት ማርካት አትችልም። ከአሁን በኋላ በዉጭም ሆነ አገር ቤት የሚኖረዉ ኢትዮጵያዊ የህዝብን ትግል የሚጎትቱና የድሉን ቀን የሚያራዝሙ ደንቃራዎችን በግልጽ ወጥቶ አላዉቃችሁም ማለት አለበት።
ያለፈዉን ሃያ አንድ አመት ታሪክና የዚህ እስቀያሚ ታሪክ መቋጫ የሆነዉን ታይቶም ተሰምቶም የማይተወቅ የአስራ አምስት ቀን ትንግርት ወደኋላ ትተን ትግላችን ላይ ብቻ ካላተኮርን እራስ ምታቱንና ሆድ ቁርጠቱን የምንችለዉ አይመስለኝም። የኢትዮጵያን ህዝብ ምረጠኝ ብሎ ያስገደደዉ ወያኔ ቁንጮዉ ሞቶበት አላቅሱኝ ብሎ ህዝብን በግድ አደባባይ ማስወጣቱ ብዙም አልገረመኝም።
መሪዉን ለመምረጥም ሆነ ለመቅበር ተገድዶ የወጣዉ የኢትዮጵያ ህዝብም ወያኔን ያዉቀዋልና ብዙ የሚገርመዉ አይመስለኝም። እኔን የገረመኝ “ለምስል አትስገድ” የሚለዉን ቃለ እግዚአብሄር የሚያስተምሩት ቀሳዉስትና መነኮሳት መስቀላቸዉን አንጠልጥለዉ እየተመለከቱ የኢትዮጵያ ህዝብ ለምስል ሲሰግድ ማየቴ ነዉ።
እግዚአብሔር ተመልካቾቹንም አስገዳጆቹንም ይቅር ይበላቸዉ! ደግነቱ ይህ ሁሉ አልፎ ዛሬ ከቀብር መልስ አዲስ ምዕራፍ ላይ ነን። ዛሬ ወያኔን ከላይም አየነዉ ከታች አንድ እግሩ ተቆርጦ በአንድ እግር ብቻ የቆመ ድርጅት ነዉ። እቺን የቀረችዉን እግሩን ቆርጠን የኢትዮጵያን ህዝብ ከዘረኞችና ከማን አለብኝ ጨካኞች ነፃ የምናወጣበት ግዜ አሁን ነዉ። ይህንን ማድረግ ከተሳነን እኛም ላይ “አንድ እግር በርበሬ መንቀል አቅቷቸዉ . . . “ ተብሎ ሊዘፈን ይችላል።
የኢትዮጵያ ህዝብ የሚፈልጋት ኢትዮጵያ ተረግዛለች። ከአሁን በኋላ የቀረን ማዋለድ ብቻ ነዉ። እኛንም ሆነ መጪዉን ትዉልድ እያስደሰተ የሚኖረዉ የአዲስቱ ኢትዮጵያ ልደት ነዉ እንጂ ማን አዋለዳት የሚለዉ ጥያቄ አይደለም። ልደት የአባትና የእናት ዉህደት ዉጤት ነዉ እንጂ የ “እኔነት” መገለጫ አይደለም። የአዲስቱ ኢትዮጵያ አባቶች ተብለን የምንዘከርበት ግዜ ቀርቧል።
የኢትዮጵያ ህዝብ እየተጎተተ የሚታሰርበት፤ እየታደነ የሚገደልበትና በገዛ አገሩ ተዋርዶ የሚኖርበት ክፉ ዘመን ማክተሚያ ዋዜማ ላይ እንገኛለን። ይህ ትዉልድ እናት አገሩ ኢትዮጵያ የገጠማትን ፈተና ሁሉ አልፎ በአሸናፊነት ለመወጣት ቃል የገባ ትዉልድ ነዉ፤ ቃል ደግሞ የእምነት እዳ ነዉ።
ከላይ ከፍ ሲል እንደጠቀስኩት ቃል የገባነዉ ወያኔን የመጨረሻ አምባገነን ስርአት ለማድረግ ነዉ። እንገዲህ ከዛሬ በኋላ አገራችን ኢትዮጵያ የሚቆምላት ትሁት ሰዉ እንጂ የሚቆምባት ጨካኝ መሪ አትፈልግም. . . እሱማ ሰለቻት!
No comments:
Post a Comment